Sunday, 16 June 2019 00:00

“ኮብላይ ዘመን”- የተሾመ ብርሃኑ ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


የነፍሴ እርካቡ - የልቤ ኮርቻ፣
ባንቺ ልክ ተሰርቶ - ባንቺው መጠን ብቻ፣
ይኸው እንደ ቁምጣ - ልብ እንደማንገቻ፣
ላንዷ እየጠበበ - ላንዷም እየሰፋ፣
እንዳንቺ የሚሆን - ለልቤ ሰው ጠፋ!

አደባባዮቻችን በግጥም መጽሐፍት ገበያ ቢጥለቀለቁም፣ ወደ ሰው ልብ የሚደርስ ውበት አስዘግነው፣ የታሪክም ይሁን የሁነት ዘር በትነው የሚቆዩ እጅግ እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ እንደዚህ ሀገር ሁሉ ገጣሚ በሚሆንበት የታሪክ አጋጣሚ፣ እሳት ያላቸው ከያንያን በዐመድ ተራራ ተጋርደው እንዳይቀሩ፣ መቆስቆስ፣ እፍፍ ማለት ካልተቻለ፣ የአንድ ዘመን - ምልክትና ፈርጦች በዕድሜ ቋት ውስጥ ከስመው ይቀራሉ፡፡
ከወረቀት ባለፈ አዳራሾች ሁሉ በተደበላለቀ ስካር ውስጥ በስንኝ በሰከሩበት ጊዜ በፀጥታ ወርቃቸውን ኮልተው የተቀመጡ ሁሉ ጆሮ እያለፋቸው፣ ልብ እየራቃቸው መባከን ፈንታቸው ሊሆን ይችላል፡፡
ይሁንና እንደ አቅማችን፣ እንደ ንባባችን ልክ፣ ወደ ሰው በመድረሻችን መንገድ መጠን፣ ሰንደሎቹን እየመዘዝን መዓዛቸውን ማጥናት፣ ቀለማቸውን ማሳየት፣ ዜማቸውን መፈልቀቅ ግድ ይላል፡፡ በዚያው በየዓመቱ ስለምናያቸው ጌጦች ምስጋናና አለኝታነት፣ በዕውቀት የተመሠረተ ሙገሣም የጥበቡን ሁዳድ ውሃ እንደማጠጣት ይቆጠራል፡፡
አንዳንዴም የገጣሚያኑን ስንኞች በመጣጥፎች ውስጥ በመሰደር፣ እንዳይተኙ የተስፋቸው ፀዳል እንዳልከሰመ ማሳየት፣ የድንኳኖቻቸውን ካስማ እንደ ማጽናት ይቆጠራል፡፡
ጋዜጠኛ ተሾመ ብርሃኑ ያሳተማት “ኮብላይ ዘመን”ም ክብሪት ሆና የተጫረች ለሰስ ያለ ብርሃን ያላት፣ በተለይም በግጥም ሙዳይ ውስጥ ዋነኛ ግብ የሆነውን የነፍስ ፈንጠዝያ ፈጣሪ ሆና ስላገኘኋት ቀደም ሲል በገለጽኩት ዝንባሌ በጥቂቱ ላያት ወድጃለሁ፡፡
መጽሐፍዋ ዘጠና ስድስት ገፆች ያሏት ሲሆን፣ በሰዓሊ ቸርነት የቀለም ጠብታዎች ስሜት ያለው ሽፋን ለብሳለች፡፡ ሰማያዊ ቀለሟ፣ በረድ ያለ መደብ ሆኖ፤ ቢጫ፣ ቀይ፣ ጥቁር ቀለም ተቀይጠው በዥንጉርጉሩ ይደንሱባታል፡፡ ከዚያም የሙዚቃው ድምጽ እየገፈተረ ወደ ሃሳቦቹ ያደርሰናል፡፡
በጭብጥ አንፃር የፍቅር ዘንፋላ ዜማዎች አሳዛኝ ትርዒቶች፣ አስቂኝ ገጠመኞች፣ የፀፀት እንጉርጉሮዎች ታስደምጣለች፡፡ በፍቅር ዝርያዎች፣ ኢሮስ አንዳንዴ ከአጋፔ፣ ሌላ ጊዜ ከኢፒቱሚያ ጋር ሆነው ከበሮ ይደልቃሉ፡፡ የታጀቡትም በእንባ፣ ወይም በሣቅ ርችት ነው፡፡ በጥቅሉ ግን መጽሐፉ የፍቅርን ቁመና ወደ ማማ ያወጣ፣ የቃልኪዳንን ባንዲራ ሰማይ ያሳሰመ ነው፡፡ የሸቀጡን ዘመን ፍቅር በኪዳን ፈርጥ ለብጦ፣ የብርሃን ቀንዶችን ሰክቶለታል፡፡ ፍቅር ቀዳዴም ከፍ ከፍ አለ” ብሎ እንደ ሣሙኤል እናቷ ሆና ቢዘምርላት አይበዛበትም! ግና ሁሉም ነገር በአጭሩ፣ እንደጣፈጠ፣ በግጥሙ ምት ብርሃን እንደደመቀ ነው:: ብዙ ጠልቆ መፈላሰፍ ስላልቃጣው፣ ከየግድግዳው በመጋጨት፣ በሚያፈስሰው ደምና ላባ ወደ መሰቀቅ አያደርሰንም!
መጽሐፉ ፖለቲካውን፣ ማኅበራዊውን፣ ባህላዊውን የህይወት ቅርንጫፍ እየወዘወዘ የሚቀጥፍልን ፍሬም አለው፡፡
በቅርፁ በአብዛኛው ሌሪክ ስለሆነ፣ የትዝታ፣ የፍቅር፣ የናፍቆት ድምፆች ይሥረቀረቁበታል፣ ለዓመል ያህል የወዘታት፣ ሽለላና ቀረርቶም አላቸው::
በቁጭት ስለ ቀድሞ ታሪካችን የመዛዛትን አንድ የሃሳብ ዘንግ ይዤ አሀዱ ብል ደስ ይለኛል፤
“ለልጄ!” በሚለው ግጥም
እውነት…እውነት …እውነት
ነበርን እንዳላት፣
ለወቀረን ሁሉ የማንፈነከት፡፡
ነበርን እንደ ንብ
ያንዲት ጥግ ጥቃት እኩል የሚያስቆጣን፣
እንደ ሐዋርያቱ
የቃል  ኪዳኑን ወይን - ባንድ ዋንጫ የጠጣን፡፡
ነበርን ባይገርምሽ
እንደ ወንዝ አሸዋ - ታሪክ የተረፈን፣
ላጣ ምናበድር ተስፋ እየተረፈን፡፡
….
ዛሬ ቁልቁል ወርደን፣
ኩሬ አከልን እንጂ
ከዚህና ከዚያ እየተቆፈርን፣ እየተቋፈርን፣
ይገርምሻል ልጄ መሆንስ ነበርን!
አሳጥሬው የግጥሙ ሃሳብና መልክ ይህ ነው:: ስለ ትናንትና የዛሬዋ ኢትዮጵያ ፀፀት ያኘከው ልብ የሚተርከው ታሪክ ነው፡፡ እንባ የተቀባ ጊዜ ያሻከረው ድምጽ ነው፡፡ ለወቀረን የማንፈነከት አለት ነበርን! አንዱ ሲነካ ሌላው እንደ ንብ እየተመመ፣ ቀፎው የተነካበትን ያህል ቅሌን ጨርቄን ሳይል ይወጣል እያለ ነው፡፡
ውቅያኖስ የሚያህል ልብ የነበረን፣ ታሪክ ሞልቶ የተረፈን፣ ዛሬ የኩሬ ያህል ወደ ጐጥ ወርደን እንደ ችቦ የታሠርነው ቀርቶ፣ ለየብቻ የቆምን ጭራሮዎች መሆናችንን እየነገራት ነው፡፡ ዛሬ ያለ ትናንት የለምና በልቡ ዐድዋን እያሰበ፣ ማይጨውን እየመዘነ ይመስለኛል፡፡ ዘር ቆጠራ ሳይኖር ሰሜኑ፣ ደቡቡ፣ ምዕራቡ ምሥራቁ ግርር ብሎ የወጣበት ዐይነት!
“እንደ ወንዝ አሸዋ” በአነፃፃሪ ዘይቤ፣ የታሪካችንን ስፋትና ልክ የለሽነት እየተናገረ ነው፡፡ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ተስፋም ነበረን ይላል፡፡ ከፊት ሥልጣኔ፣ ወደፊት አንድነት ካለ ተስፋ የት ይጠፋል? እየወቀስን ነው፣ እያሳሰበን ነው፡፡ ይሁንና ቤት እየመታ ነው፤ በዜማ እሽሩሩ እያለ ነው፡፡ ቤት አመታቱ ከፍ ያለ ድምጽ ያላቸው አናባቢዎች ጧ! እያሉ ባያስደነግጡንም ሃሳቡ አሸንፎት ወጥቷልና አልቀዘዘም፡፡
ሌላዋ የፍልስፍና መዐዛ ያላት ሸንቋጭ ግጥም ገጽ 31 ላይ ያለችው “ከእግዜር በታች” የሚል ርዕስ የተሰጣት ናት፡፡ አንድ አንጓ ወርጄ እንዲህ እጀምረዋለሁ
ባቢሎን ተረት ነው ካፈረስነው ቆየ፣
ቋንቋችንን ወስዶ እግዜር ግን ዘገየ፡፡
ባደልከን ልሳን ልክ - ተክለን ተክለን ድንበር፣
አንተ ምድር አለህ - እኛ ግን እልፍ አገር
ዘመን እንደ ዶሮ - እሳት እየጫረ፣
ያኔ ያልከው ዛሬ - ሲነድ እያደረ፣
በፈርዖን ሲሆን - ውሎ አዳር ሚለካው፣
ሙሴስ አንዴ ጠፍቷል - ቀይ ባህር ምን ነካው?
ሳይቸግረን ቃልህ - ትዕዛዝህ ሳይጠፋን፣
ከበደሉ በላይ - ዝምታህ አስከፋን፡፡
በዝምታ አይነፃም - እድፍና በደል፣
ወይ አቤልን አንሳ - ወይ ቃየልን ግደል!
ይህ ግጥም በጠቃሽ ዘይቤ (Allusion) የሰከረ ነው፡፡ በተለይ “መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ” ዘይቤን ይዞ፣ ትልልቅ የታሪክ አንጓዎችን ረግጧል፡፡ እነዚህ አንዱ የባቢሎንን ግንብ የገነቡ የሰው ልጆች ታሪክ ሲሆን፣ ሌላኛው የሙሴ ዘመኑ ፈርዖንና የቀይ ባህርና ሙሴ ፍጥጫ ነው፡፡ የግጥሙ ማሳረጊያም የሁለት ወንድማማች በቅንዓት መገዳደል ነው፡፡ ሦስቱም የየራሳቸው ሰፊ ዝርዝር ቢኖራቸውም፣ ሁሉም ግን የሙሴ መጻሕፍት ከሆኑት አምስቱ፣ በሁለቱ የተፃፉ ናቸው -  በዘፍጥረትና በዘፀዐት!
ዞሮ ዞሮ ጥያቄ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ነገር መፍተል፣ ሃሳብ መቅደድ፣ መጠየቅ ነው? ፔሪኔ እንደሚሉት፤ “Beauty and Philosophical truth are aspects of experience, and the poor is often engaged with them”  መሆኑ ነው፡፡ ገጣሚ - ሲገጥም ውበት ያሳድዳል፣ ሲኖር በህይወት ገጠመኙ - በሚገጥሙት ሰናይና እኩዮች ይተይተነሳል፣ ነገር ይፈለቅቃል ያሰላስላል፣ ይጠይቃል!
ቋንቋችን ባይደባለቅ፣ ድንበር አናበጅም፣ ድንበር ባናበጅ አንፋጅም! ቀይ ባህርን በሰውኛ ባህሪ ማውራቱም አሽሙር ነው፡፡ ቀይ ባህር ምን አገባው? መፍሰስ ነው፡፡ ቁም ሲባል ቆሞ፣ እሥራኤልን አሻገረ፣ የፈርዖንን ሠረገላዎች ሥራው ክደናቸው ሲባል ከደነ፤ በቃ ታሪኩ አሻሚ ነው፡፡ ከባህሩ መከፈል በፊት የሚመስል ነገር አለው፡፡ ዝምታህ አስከፋን የሚለውም የተመረጠው የፈርዖን ሠራዊት፣ ከቀይ ባህር ጋር የተስማሙ በመሠለበት አጣብቂኝ ይመስላል፡፡ ገፀሰቡ (Personal) ግን እዚያ ብቻ አልቆመም! የአቤል ሞት ቁጭት ያንገበገበው ይመስላል፡፡ ቢቻል አቤል ከሞት እንዲነሳ፣ ካልሆነ ያ ነፍሰ ገዳይ የሞትን ጽዋ እንዲጨልጥ ይሞግታል! የእግዜር ጆሮ አይስማ አንል ነገር!
ቅድም ከልጁ ጋር ያወራው ገጸስብ እዚህ ከአያቱ ጋር እንደሚያወራ እንውሰደው “እኔና አያቴ” ይላል ግጥሙ፡፡
እኔ ያመት ጮራ - እኔ የዕድሜ ለጋ፣
እሱ ያመት ዲታ - የዕድሜ ባለፀጋ፡፡
ጊዜዬ
እንደ እንቡጥ አበባ - ደረቴን ወጥሮት
ጊዜው
እንደ ቆላ ምርኩዝ - አንገቱን ከዝሮት
ጉንጩን እየሳመ - ጺሙ እየሻከረኝ
ህልመኛው አያቴ - እንደዚህ መከረኝ፣
ልጄ ሆይ!
ስለመኖር ብለህ - ስለ ተስፋ ዋጋ፣
ከተኩላ ተላመድ - ከእሾህም ተጠጋ፣
ግና የኔ አበባ - ልጄ የኔ ፀጋ፣
ቆርቁሮህ አትኑር - ጫማ፣ ትዳር፣ አልጋ!
አያቱ ሦስተኛው የህይወት አንጓ ላይ ናቸው:: ልጁ ገና ዕምቡጥ ዕድሜ ላይ ነው፡፡ ታዲያ በህይወታቸው፣ ዋና ዋና ያሏቸውን ነገሮች በግጥሙ ላይ ዘራቸውን በትነዋል፣ በልቡ ትበቅል ዘንድ! ጫማ ቀን ሙሉ ይዋልበታል፤ ትዳር ለዝንታለም ይኖርበታል፤ አልጋም ሁልጊዜ ይታረፍበታል፡፡ ጫማው የቆረቆረው፣ ትዳሩ ያልቀናለት፣ እንቅልፍ ያጣ ሰው፣ መቸም አይሠምርለት እያሉ ነው!
ሲቪል አስበርን የተባሉ ፀሐፊ፤  “ከጫጉላ ቤት በኋላ” በሚል ርዕስ ሲጽፉ፤ “ፍቅር ማለት በልጅነትህ እንደምታስበው አይደለም” ያሉት ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ውበት ሆኖ አይቀጥልም! እሾሆቹ ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ ስለዚህም ፀሐፊው “It is much much more, and far more complex` ይሉታል፡፡ ከዚያ በጣም እጅግ በጣም ሩቅ፣ ውስብስብም ነው!
ከተኩላ መላመድ፣ ከሾህም መጠጋት ጣጣ የለውም፡፡ ሁሉም ይለመዳል፡፡ ሸፋፋ ትዳር፣ አይግጠምህ እያሉ ነው፡፡ ግን እንዲያም ሆኖ ጫማውን ትጥለዋለህ፣ አልጋውን ትቀይረዋለህ ያኛው ግን አይጣል ነው፡፡
ጋዜጠኛና ገጣሚ ተሾመ ብርሃኑ፤ የዚህ ዐይነት ብዙ ግጥሞች፣ ብዙ ሃሳቦች ይዞልን መጥቷል:: ፍቅርም ባገኙበት የሚወድቅ ልብ ሳይሆን፣ እየመረጠ የሚቀበል እንደሆነ በአጭር ግጥሙ አስቀምጦልናል፡-
“ላንቺ ብቻ!”
የነፍሴ እርካቡ - የልቤ ኮርቻ፣
ባንቺ ልክ ተሰርቶ - ባንቺው መጠን ብቻ፣
ይኸው እንደ ቁምጣ - ልብ እንደማንገቻ፣
ላንዷ እየጠበበ - ላንዷም እየሰፋ፣
እንዳንቺ የሚሆን - ለልቤ ሰው ጠፋ!
“ኮብላይ ዘመን” የምሠላ ልዕቀቱ ከፍ ያለ ባይሆንም፣ በማያንገጫግጭ ዜማ፣ በተከረከመ አሰነኛኘት የተሞላ ስለሆነ እንደምንም የሚንቆረቆር ነው፡፡ ሃሳቦቹ ጥምዝምዝና ቁመናቸው የዘለጋ ባለመሆኑ፣ በአንድ ትንፋሽ፣ የሚጣጣሙ ናቸው፡፡
አልፎ - አልፎ ቤት መምቻ ላይ ያሉት አናባቢዎች፤ ድምፀ ደካማ መሆናቸውና የመካነ - ድምፆች ምርጫ ላይ የሚታዩ ድክመቶች ቢኖሩም፣ ጥሩ ግጥሞች የተካተቱበት በመሆኑ አንባቢን ፈንጠዝያ ጋባዥ ናቸው፡፡ `
                                   

Read 2474 times