Sunday, 16 June 2019 00:00

ከኔና አንቺ በፊት እነማን ነበሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  መዲናችን አዲስ አበባ ግዙፍ ከተማ ነች:: በአገራችን ካሉ ነባር የመንግስት መቀመጫ ከነበሩ ከተሞች ጋር ስትወዳደር ዕድሜዋ ረጅም አይባልም፡፡ 130 ዓመታት አካባቢ፣ እ.ኤ.አ በ1886 ተቆረቆረች ነው የሚባለው፡፡ በደቡብ ሕዝቦች ቤንች ማጂ፣ ከምትገኘው ከማጂ፣ በዕድሜ በጥቂት ዓመታት ነው የምትበልጠው:: የኦሮምያዋ ጅማ አሁን እንደምናውቃት አዌቱ አካባቢ ጣልያን መልሶ ያለማት ትሁን እንጂ ከአዲስ አበባ በጣም ቀድማ የተቆረቆረችና ለብዙ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ለወላይታ፣ ከምባታ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ የንግድ መናኸሪያ መተላለፊያ ነበረች፤ አሁንም ነች:: ጅማ ከአዲስ አበባ በዕድሜ የምትበልጥ ከተማ ነች፡፡ በምስራቅም ሐረር ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የከተማ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ የገነነች የንግድና ባህል መናኸሪያ ነበረች:: በሰሜን እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጐንደር መቼ አብበው፣ መቼ ገንነው፣ መቼ እንደደከሙ ብዙ አንባቢ ያውቃል፡፡ ነገር ግን እንደ ጅማ እና ሐረር፣ አዲግራት የመሳሰሉ የቆዩ ከተሞች፤ እንደ አዲስ አበባ ለምን አልገዘፉም? ለምን በአካባቢያቸው ላሉ የገጠር ነዋሪዎች የከተሜነት ተምሳሌት እየሆኑ፣ የኢትዮጵያን የከተሜነት እንቅስቃሴ ለምን አላፋጠኑም? የሚሉት ጥያቄዎች አንባቢያን ቢያነሱ፣ መልሱ እንዲህ በቀላሉ የሚሰነዘር አይደለም፡፡ የከተማ ልማትና የታሪክ ተመራማሪዎች፤ የኢትዮጵያ የከተሜነት የዳዴ ጉዞ፣ ከስር መሰረቱ ከነበረው በተስፋፊነት የተቃኘ ሂደት በመነሳት፣ የመደቦችና የሕዝቦች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ታሪክ ለዛሬውም የተዛባ የከተማ ምጣኔ መሰረት ነው የሚሉ አሉ፤ እኔም አንዱ ባይ ነኝ፡፡
“ከተማ” የሚለው የአማርኛ ቃል በመጀመሪያ “ከፍታ”፣ ቀስ እያለ ደግሞ “ከተማ” ማለት የተስፋፊው ኃይል መከማቻ ሰፈር (የጦር ካምፕ) ሆኖ መቆየቱን የዕውቀት መዛግብት ያስረዳሉ::” በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ወራሪውና ጭፍራዎቹ በኅብረተሰቡ ላይ “እንደ አንበጣ መንጋ” ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየሰፈሩበት፣ ያፈራውንና ያከማቸውን ሃብት፣ ከብቱን፣ ምንም ሳይቀር ጠራርገው እንደሚወስዱበት፣ ትዳርና ልጆቹን እንደሚደፍሩበት፣ ሲያልቅበትም ከዚህ ተነስተው ወደ ሌላ ያልተነካ ደንና ግብርና እንደሚያቀኑ ተጽፏል፤ መሰል ግፉ በመጻሕፍት ተተርኳል፡፡”
“ከተማ” ማለት በደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜም የቆየ ትርጉሙ ማጂ፣ ሀገረማርያም፣ ጅግጅጋ እንደዚህ ነው የተፈጠሩት፡፡ ንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ እ.ኤ.አ በ1932 በአፄ ምኒልክ እና በአባ ጅፋር መካከል ተደርጐ የነበረውን የቀድሞ ስምምነት አፍርሰው ጅማን ወደ አውራጃ፣ ያን የቆየ የኦሮሞ የገበያና የባህል መጋላ ወደ “ከተማ” ቀይረው ከጠቀለሉት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ፣ በያኔው አውራጃ (በዛሬው ዞን) የሚኖረው ሰው ቁጥር፤ ከአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር ጋር የሚቀራረብ መጠን ድረስ አድጓል፡፡ ነገር ግን ከጂማ ዞን ነዋሪ ውስጥ 120ሺ አካባቢ (5 በመቶ) ብቻ ናቸው በከተሜነት የሚኖሩት፡፡ የምዕተ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የራሷ መሪ የነበራት፣ ለምዕራብ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ንግድና ባህል መዳበር ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ የነበረችው ጅማ፤ በከተሜነት ለምን ከእህትዋ ከአዲስ አበባ ወደ ኋላ ቀረች?
(ሾተል፡ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፤
ፀደቀ ይሁኔ ወልዱ)

Read 2623 times