Sunday, 16 June 2019 00:00

ማጣፊያ ያጠረው ፌዴራላዊው ሥርዓት

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)


           “--የጉራጌ፣ የከምባታ፣ የሀዲያ ሕዝብም የክልልነት ጥያቄ ለማቅረብ ሠልፍ አድርገዋል፡፡ በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚጎርፈው ጥያቄ
ማብቂያ ያለው አይመስልም፡፡ አብዛኞች በደቡብ ክልል የሚገኙ ጽንፈኞች፤ የክልል ጥያቄ የሚያቀርቡት፣ ለሰፊው ሕዝብ በረከት ያመጣል ብለው አይደለም፡፡ ጥያቄውን የሚያነሱት ከዞንነት ወደ ክልልነት ሲታደግ የሚቀራመቱትን በጀት እያሰሉ ነው፡፡--”

                ኩርማን እውነታ
ባለፈው ዓመት ሀገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለመግባት በቋፍ ላይ በነበረችበት ወቅት አዲሱ የለውጥ አስተዳደር ማንም ባልገመተውና ባላሰበው ደረጃ ለጥቂት እንደታደጋት ይታወቃል፡፡ ይኽም ሆኖ ግን ሥርዓት አልበኝነት በኹሉም የሀገሪቱ ክፍል ላይ ነግሷል፡፡ ለዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈፀሙት  የመንጋ ፍርዶችንና ማፈናቀሎችን ዋቢ ማድረግ እንችላለን፡፡ የለውጡ ሽግግር በፈጠረው ክፍተት ምክንያት የየአካባቢው የዘውግ አለቃዎች፣ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊት ለመፈጸም ችለዋል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ወይ አቅም አንሶታል ወይም ጽንፈኞች ለሚጎስሙት የዕልቂት ነጋሪት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡
የብሔር ነጋዴዎች ቋንቋን መሠረት ያደረገ አዲስ የክልልነት ጥያቄ ተቀባይነት አንዲያገኙ ሳይታክቱ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁን ሀገራችን ለገባችበት ቅርቃር ዋንኛው መንስኤ፣ ፌዴራላዊው ሥርዓት እንደሆነ ከማንም የተሰወረ ሐቅ አይደለም፡፡
ፌዴራሊዝሙ ምን አሳጣን?  
የ1987ን ሕገ መንግሥት ተክትሎ የተተከለው ፌዴራላዊው ሥርዓት፤ ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር ጠበኛ ነው፡፡ ሥርዓቱ የቆመው በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መርህ በዋጀ በፓርቲ አምባገነናዊ የእዝ ሰንሰለት ሲሆን ዋንኛ የማዋቀሪያው መስፈርት የቋንቋ ማንነት ብቻ ነበር፡፡ በርግጥ ፌዴራላዊው ሥርዓቱ፣ ላይ ላዩን ቋንቋን ማእከል ያደረገ ቢመስልም፣ ጠለቅ ብለን ስንመረምረው፣ አጥንት ቆጠራ ወይም ደማዊ ማንነት ዋንኛ መለያው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለአብነት ሲዳማ ዞን ተወልዶ ያደገ፣ ቋንቋውንም አቀላጥፎ መናገር፣ የካበተ ልምድና ትምህርት ካለው የአማራ ብሔር ተወላጅ ይልቅ ባህር ማዶ ተወልዶ ያደገ ሲዳማ የአመራርነት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡  
ሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘውጌን የሚረዳበት ማእቀፍ ምንዝላታዊ መሳሳብ /Premordial connection/ ነው፡፡ ይህ ዓይነት እሳቤ ግን ከሀገራችን ሕዝቦች ነባራዊ ሁኔታ ጋር ኩታገጠም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዘመናት የእርስ በርስ  ትስስር የተነሳ ከምንዝላታዊ መሳሳብ ይልቅ ማኅበራዊ ሥሪት /Social Construction/ ይገልጻቸዋል፡፡ በርዕዮተ ዓለም ጣልቃ ገብነት ጠባብ ዓላማን አንግቦ ገቢራዊ የሆነው ፌዴራላዊው ሥርዓት የመርገም ማድጋው /ፓንዶራ ቦክሱ/ ተከፍቶ ዙሪያ ገባችንን ማመስ ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የተፈናቀሉት፣ በዘውጉ ፌዴራሊዝሙ የተነሳ ነው፡፡ ሀገሪቱ በውስጥ ተፈናቃይ ብዛት ከዓለም አንደኛ ሆናለች፡፡ ሃያ ሰባት ዓመታት በሀገራችን ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተጭኖ የኖረው የጭቆና ቀምበርን በማጽናቱ ረገድ ይህ የግዛት አወቃቀር ሚናው የጎላ ነበር፡፡ የዘውግ ማኅበረሰቦች ለብዙ ሺህ ዘመናት አብረው የተጋመዱበትን የአንድነትን ሰንሰለት በመበጣጠስ ለሕዳጣኑ ሕወሓት፣ የዘረፋና የግፍ አገዛዝን አውድ፣ ለአውደ ርዕይ አቅርቧል፡፡  
ሥርዓቱ ሀገሪቱ በጥቃቅን የዘውግ አጥሮች የተቀነበቡ ግዛቶችን በመፍጠር፣ በተድላና በፍሰሀ ተከባብረው በኖሩ ሕዝቦች መካከል የጠላትነትና የልዩነት ሰንኮፍ ተክሏል፡፡ ሌላው ይቅርና በዘር ልዩነት ምክንያት፣ ጎጇቸው የፈረሰ ጥንዶችን ቤት ይቁጥራቸው፡፡
ጌዲዮዎች ላይ የደረሰው ትራጄዲ፣ ፌዴራላዊው ሥርዓት በፈጠረው ክፍተት ነው፡፡ የጌዲዮን አክራሪዎች፤ በዲላ ላይ የወሰዱት የግፍና የኃይል  እርምጃ፣ ውሎ አድሮ፣ በጉጂ ዞን በሚኖሩት የብሔረሰቡ አባላት ላይ የአፀፋ ምላሽ እንዲወሰድ አድርጓል፡፡ በማንነት ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች በትውልድ ቀዬአቸው፣ በብሄር ነጋዴዎች ችሮታ ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ ለአብነት በድሬዳዋና በአዋሳ የሚኖሩ ዜጎች፣ እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ ነው የሚቆጠሩት:: ይህ አይነት ከኢኮኖሚና ፖለቲካ ተሳትፎ ያገለለ ሥርዓት፣ ልክ የወደቀው የአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን አምሳያ ነው ቢባል፣ ከእውነታው ጋር መጋጨት አይሆንም፡፡
ጉራማይሌ አቋሞች
ይህንን የዕልቂት ዋሻ ሲምስ የኖረ ሥርዓት፣ በተለይ አክራሪ የኦሮሞና የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች፣ አጥብቀው ሲደግፉት ይስተዋላል፡፡ በርግጥ ጽንፈኞች ከአንድ ባህር ነው የሚቀዱት:: ሁሉም ጠርዘኛ አቋም በማራመድ የሚታወቁት የዘውጌ ቡድኖች፣ በሥርዓቱ ላይ የሚያንጸባርቁት አቋም  ወጥ እንደሆነ እሙን ነው፡፡
በአንጻሩ ገለልተኛ ጸሓፍት በሕወሓት/ኢሕአዴግ አማካኝነት የተተከለው ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪቃ መርገም እንደሆነ አዕንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ፡፡ በኬፕታውን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዮናትን ፍስሐ፤ “The original sin of federalism” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ትንታኔ ላይ፣ ይህንን ሐሳባቸውን አንጸባርቀዋል ፡ “ይህ ለአፍሪቃም ሆነ ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የሚቆጠረው ሥርዓት፤ በውስጡ ብዙ ፀጉረ ልውጥ ባህሪያትን አቅፎ  ይዟል፡፡ የዘውግ ማንነት ከሁሉም የፖለቲካ ማንነት በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት፣ በአንድ ወይም በሁለት ግዛት ላይ የበላይ እንዲሆን የይለፍ ፍቃድ የተሰጠበት ውሳኔ የመርገሙ ጅማሮ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በዘውግ መስመር የሚሰባሰቡ ኃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ተጽኗቸው እየበረታ እንዲሄድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡”  
የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲው ልኂቅ መሐመድ ማምዳኒ፤ ፌዴራል ሥርዓቱ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በየክልሉ ፈጥሯል ይላሉ፡፡ የሀገሪቱን ሕዝቦች ታሪካዊ ኹነትን ታሳቢ ሳይደርግ፣ በግብር ይውጣ እንደተጫነ ያብራራሉ፡ “የዘውግ ፌዴራሊዝሙ በውስጡ ብዙ የተዛነፉ መርህዎችን ታቅፏል፡፡ በዚህም በተግባር የተሳከሩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመውለድ በቅቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ አካባቢ እንደ ኩሬ ተከትሮ አይደለም የኖረው፡፡ ለዘመናት በጋብቻ፣ በንግድና በሥራ ምክንያት በየአቅጣጫው  የትውልድ ቀዬውን ጥሎ ሲፈልስ እንደኖረ የአደባባይ እውነታ ነው:: በአራቱም የሀገሪቱ ጫፎች ያልተበተነ የዘውግ ማኅበረሰብን ማግኘት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ለእነዚህ ዜጎች ምንም አይነት ከለላ አይሰጥም፡፡ ሰነዱ አንዱን ባለቤት ሌላውን ደባል አድርጎ፣ የልዩነት ግምብ ይፈጥራል፡፡”
ከሁለቱ ልኂቃን በተቃራኒ የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የፒኤች.ዲ እጩ ተማሪ የሆነው ጎይቶም ገብረሉእል  በአልጀዚራ ድረገጽ ላይ ባቀረበው ረጅም ሐተታው፤ የፌዴራላዊውን ሥርዓት፤ ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መቀየር፣ ምንም መፍትሄ እንደማያመጣ አጽኖት ሰጥቶ ተንትኗል፡፡ አሁን በሀገሪቱ ላይ የነገሰው ሥርዓት አልበኝነት ምንጩ፣ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ቆሞ ቀር የሆነ አሠራርን በመከተሉ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ የድርጅቱን ባህል ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በመቀየር፣ በሥራ ላይ ባለው ፌዴራላዊ ሥርዓት የሀገራችንን ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰንን ሥልጣን አውን ማድረግ ይቻላል”  ይላል፡፡ “ይህንን ፊዴራላዊ ሥርዓት ወደ ጎን ገፍቶ መልክአ ምድራዊ አወቃቀርን እንደ ብቸኛ የመፍትሄ አማራጭ መቁጠር አመክኖአዊ አይሆንም፡፡ ፌዴራሊዝሙ ላይ ሂስ የሚሰነዝሩ ኃይሎች፤ የሕዝቦችን በራሳቸው ቋንቋ የመዳኘትና ባህላቸውን የማዳበር ነጻነትን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ሕጸጽ ለማረም ሥርነቀላዊ ለውጥ የመፍትሄ አማራጭ አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ የባህል ብዝሃነት የሚያስተናግድን ሥርዓት፣ ካልተማከለ አገዛዝ ጋር የሚኖረውን ግልጽ ያለ የልዩነት መስመር በቅጡ መለየት ይኖርበታል፡፡”
የደቡብ ነባራዊ ሁኔታ
የሲዳማ ጽንፈኛ ቡድኖች በመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ክልላቸውን እንደሚያውጁ መንግሥትን አስጠንቅቀዋል፡፡ የራሳቸውን ሕገ መንግሥት እንዳረቀቁና ለአዲሱ አደረጃጀት ብቁ የሚሆኑ አስተዳዳሪዎችንም ጭምር በመልመል ሂደት ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ክልል በዘጠኝ ዞን የተዋቀሩት ብሔረሰቦች፣ የራሳቸውን ቋንቋ ማእከል ያደረገ ክልልን እያለሙ ነው፡፡ ከወር  በፊት በወላይታ የክልልነት ጥያቄ ያነገበ መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ ተካሄዶ ነበር፡፡ በቀጣይነት የሲዳማ ሴቶች በአዋሳ አደባባይ ላይ ሰልፍ በማድረግ፣ የክልልነት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ የጉራጌ፣ የከምባታ፣ የሀዲያ ሕዝብም የክልልነት ጥያቄ ለማቅረብ ሠልፍ አድርገዋል፡፡ በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚጎርፈው ጥያቄ ማብቂያ ያለው አይመስልም:: አብዛኞች በደቡብ ክልል የሚገኙ ጽንፈኞች፤ የክልል ጥያቄ የሚያቀርቡት፣ ለሰፊው ሕዝብ በረከት ያመጣል ብለው አይደለም፡፡ ጥያቄውን የሚያነሱት ከዞንነት ወደ ክልልነት ሲታደግ የሚቀራመቱትን በጀት እያሰሉ ነው፡፡
በሐዋሳ የሚኖሩ የሲዳማ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ክልል ለመሆን ባላቸው ጥብቅ ምኞት ምክንያት፣ በርካታ የወላይታ ብሔረሰብ አባላትን በግፍ አፈናቅለዋል፡፡ ሀገሪቱ ሰማኒያ የዘውግ ማህበረሰቦች አሏት፡፡ ሁሉም የዘውግ ማህበረሰብ፣ የክልልነት ጥያቄ ቢያቀርብ፣ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው? የሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47፣ ሁሉም የዘውግ ማኅበረሰብ የክልል ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል:: የሲዳማ ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ፣ ለምን የጉራጌና የወላይታ ጥያቄ ቅቡል አይሆንም?
አዲስ ክልል በተፈጠረ ቁጥር ማፈናቀልና ግጭት የሚጠበቅ ነው፡፡ የአዲሱ ክልል ክልሎች ተጨማሪ መሬት ለመቀራመት ግጭት ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው፡፡ ለአብነት የኦሮሞ ማህበረሰብ በሲዳማ ውስጥ የሚገኙትን ቱላ እና አባለን ወደ ኦሮሞ ክልል እንዲጠቃለሉ ጠይቀዋል፡፡ ሲዳማ ክልል ከሆነ በእነዚህ ቦታዎች የተነሳ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ግጭት መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡
የሐዋሳ ዕጣፈንታ
በደቡብ ክልል የተነሳው ጥያቄ ብዙ መዘዞችን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በ1995 ዓ.ም በደቡብ ክልል ምክር ቤት በወጣ አዋጅ፣ ሐዋሳ በራሷ የከተማ አስተዳደር የምትመራ፣ ተጠሪነቷም ቀጥታ ለክልሉ መስተዳደር እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ የሲዳማ ክልልነት ከተረጋገጠ ይህንን አዋጅ በምን አግባብ እንደሚሽሩት ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡ የሐዋሳ እጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው? በከተማዋ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ከተማዋ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላብ ነው የተገነባችው፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥቱ በከተማዋ ላይ  በአፍሪቃ ትልቁ የኢንዱስትሪ ፓርክን ለመትከል፣ በቢሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ አፍስሶበታል፡፡ ስለዚህ የክልልነት ጥያቄ ተቀባይነት እንኳን የሚኖረው ከሆነ፣ ሐዋሳ ልክ እንደ አዲስ አበባ፣ በፌዴራል መንግሥቱ እጅ ካልወደቀች ዳፋው የከፋ ይሆናል፡፡
ሕዳግ
ፌዴራል ሥርዓቱ፤ የሕገ መንግሥቱ የግብር ልጅ ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የጫነብንን ሰነድ፣ አምርረን የምንቃወመው፣ የመቃወም ሱስ ስላለብን አይደለም፡፡ ሀገራችንን አጽንቶ  ያቆመውን ካስማ፣ ከሥር መሠረት  ስለሚያናጋ ነው፡፡ በርግጥ አሁን ላይ ሆነን ሰነዱን ስለ ማሻሻል ማውራት ቅንጦት ነው፡፡ ቅድሚያ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀች ሀገር ትኑረን:: ለዚህ ደግሞ አዲሱን የለውጥ አስተዳደር፣ ከእነ ድክመቱም ቢሆን የመደገፍ ሀገራዊ ግዴታ አለብን፡፡

Read 1506 times