Sunday, 16 June 2019 00:00

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ ላይ የቀረበ ሒሳዊ አስተያየት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል-፫ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የጎደለው ምንድን ነው?
                      ‹‹በዚህ ሜዳ ብዙዎች የመንፈስ ጀግኖች በእምነት ተጋድለዋል፡፡ ሃይማኖት ተአምራት ሰርቷል፡፡ ተራራውን፣ ምድረ በዳውን አፍልሰው የሥልጣኔ መደብር ከተማ አድርገውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በክርስትና ክንፍ ላይ ሆነው አየር አየራት ወጥተው፣ እመቀ እመቃት ወርደው የነገሮችን ባህሪ ለመመርመርና ለመረዳት የህሊና ጥረት አድርገው፣ ከብዙ የሐሳብ ትክክለኛነትና ጽርየት ላይ ደርሰዋል››
                    
            በክፍል-2 ፅሁፌ፣ እጓለ ሥልጣኔን ሲተረጉም ‹‹አምስት ተናባሪ ዋጋዎች (እሴቶች) ያሉት ትልቅ ሕብር›› እንደሆነና እነዚህም ተናባሪዎች ሃይማኖት (ቅድስና)፣ ሥነ ምግባር (ደግነት)፣ ዕውቀት (እውነት)፣ ኪነ ጥበብ (ውበት) እና ኢኮኖሚ (ጠቃሚነት) መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ በእጓለ አስተሳሰብ ከእነዚህ አምስት የሥልጣኔ መሪ አኃዞች ውስጥ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ከአንደኛው በስተቀር አራቱን ያሟላል (ገፅ 63)፡፡
ያሬዳዊው ሥልጣኔ ይቺ የጎደለችውን ወሳኝ የሥልጣኔ መሪ አኃዝ ለማሟላት ለዘመናት ሲታገል ቢኖርም ሊሳካለት ግን አልቻለም፡፡ ለእጓለ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ነገር ደግሞ፣ እንደ በፊቱ ይቺን ጎደሎ በሌሎች እሴቶች እየጠጋገኑ ከዘመን ወደ ዘመን መሸጋገር የማይቻልበት ጊዜ መምጣቱ ነው:: በመሆኑም፣ የእጓለ ዘመንና ትውልድ ከዚህ አፍጥጦ ከመጣ እውነት ጋር መጋፈጥ ግዴታው ሆነ - ‹‹በዘመናችን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር ፊት የተደቀነው ሥራ ይሄ ይመስለኛል›› (ገፅ 78)፡፡
እጓለ ‹‹ጎደለች›› ያላትን ነገር ለማብራራት ረጅም ርቀት ይሄዳል፤ ታሪክን፣ ሃይማኖትን፣ ፍልስፍናንና ባህልን ይፈትሻል፡፡ እጓለ፣ ተዋሕዶን አስፈላጊ አድርጎ ከማምጣቱ በፊት ሥልጣኔያችን ስለ ጎደለው ነገር በደንብ እንድናውቅ ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ ለመሆኑ፣ እጓለ ‹‹ጎደለች›› ያላት ይቺ የሥልጣኔ ፍሬ (እሴት) የትኛዋ ናት?
ለዚህ ጥያቄ የእጓለን መልስ የምናገኘው ‹‹ያሬድ ወይም ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ-II›› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እጓለ፤ አውሮፓውያን በ4 የዕውቀት ዓይነቶች - ማለትም በሥነ ተፈጥሮ ዕውቀት (በሳይንስ)፣ በቴክኖሎጂ፣ በሥነ ምግባርና በውበት ጥበባት (Fine Arts) - እንደሚታወቁ ገልጧል (ገፅ 67)፡፡ እንደ እጓለ አገላለፅ፤ ኢትዮጵያም ከቴክኖሎጂ በስተቀር በሌሎች ሦስት የዕውቀት ዘርፎች (ማለትም በሳይንስ፣ በሥነ ምግባርና በኪነ ጥበብ) ከአውሮፓውያን ጋር የተስተካከለ ደረጃ አላት (ገፅ 74)፡፡
እጓለ በትክክል እንዳስቀመጠው፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አውሮፓውያን በሐብት ረገድ ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ አይቶት የማያውቀውን ብልፅግና ለማስገኘት ችለዋል (ገፅ 50)፡፡ ከላይ የቀረቡትን የእጓለን የተበታተኑ ሐሳቦች ስናያይዛቸው፣ ከአምስቱ የሥልጣኔ ዋጋዎች ውስጥ ያሬዳዊው ሥልጣኔ የጎደለው ‹‹የተጠቃሚነት ዋጋ›› ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እጓለ ‹‹የተጠቃሚነትን ዋጋ የሐብት ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣኔ መሪ አሃዝ ነው›› ብሎታል (ገፅ 63)፡፡ ይሄም ማለት፣ እንደ እጓለ አመለካከት፤ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ‹‹የተጠቃሚነት ዋጋ›› ሊኖረው ያልቻለው በቴክኖሎጂ ኋላቀር በመሆኑና በዚህም የተነሳ ሐብት (የኢኮኖሚ ሥልጣኔን) መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡ ይሄም የሚያመላክተን የእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት ከምዕራባዊው ሥልጣኔ የሚፈልገው ቴክኖሎጂን እንደሆነ ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ እጓለ ከአውሮፓ የሚፈልገው ቴክኖሎጂን ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ በሌላ ቦታ ላይ ‹‹የአውሮፓ ሥልጣኔ በንፁህ የህሊና ጥረት (Pure Reason) የተገኘና ጠቅላላ የሰው መንፈስ ህግ ስለሆነ በሁሉም ህዝቦች ዘንድ የሚፀና ነው፤ እስያውያንና አፍሪካውያንም በትምህርት የራሳቸው ንብረት ሊያደርጓቸው ይችላሉ›› ይላልና (ገፅ 58):: በመሆኑም፣ የእጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት፣ ከምዕራባዊው ሥልጣኔ የሚፈልገው ቴክኖሎጂንና ቴክኖሎጂ ያመነጨውን ህሊና (ትምህርታቸውን) ነው፡፡ ትምህርታቸውን ለንፁህ አንክሮ፣ ቴክኖሎጂያቸውን ደግሞ ለተጠቃሚነት፡፡
እዚህ ላይ አምስት ሒሳዊ አስተያየቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው፣ እጓለ ሳይንስና ቴክኖሎጂን አንደኛው የሌላኛው ግልባጭ አድርጎ ያያቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የተከማቸ የሥነ ተፈጥሮ (ሳይንስ) ዕውቀት እንዳላት ቢነግረንም፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ወደ ቴክኖሎጂ ለምን መቀየር እንዳልቻልን ግን  ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
2ኛ፤ እጓለ ‹‹በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ብዙ ዕውቀቶች ስለ ዓለምና ስለ ህይወት ተገኝተዋል›› (ገፅ 65) ለሚለው ድምዳሜው ማስረጃ አድርጎ የጠቀሳቸው ነገሮች፣ ባህረ ሐሳብንና ተአምራትን ነው (ገፅ 70 እና 65)፡፡ እጓለ ተአምራትን እንደ ዕውቀትና የሥልጣኔ መሰረት አድርጎ ሲጠቅሰው እንዲህ ይላል፡- ‹‹በዚህ ሜዳ ብዙዎች የመንፈስ ጀግኖች በእምነት ተጋድለዋል፡፡ ሃይማኖት ተአምራት ሰርቷል፡፡ ተራራውን፣ ምድረ በዳውን አፍልሰው የሥልጣኔ መደብር ከተማ አድርገውታል (ገፅ 65):: ኢትዮጵያውያን በክርስትና ክንፍ ላይ ሆነው አየር አየራት ወጥተው፣ እመቀ እመቃት ወርደው የነገሮችን ባህሪ ለመመርመርና ለመረዳት የህሊና ጥረት አድርገው፣ ከብዙ የሐሳብ ትክክለኛነትና ጽርየት ላይ ደርሰዋል›› (ገፅ 73)፡፡
እናም እጓለ እዚህ ጋ የሳተው ነገር ቢኖር፣ ተአምራት እንደ ዕውቀት ሊቆጠር እንደማይችልና የሥልጣኔም መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል ነው፡፡ አንድ ሐሳብ ወይም ድርጊት እንደ ዕውቀት ሊቆጠር የሚችለው በዚያ ነገር ላይ ስለ መንስኤው፣ ሂደቱና ውጤቱ የተብራራ መልስና ቁጥጥር ሲኖረን ነው፡፡ ‹‹ተአምራት››ን በተመለከተ ስለ ምንነቱና ሂደቱ እንደዚህ ዓይነት የተብራራ ሐሳብም ሆነ በነገሩ ላይ የበላይነት የለንም፡፡
3ኛ፤ ባሕረ ሐሳብን (‹‹አቡሻህር››ን) በተመለከተ በኢትዮጵያውያንና በግብፃውያን መካከል በጣም የቆየ የባለቤትነት ጥያቄ አለ፤ ውዝግቡ አሁንም ድረስ እልባት አላገኘም፡፡ ‹‹አቡሻህር›› ከሚለው የአረብኛ ስያሜ በመነሳት ባለቤትነቱን ለግብፅ የሚሰጡ በርካታ ሊቃውንት አሁንም ድረስ አሉ፡፡ እንግዲህ፣ ይሄ ውዝግብ ባልሰከነበት ሁኔታ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያውያን ስለ መሆኑ አሳማኝ ማስረጃ ባላቀረበበት ሁኔታ፣ እጓለ ባህረ ሐሳብን የጥንት ኢትዮጵያውያን ሳይንሳዊ ሥራ አድርጎ እንደ ማስረጃ ማቅረቡ ትክክል አይደለም፡፡
4ኛ፤ የባሕረ ሐሳብ ባለቤትነት የእኛ እንኳን ቢሆን፣ ባሕረ ሐሳብ ብቻውን በሳይንሳዊ ዕውቀት ዘርፍ ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ጋር ሊያስተካክላት አይችልም፡፡ ምክንያቱም፣ አውሮፓውያን ከቀን መቁጠሪያ ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ዕውቀቶችን በየዘመናቱ አከማችተዋልና፡፡
5ኛ፤ እጓለ ስለ አውሮፓ ታሪክ፣ ዕውቀትና ሥልጣኔ ሲነግረን በጣም በዝርዝርና በጥልቀት ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ዕውቀትና ሥልጣኔ ሲናገር ግን ዝርዝሩ በጣም ይሳሳበታል፡፡ ይሄም ከሁለት ምክንያቶች በአንዱ ሊሆን ይችላል:: አንድም፣ እጓለ በባህላዊው ትምህርት ውስጥ ‹‹የዕውቀት ባህር›› የሚባሉትን ቅኔ ቤትንና መፃህፍት ቤትን አለመዝለቁ (እጓለ፤ ዜማ ቤት እያለ ነበር በስኮላርሺፕ ወደ አውሮፓ የሄደው)፤ ወይም ደግሞ በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ያን ያህል በሥርዓት የተሰነደ ዕውቀት የለንም ማለት ነው፡፡
እነዚህ አምስት ሒሳዊ አስተያየቶች የሚያመላክቱት፣ ያሬዳዊውን ሥልጣኔ በተመለከተ የእጓለ ድምዳሜ፣ ከምሁራዊ ታማኝነት (Intellectual Integrity) ይልቅ ሀገራዊ ወገንተኝነት እንደሚጫነው ነው፡፡
በክፍል-4 ፅሁፌ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› እንደ መፍትሔ የቀረበበት ወቅት ትክክለኛ ነበር ወይ? ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ውስጥ የሚዋኻዱት ምንና ምንድን ናቸው? ሐሳቡስ ፖለቲካዊ ወይስ ፍልስፍናዊ መፍትሔ ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ እናፈላልጋለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 848 times