Print this page
Wednesday, 19 June 2019 09:16

ቃለ ምልልስ “ለሆስፒታሎች ድጋፍ ማሰባሰባችንን እንቀጥላለን”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


                       • በልመና የሚመጡ የህክምና ቁሳቁሶች ያለ ቀረጥ ቢገቡ መልካም ነበር
                       • ለጉንችሬ ሆስፒታል የ13.5 ሚ. ብር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

           የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘላለም ጭምዴሳ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከአሜሪካን ሀገር ያሰባሰቡትን 13.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች፣ በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ለሚገኘው የጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም  ለግሰዋል፡፡
በ2007 ከጤና ጣቢያነት ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያደገው የጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፤ በወር እስከ 3ሺ ህመምተኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን ለህክምና አስፈላጊ ከሆኑ ቁሳቁሶች ግማሽ ያህሉ እንኳ ያልተሟላለት መሆኑ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
35 የህሙማን አልጋዎች ያሉት ሆስፒታሉ፤ ስምንት ጠቅላላ ሃኪሞች፣ ሶስት አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ሃኪሞችና 26 ነርሶች እንዳሉት ተጠቁሟል:: ሆስፒታሉ ካለው ተገልጋይ አንፃር የሚሰጠው አገልግሎት በህክምና ቁሳቁሶች እጥረት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን የገለጹት የሆስፒታሉ አስተዳደሮች፤ ዶ/ር ዘላለምና አጋሮቻቸው ያበረከቱት ድጋፍ ለሆስፒታሉ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡  
የደም ማቆያ ባንክን ጨምሮ 20 ያህል አልጋዎች፣ ዊልቼሮችና ሌሎች በርከት ያሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለሆስፒታሉ ያበረከቱት ዶ/ር ዘላለም፤ ስለ እርዳታ አሰባሰቡና ስለ ወደፊት ዕቅዳቸው እንዲሁም ስለሚሰጡት  ነጻ የህክምና ድጋፍ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡  
          ሆስፒታሎችን በህክምና ቁሳቁስ የመደገፍ ሃሳብ እንዴት ተጀመረ?
በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ከተመረቅሁ በኋላ በሲዳማ ዞን ቦና ሆስፒታል ነበር የምሰራው:: ሆስፒታሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነበር፡፡ እዚያ ሆስፒታል ውስጥ ከፍተኛ የህክምና መሣሪያ እጥረት ነበር፡፡ በወቅቱ ለዚህ ሆስፒታል በኔ በኩል ምን ማድረግ ነው የምችለው የሚለውን ሳስብ፣ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ረጂ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመስራት ሃሳብ ነው የመጣልኝ፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ የአክስቴ ልጅ አሜሪካን ነው የምትኖረው፡፡ ከእሷ ጋር ተመካከርን:: በእርዳታ የተሰጠን አንድ ኮንቴነር የህክምና እቃ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ 24 ሺህ ዶላር ያስፈልጋል ተባልን:: እኛም ጓደኞቻችንን እርዳታ አድርጉልን እያልን በፌስ ቡክ እየለመንን፣ 120 የሚሆኑ ሰዎች ከ10 ዶላር እስከ 4ሺህ ዶላር ከረዱን በኋላ፣ ገንዘቡ ሲሞላልን  ከፍለን ለቦና ሆስፒታል አንድ ኮንቴነር የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች አስመጣን፤ ከአንድ አመት ከ6 ወር በፊት፡፡  
ያንን ካየንና በዚያ ከተበረታታን በኋላ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ማሰባሰብ እንዳለብን ወሰንን፡፡ ይሄን የጉንችሬ ሆስፒታል እንድናስብ ቅድሚያ ፋውንዴሽን ከተባለ የወዳጆቻችን ድርጅቶች ሃሳብ ቀረበልን፡፡ እኛም ሄደን ስናየው ሆስፒታሉ ትልቅ ችግር ያለበት መሆኑን ተረዳን፡፡ ወዲያው የመጀመሪያውን የቦና ሆስፒታል ድጋፍ ካደረገልንና አሜሪካ ከሚገኘው “ፕሮጀክት ኪዩር” ከተሰኘው ተቋም ጋር ተነጋገርን:: እሱም በድጋሚ ድጋፉን አደረገልን ማለት ነው፡፡ ቅድሚያ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፣ የማጓጓዣ ወጪ 24ሺህ ዶላሩን አሜሪካ ካሉ ወዳጆች አሰባስበው ከፍለው ነው ድጋፉ  የመጣው፡፡
ያሰባሰባችሁት የህክምና መሳሪያዎች  የዋጋ ግምት ምን ያህል ነው?
እስከ 450ሺህ ዶላር ወይም 13.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ እኛ ምንም ገንዘብ አላወጣንም:: ያደረግነው ነገር ያው በቅን ልቦና ተነሳስተን፣ ጊዜያችንን በመጠኑ ሰውተን፣ ለህብረተሰቡ የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የሞከርነው፡፡ ሃሳብ እንጂ ገንዘብ ያወጣነው የለም፡፡
ለወደፊት ምን እቅድ አላችሁ?
ከቅድሚያ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት አቶ አስቻለው ጋር በመሆን በአመት ሁለት ሆስፒታሎችን በዚህ መልኩ መደገፍ የሚል እቅድ ይዘናል፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ እቅድ መሠረት ለሆስፒታሎች ድጋፍ ማሰባሰባችንን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በተለይ ከአሜሪካ የሚመጡ እቃዎች ጥራታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የህክምና መሣሪያዎች የጥራት ችግር እየተባለ የሚነሳውን ችግር ይቀርፋል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ የድጋፍ ማሰባሰብ ፕሮጀክቶች፣ በሌሎች ሀገራት፣ በአብዛኛው በቀዳማዊ እመቤቶች የሚመራ ነው፡፡ ለምሣሌ በኬንያ ከፕሮጀክት ኪዩር ጋር እየተፃፃፈች፣ ገንዘቡን እየከፈለች የምታስመጣው የኡሁሩ ኬንያታ ባለቤት ነች፡፡ ስለዚህ እኛም እድሉን የምናገኝ ከሆነ ከቀዳማዊ እመቤት ጋር መስራት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም ፕሮፖዛል አዘጋጅቻለሁ፡፡
ከሙያ ድጋፍ አንፃርስ ምን እያከናወናችሁ ነው?
የሙያ ድጋፍ ከዚህ በፊትም አድርገናል፡፡ 16 እናቶችን በሁለት ቀናት ቀዶ ጥገና አድርገንላቸዋል:: ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ነበርን፡፡ አንድ ቡድን ከጓደኞቻችን ጋር አቋቁመን፣ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ነፃ የህክምና ድጋፎችን እናደርጋለን:: ለወደፊትም በጐ ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ጓደኞች አሉን፤ ቢያንስ 10 ያህል የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች አሉ፡፡ በየአካባቢው የነፃ ህክምና ዘመቻዎችን እናደርጋለን፡፡
የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ በማስመጣት ሂደት የገጠማችሁ ትልቁ ተግዳሮት ምንድን ነው?
አንዱ የጉምሩክ ጉዳይ ነው፡፡ የፍቃድና የጉምሩክ ክፍያ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ በልመና የሚመጡ የህክምና ቁሳቁሶችን በነፃ ቢያስገቡ መልካም ነበር፡፡ ለጉምሩክ ሂደት ብቻ ከ100ሺህ ብር በላይ ተከፍሏል:: ይህ ቢቀር የተሻለ ይሆን ነበር፡፡

Read 4557 times
Administrator

Latest from Administrator