Sunday, 16 June 2019 00:00

የባህል ፌስቲቫል፣ የፋሽን ትርኢት፣ ነፃ የትምህርት ዕድል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  እርቅ ወንድማማችነትና አብሮነት የተከበረበት ሳምንት
                         
                  56 ብሔር ብሔረሰቦች፣ 56 ዓይነት ውበት፣ ባህልና ድምቀት የሚንፀባረቅበት ነው፤ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል፡፡ ይህንን ደማቅ ውበት ባህልና አብሮነት ባንድ ቦታ ለማሳየት የተዘጋጀው የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች የባህል ፌስቲቫልም፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ በሊጋባ በየነ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የተንጣለለ ግቢ ውስጥ ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ረፋድ ላይ በድምቀት ተጀመረ፡፡
የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ፌስቲቫሉን በክብር እንግድነት  የከፈቱት ሲሆን   የደቡብ ክልል ም/ቤት ዋና አፈጉባኤ ሄለን ደበበ፣ የደቡብ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰብለፀጋ አየለና ሌሎችም የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በበዓሉ ላይ  ታድመዋል፡፡ የወላይታ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ “ሀሹ ሰረዎታ” (እንኳን ደህና መጣችሁ) በሚለው የወላይትኛ ቋንቋ ነበር ሰላምታ ያቀረቡት፡፡
ከዚያም ብሔር ብሔረሰቦቹ በየቅደም ተከተላቸው በባህላዊ አለባበስ፣ ባህላዊ ጭፈራቸውን እያሳዩ በእንግዶች ፊት በማለፍ፣ ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች ታዳሚዎች አብረዋቸው እንዲጨፍሩ አስነስተዋቸዋል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦቹ ቅዳሜ ግንቦት 24 በዚህ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ በባህላዊ አልባሳት ጌጣጌጥ፣ ምግብ፣ የቤት ውስጥ መገልገያ መሳሪያዎችን ሲያስጎበኙና ሲሸጡ ውለዋል፡፡ በነጋታው እሁድም  ትርኢቱ ቀጥሎ ውሏል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦቹ ባህላዊ የእርቅና የግጭት አፈታታቸውን፣ የጋብቻ፣ የግርዛት፣ የሥራ ባህልና አጠቃላይ አኗኗራቸውን የሚያሳይ ትርኢት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ እንስሳት ከእንስሳት አብረው ተስማምተው እየኖሩ፣ እንዴት ማሰብ የምንችል እኛ ሰዎች በረባ ባልረባው እንጋጫለን፣ ወንድም ወንድሙን እንዴት ይገድላል፣ በሰለጠነ ጊዜ እንዴት በብሔር ፅንፍ እንይዛለን የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችን  በድራማ መልክ አቅርበዋል፡፡
እኛ የተለያየ ባህል ብንከተልም የተለያየ ቋንቋ ብንናገርም፣ በኢትዮጵያዊነታችን አንደራደርም የሚል አቋምም አንፀባርቀዋል፡፡ የየብሔር ብሔረሰቦቹ የዳኝነት፣ የግጭት አፈታትና የእርቅ ሥርዓት ሊበረታታና ሊታገዝ ከቻለ ከዘመናዊው የዳኝነት፣ የግጭት አፈታትና የእርቅ ሥርዓት እኩል  የአገርን ችግር ሊፈታ እንደሚችል በባለሙያዎች አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው፤ ይህ ፌስቲቫል ከነሙሉ ክብሩ ተጠብቆ በየጊዜው እየቀረበ የቱሪስት መስህብ መሆን እንዲችል የሚመለከተው በሙሉ በጉዳዩ ላይ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
የፋሽን ትርኢት - በጉተራ አዳራሽ
በዚሁ ዕለት አመሻሹ ላይ ሁሉም በሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ ከትቷል፡፡ የሶዶ ከተማ ተወላጇና ኑሮዋን በጣሊያን አገር ያደረገችው ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ ባዘጋጀችው ሁለት መሰናዶዎች ላይ ነበር እንግዶች የታደሙት:: የመድረኩ አጋፋሪዎች ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገንና የፋናዋ ጋዜጠኛ የሸዋ ማስረሻ ነበሩ፡፡ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በተጨማሪ በርካታ የጣሊያን ጋዜጠኞችና  እንግዶች ታድመው ነበር፡፡
“ዋን ፒስ ፋሽን” በተባለው ድርጅቷና በወላይታ ዞን ትብብር የተዘጋጀ የወላይታን የባህል ልብስ በጣም አስደናቂ በሆነ መልኩ የሚያሳይ የፋሽን ትርኢት ነበር አንዱ ሞዴልና ዲዛይነሯ ያዘጋጀችው መሰናዶ፡፡ በዚህ የፋሽን ትርኢት በርካታ ከአዲስ አበባ የተጋበዙ ዲዛይነሮች፤ የወላይታን ባህል ልብስ በሴትና ወንድ ሞዴሎቻቸው አማካኝነት ለእይታ አቅርበው ተመልካቹን አስደምመዋል፡፡ የወላይታን በሽመና የተሰራ ልብስ ለበጋ ለክረምት፣ ለሽርሽር፣ ለሰርግ፣ ለቦርሳና ለጫማ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የታየበትና የዲዛይነሮች ድንቅ ብቃት የወጣበት ምሽት ነበር፡፡ ይህንን ትርኢት ያዘጋጀችው ሰናይት ማሪዮና አልባሳቱን ዲዛይን ያደረጉት ባለሙያዎች አድናቆትና ሙገሳ ተችሯቸዋል፡፡
የሁለት ከተሞች እህትማማችነት
ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ ምንም እንኳን መኖሪያዋን በጣሊያን ሮም ከተማ ያደረገች ቢሆንም እትብቷ የተቀበረባት የወላይታ ጉዳይ ሁሌም እንደሚያሳስባት ትናገራለች፡፡ ከማሰብ ባለፈ ለከተማዋ የበኩሏን በማድረግ ለማሳደግና ለማዘመን ደፋ ቀና እንደምትልም የምታደርጋቸው ጥረቶች ይመሰክራሉ፡፡  አንዱ ማሳያዋ ሶዶን ከጣሊያኗ ማቻራኖ ጋር እህትማማች ከተሞች የማድረግ ስምምነት መፈጸም ነው፡፡ በልምድ ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂ፣ በትምህርትና መሰል ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ከተሞች በጋራ እንዲሰሩ  ስትጥር ቆይታ በዚሁ እለት ህልሟን እውን አድርጋለች፡፡ በመጀመሪያ ሁለቱ ከተሞች እህትማማች ለመሆን ምን የሚያመሳስላቸው ጉዳይ አለ የሚለው  ጥናት ተደርጎበታል፡፡ የጣሊያኗ ማቻራኖ ከተማ በውሃ የተከበበች፣ በተራራ ስር የተመሰረተች ስትሆን፣ ወላይታም ከዳሞታ ተራራ ስር መመስረቷ፣ ከአባያ ሀይቅ መዋሰኗ እንዲሁም የአየር ንብረቷና የተመሰረተችበት እድሜ በእጅጉ ያመሳስላታል ተብሏል፤ በጥናት አቅራቢዎቹ፡፡
 የወላይታ ከተማ ከንቲባ፣ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና ሌሎችም ከሶዶ ከተማ ሲገኙ፤ የማቻራኖ ከተማ ከንቲባ ተወካይ፣ በርካታ የጣሊያን ጋዜጠኞችና የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከጣሊያን ወገን ተገኝተው በቀጣይ እንደ እህትማማች ከተማነታቸው፣ ሁለቱንም ከተሞች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የትምህርት፣ ጤና፣ ቴክኖሎጂ፣ የባህልና የልማት ሥራዎችን ለማከናወን  ስምምነቱ በሁለቱ ከተሞች ተወካዮች መካከል ተፈርሟል፡፡ ከስምምነቱ በኋላም በሁለቱም ወገኖች በኩል ከተሞቻቸውን ይወክላሉ ያሏቸውን ስጦታዎች ተለዋውጠዋል፡፡ የማቻራኖ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የስራ ባልደረቦቸው ሶዶን እንደጎበኙ ሁሉ፣ የሶዶ ከተማ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ማቻራኖን እንዲጎበኙ ተጋብዘዋል፡፡  
ነፃ የትምህርት ዕድል ግብዣ
በዚሁ ዕለት በዚያው አዳራሽ በክብር እንግድነት ከተጋበዙት መካከል  ዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ይገኝበታል፡፡ ካሙዙ ወላይታን ከማስተዋወቅ አኳያ በወላይታ ዙሪያ የሰራቸው ሙዚቃዎች ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደነበረ በዞኑና በሶዶ ከተማ የስራ ኃላፊዎች ተገልፆ፣ አክብሮትና ምስጋና ተችሮታል፡፡ በምስጋና ብቻ አላበቃም፡፡ ካሙዙ ጣሊያን ሄዶ የሙዚቃ ትምህርቱን እንዲማር ነፃ የትምህርት እድል ተመቻችቶለታል፡፡ የአዳራሹ ታዳሚዎች አርቲስቱ ለተሰጠው የትምህርት ዕድል፣ ደስታቸውን በጭብጨባና በፉጨት ገልፀውለታል፡፡ በዚህም  መርሃ ግብሩ ተቋጭቷል፡፡   

Read 1063 times