Print this page
Monday, 24 June 2019 00:00

ኤርባስ ያለአብራሪ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን ሊያመርት ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አውሮፕላኖች ከአብራሪዎች ቁጥጥር ውጭ እየሆኑ በመከስከስ በርካታ መንገደኞችን ለህልፈተ ህይወት በሚዳርጉበትና የአቪየሽን ኢንዱስትሪ በደህንነት ስጋት ውስጥ በወደቀበት በዚህ አደገኛ ወቅት ላይ፣ ታዋቂው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኤርባስ፤ ያለአብራሪ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን ላመርት ነው ማለቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
ኤርባስ ኩባንያ ያለምንም አብራሪ በቴክኖሎጂ ብቻ እየታገዙ መንገደኞችን አሳፍረው የሚበርሩ አውሮፕላኖችን ለማምረት ማቀዱን የኩባንያው የንግድ ዘርፍ ሃላፊ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ብዙዎች ሃሳቡን ቢቃወሙትም ከሰሞኑ በአሜሪካ በ22 ሺህ ሰዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ግን 70 በመቶ ያህሉ አብራሪ በሌላቸው መሰል አውሮፕላኖች ለመጓዝ እንደሚመርጡ መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለማችን ያለአብራሪ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን የሚጠቀም የንግድ ተቋም እንደሌለ የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል አውሮፕላኖችን መንገደኞችን በመደበኛነት ለማጓጓዝ በጥቅም ላይ ማዋል በህግ እንዳልተፈቀደም ገልጧል፡፡ በተያያዘ ዜናም፣ ተፎካካሪው ቦይንግ ኩባንያ፤ በ737 ማክስ ኤይት  አውሮፕላኑ ሳቢያ ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ ኤርባስ ገቢው መጨመሩንና አዲስ ያመረተውን ኤ321ኤክስኤልአር የተባለ ግዙፍ አውሮፕላን በገፍ መሸጥ መጀመሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው 27 ያህል አውሮፕላኖችን ለተለያዩ ደንበኞች ለመሸጥ ትዕዛዝ መቀበሉንና ሽያጩ 15 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስገኝለት ባለፈው ሰኞ ዕለት በፓሪስ በተጀመረው አለማቀፍ የአየር መንገዶች ኤግዚቢሽን ላይ ይፋ ማድረጉን ያስታወሰው ዘገባው፣ 200 አውሮፕላኖችን ይሸጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

Read 2845 times
Administrator

Latest from Administrator