Sunday, 16 June 2019 00:00

“ውለታ አይረሳም ያሳደጉት ውሻ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)


           “እኔ የምለው…ይሄ ዘላለሙን ‘አሻሮ’ ነገር ሆኖ የቀጠለ ቦተሊካችን፤ ‘ደግ የማያናግር፣ ደግ የማያሳስብ፣’ የሆነ ‘ጅኒ’ ነገር አለው እንዴ! እኛ ስለ ዛሬና ስለ ነገ እንዲወራልን፣ እንዲመከርልን ስንፈልግ፤ ዘላለም ትናንትን መጎተት ምንድነው!… ያውም እኮ ለበጎና ከተሞክሮ አዎንታዊ ትምህርት ለማግኘት ሳይሆን ያኛውን ግለሰብ ለማጣጣል ነው፡፡--”
          

                  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንዲት የድሮ ዘፈን አለች…
ከእንስሳ ጋር መኖር እኔ እመርጣለሁ
የብቻ ጓደኛ ውሻ አሳድጋለሁ፣
አሳዳጊው ቢሞት ይገባል ከዋሻ
ውለታ አይረሳም ያሳደጉት ውሻ
… ትላለች፡፡ ከአራትና አምስት አስርት ዓመታት በፊት የተዜመች ነች፡፡ እንደውም በአንጻራዊ መልኩ ማህበራዊ ሰንሰለቶች ጠንካራ ነበሩ በሚባልበት ዘመን ነው፡፡ እኔ የምለው… ይህን ሁሉ ዘመን ቆይቶ እንኳን ነገሮች ከመሻሻል ይልቅ ይብስባቸዋል!? “የብቻ ጓደኛ ውሻ አሳድጋለሁ” አሁንም ትርጉም ያላት ነች፡፡
ስሙኝማ… ምን አለ መሰላችሁ፣ ትናንትን መካድ፣ ትናንት በተራብን ጊዜ ፈትፍቶ፣ አጉርሶ ህይወታችንን ያቆየልንን እጅ ዛሬ መቀርጠፍ፣ ትናንት በታረዘ ገላችን ላይ ጨርቅ ጣል አድርጎ  ከቁር ያተረፈንን ዛሬ ከጨርቅ አሳንሶ ለማሳጣት መሞከር፣ ትናንት ለአጣዳፊ ችግራችን አጣዳፊ ምላሽ የሰጠንን ዛሬ… “ቡና ማሽን ውስጥ ከትህ ብትጨምቀው ሰባራ ሳንቲም ጠብ አይለውም…” አይነት ስም ማጠልሸት፡፡ ትናንት አፈር ፈጭተን፣ ውሀ ተራጭተን፣ ዓመታትን እንዳላሳለፍን፣ ዛሬ ሁሉንም ነገር መናድ፡፡  
“ስሚ፣ እኩዮች ናችሁ፣ አይደል!”
“ማንና ማን?”
“አንቺና እሷ ብዙም አትበላለጡም አሉ፡፡”
“አትበላለጡም! ስሚ፣ እሷ አርባ ኪሎ ጤፍ ተሸክማ አስፈጭታ ስትመለስ፣ እኔ እኮ ገና ሰኞ ማክሰኞ ነበር የምጫወተው፡፡”
እና፣ እንዲህ የተባለችው ሴት፤ ወይ ቀን ጥሏት እንኳን ለሰው ልትተርፍ ለራሷም መሆን አልቻለችም፤ ወይ ደግሞ ኢምፖርት/ኤክስፖርት ቢዝነስ ያለው አባወራ ‘ጠብ’ አላደረገችም፤ (ቂ..ቂ…ቂ…ሲባል ስለምንሰማ ነው፡፡ የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ቆንጆዎቹን፣’ ወይም ‘ቆንጆ’ የሚባሉትን ‘ገቢ’ ለማድረግ በቃ ስምንት ዲጂት የባንክ አካውንት ኮምፐልሰሪ ሆነ ማለት ነው! ድርቆሽ በውሀ!) እናማ…በአንጻራዊነት የተሻሉ የሚባሉ ዓመታት ታሳልፉና በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ችግር ጓዙን ጠቅልሎ  ሲመጣ፣ የጓደኝነት ብቻ ሳይሆን የአብሮ አደግነት ገመዶች ሁሉ ይበጣጠሳሉ፡፡
“እንዴት ነው እኔና እሱ አብሮ አደግ የምንሆነው! እኔ ስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ስፈተን፣ እሱ እኮ ‘ቆሞ ሊቀር ነው’ ተብሎ ሚስት ይፈለግለት ነበር፡፡” አያምጣው ነው አንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡
እናላችሁ… ከብዙ ሞራል ክስረታችን መሀል ይሄ ቀድሞ ወዳጅነትን መካድ፣ የትናንት እውነታዎችን መካድ የምር አሳፋሪ ነው፡፡ ይሄ ዘላለም የማይለቀን ‘ቀን የጣለው’ ላይ መረባረብ ሲብስበት እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡
“እንዴት እኔን የእሱ እኩያ ታደርገኛለህ!”
“ሲባል የሰማሁትን ነዋ! ምናልባት በሰባት ስምንት ወር ብትበላለጡ ነው ሲባል ነው የሰማሁት::”
“ምን! ስማ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲኒማ አዲስ ከተማ የገባሁ ጊዜ እኮ እሱ ነው እንኮኮ አድርጎኝ በሰዉ ላይ ያሳለፈኝ!”
አሳዳጊው ቢሞት ይገባል ከዋሻ
ውለታ አይረሳም ያሳደጉት ውሻ
ደግሞላችሁ… አለ አይደል…እሷዬዋ ወይ በገንዘብ፣ ወይ በዝና የተሳካላት ከሆነች ደግሞ ሌላ ታሪክ ይጻፋል፡፡
“ይገርምሻል፣ እንዴት አይነት ጓደኞች ነን መሰለሽ!” ይባላል፡፡
“አንቺና እሷ?”
“ምን ልበልሽ፣ አብረን የተሰፋን ይመስል ጠዋት ማታ አንለያይም ነበር፡፡ በቃ፣ መንታ እህትማማቾች በዪን፡፡”
“እኔ ደግሞ የሰማሁት ሌላ ነው...”
“የሰማሁት ሌላ ነው ማለት…”
“ከርቀት ሰላምታ ውጪ ይሄን ያህል ቅርበት የላቸውም ሲባል ነው፡፡”
“ይሄ የሀበሻ ምቀኛ የሚያወራው ነው፡፡ አንቺ የምታምኚው እኔን ነው እነሱን?!”
አዎ ‘ሲሳካላችሁ’፣ በሆነ ነገር ከፍ፣ ከፍ ስትሉ የሚያጎነብሰው፣ በሌለ ዝናብ ዣንጥላ የሚዘረጋው፣ የማስነጠስ ጫፍ እንኳን ሳይደረስ መሀረብ የሚያቀርበው፣ የተደናቀፈ ሰው በሌለበት “እኔን ይድፋኝ…” የሚለው…ምን አለፋችሁ ከያደፈጠበት ብቅ ይላል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ በአንድ ነገር ወይ በሌላ ባለጊዜ የሚባሉ ሰዎችን ጠጋ፣ ጠጋ ማለት  የሆነ ሱስ ነገር ነው እንዴ! የሆነ እሽቅድድም ነገር እየሆነ ነው እኮ! አሁንም ራስን ከባለሀብትና ከ‘አዳዲስ’ ባለስልጣናት ጋር  የማስተሳሰር ነገር እየጦፈ ነው ይባላል፡፡ የአሁኑን ደግሞ የበለጠ ቀሺም የሚያደርገው ‘ለመጠጋትም’ ሆነ ‘ለማስጠጋት’ የጎሳ ‘ክራይቴሪያ’ ስለተካተተበት ነው፡፡
እኔ የምለው…ይሄ ዘላለሙን ‘አሻሮ’ ነገር ሆኖ የቀጠለ ቦተሊካችን፤ ‘ደግ የማያናግር፣ ደግ የማያሳስብ፣’ የሆነ ‘ጅኒ’ ነገር አለው እንዴ! እኛ ስለ ዛሬና ስለ ነገ እንዲወራልን፣ እንዲመከርልን ስንፈልግ ዘላለም ትናንትን መጎተት ምንድነው!… ያውም እኮ ለበጎና ከተሞክሮ አዎንታዊ ትምህርት ለማግኘት ሳይሆን ያኛውን ግለሰብ  ለማጣጣል ነው፡፡
“ያኔም እኮ አቋም የሌለው ነበር…”፣ “እየዶለቱ ሊያፈርሱን ሲሞክሩ የነበሩት እነሱ አይደሉ እንዴ!” ምናምን ሲባባሉ ስንሰማና ስናይ ደስ አይልም፡፡ እኔ የምለው… አሁን የሚሉትን ያን ጊዜ  ያልነገሩን የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር! አሁን፣ የወጣቶቹን ቋንቋ ለመጠቀም… የምን “አጠቃቀስኩ” ነው!
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛ አገር ፖለቲከኞች አይገርሟችሁም! ማንኛቸውም እኮ በቀን ሁለቴ መብላት የህይወት ማቆያ መሆኑ ቀርቶ፣ ቀንቶት እየሆነበት ስላለው ህዝብ ምንም አይሉም:: ማንኛቸውም እኮ ሀኪም ቤት ሄዶ የመጨረሻዋን ተራ ምርመራ ለማድረግ፣ እንዴት አስቸጋሪ እየሆነብን እንደሆነ እየነገሩን አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ስለ ዛሬ ችግሮቻችንና መፍትሄዎቻቸውን እየነገሩን አይደለም፡፡ እናማ… ዛሬ የደላን ይመስል አሁንም “ትናንት፣ ትናንት፣ ትናንት…” እያሉ ማለቂያ የሌለው ኩነኔ ነገር ብቻ!
አሳዳጊው ቢሞት ይገባል ከዋሻ
ውለታ አይረሳም ያሳደጉት ውሻ
እሱዬው እንትናዬን እንደ ዓለም ዋንጫ እየከረመ እንደሚያደርገው፣ ምሳ ሊጋብዛት አሪፍ ሬስቱራንት ይዟት ይገባል፡፡ ሜኑው ይቀርባል፡፡ ልክ የአይንስታይንን የሆነ ንድፈ ሀሳብ እየመረመረች ይመስል አፍጣ ትቆያለች፡፡ እሱ ጣልቃ ይገባል…
“እዚህ ቤት ስቴካቸው አሪፍ ነው፣ ለምን እሱን አትበዪም!”
ግንባሯን ትቋጥራለች፡፡ “እኔ ስጋ ብዙም አይመቸኝም፡፡”
“ምነው… ስጋ ስትመገቢ ያምሻል እንዴ!”
“ማመም ሳይሆን ገና ልጅ እያለሁ እንኳን ስጋ ሲቀርብልኝ ደስ አይለኝም ነበር፡፡ ላዛኛ፣ ሰፓጌቲ ምናምን ነገር አድርጉልኝ ነበር የምለው፡፡”
ቆዪማ የእኔ ቆንጆ…ፖዝ! ፍሬን በጥሰሻል እንዴ! ምን መሰለሽ… በአምስተኛ ማርሽ ስታስነኪው ግራ ገብቶን ነው፡፡ የፍሬን ዘይት አልቆ ይሆን እንዴ! ወይስ መጀመሪያም ‘ፍሬን’ የሚባል ነገር የለም! ትምህርት ቤት ስትሄጂ ፊትሽ በራ ካለና ሳቅ፣ ሳቅ ካለሽ፣ ጓደኞችሽ “ዛሬ ቤታቸው ስጋ ተገዝቷል ማለት ነው” ይሉ አልነበረም እንዴ!
የትናንት ትርክቶችን ለመማማሪያ ሳይሆን ለመጠፋፊያ፣ ውለታን ለመመስከሪያ ሳይሆን ለማፍረሻ…አይነት መጠቀሙ ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋ እንኳን በከፍተኛ ደረጃ ካልቀነሰ መራመድ የሚቻለው በአንድ ዘዴ ብቻ ነው…‘በተአምር!’  
አሳዳጊው ቢሞት ይገባል ከዋሻ
ውለታ አይረሳም ያሳደጉት ውሻ
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 901 times