Sunday, 16 June 2019 00:00

አይስላንድ ዘንድሮም የአለማችን እጅግ ሰላማዊ አገር ተብላለች

Written by 
Rate this item
(3 votes)


                 - ለ11 ተከታታይ አመታት በሰላማዊነት የሚስተካከላት አልተገኘም
                 - ኢትዮጵያ ከ163 የአለማችን አገራት 131ኛ ደረጃን ይዛለች


             ላለፉት 10 ተከታታይ አመታት በአለማቀፉ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት ውስጥ ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የዘለቀችው አይስላንድ፣ ዘንድሮም ክብሯን በማስጠበቅ የአለማችን የአመቱ እጅግ ሰላማዊ አገር በሚል ተመርጣለች፡፡
በአምናው የሰላም ደረጃ በ131ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘንድሮም ከፍም ዝቅም ሳትል በሪፖርቱ ከተካተቱት 163 የአለማችን አገራት መካከል አነስተኛ ሰላም ያላቸው ከሚለው ምድብ ውስጥ በ131ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል፡፡
ዜጎቿ ሰላማዊ ህይወትን የሚገፉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር በሚል አይስላንድን በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠውና ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው የ2019 አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት እንደሚለው፣ በአገሪቱ በአመቱ የተፈጸመው ወንጀል በሚገርም ሁኔታ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
ከአይስላንድ በመቀጠል በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት 163 የአለማችን አገራት መካከል በሰላም ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ኒውዚላንድ ስትሆን ፖርቹጋል በሶስተኛ፣ ኦስትሪያ በአራተኛነት ይከተላሉ ያለው ዝርዝሩ፤ አራቱ አገራት ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት፣ የአለማችን ምርጥ አራት ሰላማዊ አገራት ሆነው መዝለቃቸውንም አስታውሷል፡፡
ተቋሙ ለ13ኛ ጊዜ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት ውስጥ በሰላማዊነት የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችውና በአመቱ እጅግ በከፋ ሁኔታ ሰላም የራቃት የአለማችን አገር አፍጋኒስታን መሆኗንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሶርያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩስያ ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው በሰላም እጦት ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
አለማችን በእርስ በእርስ ግጭትና ብጥብጥ በየአመቱ 14 ትሪሊዮን ዶላር  ታጣለች ያለው ሪፖርቱ፣ በግጭትና በብጥብጥ ሳቢያ በአመቱ 28.9 ቢሊዮን ዶላር ያጣችው ሶርያ፣ ክፉኛ የተጎዳች የአለማችን ቀዳሚዋ አገር ናት ብሏል፡፡
የአለማችንን አገራት ማህበራዊ ደህንነት፣ ግጭትና ሌሎች ሁኔታዎች በመገምገም በየአመቱ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው ተቋሙ፣ በአመቱ የአለማችን አማካይ የሰላም ሁኔታ እጅግ በጥቂቱም ቢሆን መሻሻል እንዳሳየ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የ86 አገራት የሰላም ሁኔታ ቢሻሻልም 76 አገራት ደግሞ ሰላማቸው ከአምናው መቀነሱን አመልክቷል፡፡
የአለማችን ሰላም ባለፉት 11  አመታት በ3.78 በመቶ ያህል መቀነሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለዚህም ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል በሚል በምክንያትነት የጠቀሳቸው ሽብርተኝነትና የአገራት ውስጣዊ ግጭቶችን ነው፡፡
በሪፖርቱ ከተካተቱት አገራት መካከል 104 በሚሆኑት ውስጥ የሽብር ድርጊቶች ጭማሪ ማሳየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከግጭት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2017 በነበሩት ጊዜያት የ140 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጧል፡፡

Read 5888 times