Sunday, 16 June 2019 00:00

እውነትም ነብይ በአገሩ ይከበራል!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)


              ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ታላቁን ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን የሚዘክር የኪነጥበብ ምሽት “ነብይ በሀገሩ እንዲህ ይከበራል” በሚል መሪ ቃል፤በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ  በድምቀት ተካሂዷል፡፡  
መጀመርያ ሀሳቡን ያመነጩት ጦቢያ ግጥም በጃዝ ላይ የሚሳተፉት ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱና እውቁ ዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም ሲሆኑ በኋላ ግን ሀሳቡን የሰሙት ሁሉ በፕሮግራሙ ላይ ግጥም ለማቅረብ፣ ሙዚቃ ለመጫወት፣ ስዕል ለመሳል፣ ምስክርነት ለመስጠት ፍላጎትና ተነሳሽነት በማሳየታቸው ሳይታሰብ የደመቀና የተዋጣለት ዝግጅት ሊሆን በቅቷል ይላሉ -የፕሮግራሙ አዘጋጆች፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዝግጅቱ ላይ  ባደረጉት ንግግር፤ “ለነቢይ መኮንን ይህ ዝግጅት መደረጉ እጅግ አስደስቶኛል፤ተገቢም ነው፤ ነቢይ መኮንን ከታላቅ ገጣሚነቱና ተርጓሚነቱ ባሻገር የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ አዲስ አድማስ ጋዜጣን በጉጉት እንድንጠብቅ ከሚያደርጉን ነገሮች መካከል የእሱ ርእሰ አንቀፅ አንዱ ነበር” ሲሉ አድናቆታቸውን  ገልፀዋል፡፡
ደራሲ እንዳለጌታ መኮንን ዝግጅቱን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት፤ነቢይን ለማክበርና ዕውቅና ለመስጠት ሃሳቡን ያመነጩትና እውን ያደረጉት ሰዎች ምስጋናና አድናቆት ይገባቸዋል ብሏል፡፡ “ነቢይ ገጣሚ ብቻ አይደለም፤ እንደ ዋርካ ከስሩ የሚጠለሉ ብዙዎችን አፍርቷል፤ የሱን ፅሁፍ አንብበው የተማሩ ብቻ ሳይሆን አብረውት ለመቆም እድል ስለገጠማቸው ብቻ ደስ የሚላቸው ብዙዎች ናቸው” ያለው እንዳለጌታ፤ “ሰው በህይወት እያለ ለሰራው ሥራ የምስጋናና የአክብሮት ፕሮግራም ሲዘጋጅለት በጣም ደስ ይላል፡፡” ብሏል፡፡
ለአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ በህይወት ሳለ፣ የውዳሴና የምስጋና ፕሮግራም ተዘጋጅቶ በነበረበት ወቅት  ሀበሾች ጀግኖቻችንን በህይወት ሳሉ የማክበር ባህል ስለሌለን የተገረመው ነቢይ መኮንን፤ ወዲያው ብዕሩን መዥረጥ አድርጎ “ሀበሻን ምን ነካው?” የሚል ግጥም ፅፎ ነበር ሲል ያስታወሰው ወዳጁ በኃይሉ ገ/መድህን፤ በዚህ ለእሱ በተዘጋጀው ምሽት ደግሞ፤ “ሀበሻን ምን ነካው? ቁ 2” እንደሚፅፍ እርግጠኛ ነኝ” ብሏል - ለታዳሚው፡፡
በክብር ምሽቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ “ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ገጣሚ ነቢይ መኮንን በጣም ትልቅና የተከበረ ሰው ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ሰው፣ በስሩ ብዙ ከያንያንን ያፈራና ለአገሩና ለወገኑ ብዙ ስራ ያበረከተ ነውና፤ አገሪቱም ውለታን የማትረሳ በመሆኗ ዝም ብለን አንተወውም፤ የአንገቱ ማስገቢያ ቤት እንሰጠዋለን፤የህክምና ወጪውንም መስተዳድሩ ይሸፍናል” ሲሉ ቃል የገቡ ሲሆን በዚህም ታዳሚው በደስታና በአድናቆት ተሞልቶ ነበር፡፡
በመድረኩ ላይ ስለ ነቢይ ሰብዕናና የጥበብ ህይወት የሚያውቀውንና ገጠመኞቹን የተናገረው ወዳጁ  አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ፤ የሰሩ ሰዎችን ማክበርና መሸለም መለመድና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መክሯል፡፡
“እኛም በህይወት እያሉ ሰዎችን ለማክበር ከዚህ በፊት ሞክረን ነበር፤ ግጥም በማንበብ፣ የግጥም ፕሮግራሙን በተለያዩ ባለሙያዎች እየሰየምን እናዘጋጅ ነበር፡፡ ነቢይም ነበረበት፤ ነገር ግን አልቀጠልንበትም፤ የቀጠለውም የለም፤ ቢለመድና ባህልም ሆኖ ሁሌ የሰሩ ሰዎች ቢታወሱ፣ ቢከበሩ በጣም ደስ ይላል፤ ሌላውንም ያነሳሳል” በማለት አርቲስት ተፈሪ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
በሳንፎርድ ትምህርት ቤት መምህርት የሆነችው የጥበብ ወዳጇ አስቴር አድማሱ፣ በዚህ የደመቀ ምሽት ላይ ከታደሙት አንዷ ነበረች፡፡ ስለ ዝግጅቱ በሰጠችውም አስተያየት እንዲህ ብላለች፡-
 “ነቢይ መኮንን የአዲስ አድማስ መስራችና ነፍሱን ይማረውና ከታላቁ አሰፋ ጎሳዬ ጋር ሌት ተቀን በመልፋት የጋዜጣውን ስም ከተከሉት መካከል አንዱ ነው፡፡ በጥበብ አበርክቶውም ቢሆን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፣ ለእኔ ቁጥር አንድ ገጣሚ ነው፤ እንደኔ እንደኔ ዝግጅቱም ሆነ ከም/ከንቲባው የተሰጠው ቤትና የሚሸፈንለት የህክምና ወጪ ካበረከተው ዘርፈ ብዙ ሥራ አንፃር ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም”  
“ሆኖም ነቢይ በህይወት እያለ መከበሩን፣ መወደዱን፣ በሰው ዘንድ ያለውን ቦታ እንዲያይና ደስ እንዲለው ይህን ፕሮግራም ያዘጋጁ እንዲሁም ቤት የሰጡትንና ህክምናውን ለመሸፈን ቃል የገቡትን ም/ከንቲባውንና ሌሎችንም ማመስገን ተገቢ ነው” ትላለች - አስቴር አድማሱ፡፡
ሌላው የሰዓሊው ሥራ ነው፡፡ ነቢይ መኮንን እንደ ገጣሚ፣ ፀሐፌ ተውኔትና ተርጓሚነቱ ምን አይነት ሰው ሊመስል ይችላል በሚል መነሻ እዚያው አዳራሽ ውስጥ ምስለ ገጹን የሳለ አንድ ታዋቂ ሰዓሊ፤ በስተመጨረሻ ስራውን ለእይታ በቅቷል፡፡
ምሽቱን በሙዚቃ ያደመቁት ዝነኞቹ የመሶብ ባህላዊ ባንድ አባላት፤ ገጣሚ ነቢይ መኮንን የሚወደውን የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን “የጠላሽ ይጠላ” እና የባንዱን የራሱን ሙዚቃ በመጫወት ታዳሚውን አዝናንተዋል::
ገጣሚያኑ ጌትነት እንየው፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ተስፋሁን ፀጋዬ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምስራቅ ተረፈ፣ መልዕቲ ኪሮስ፣ ደምሰው መርሻ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ አበባው መላኩና ረድኤት ተረፈ፤ የነቢይ መኮንንን ግጥሞች ለታዳሚው አንብበዋል፡፡
ወጣት ጣሰው ወንድም እንደሚለው፤ በአዳራሹ ፊት ለፊት ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩት እነ አበበ ባልቻ፣ በሀይሉ ገ/መድህንና ሌሎች በርካታ ታላላቅ  ሰዎች በፕሮግራሙ እጅግ መደሰታቸውን ከፊታቸው ላይ ማንበብ ይቻል  ነበር፡፡ በመቀጠልም በሰጠው አስተያየት፤ “ጀግኖቻችንን የማክበር ልምድ የለንም፤ እኛም እስቲ ለዚህ  ሰው ቀለል ያለ ያቅማችንን ፕሮግራም እናዘጋጅለት ብለን ነበር የጀመርነው፤ ግን ሀሳቡ ሲነሳ ሁሉም በደስታ አስተዋፅኦ ማድረግ ጀመረና ያማረ ሆነ፤ ጋሽ ነቢይም በእጅጉ ተደስቷል፤ባጠቃላይ ሁሉንም ያስደሰተ ምሽት ነበር፤ ይሄ ነገር መለመድ አለበት” ብሏል፡፡ በመጨረሻም ወጣቱ ለዝግጅቱ ምስጋናውን  አቅርቧል፤  
“በዝግጅቱ ላይ ደስ ብሏቸው አስተዋፅኦ ያደረጉትንም፣ ታዳሚውንም በተለይ ደግሞ ጤናው እንዲስተካከልና መኖሪያ ቤት ለመስጠት  ቃል የገቡትን ም/ከንቲባ ታከለ ኡማን እንዲሁም  ረ/ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬንና የነቢይ መኮንን የቅርብ ጓደኞቹን በሙሉ እናመሰግናለን፡፡”  

Read 724 times