Wednesday, 26 June 2019 00:00

በህንድ የተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት 180 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               ካለፈው ሳምንት አንስቶ በህንድ ምስራቃዊ ግዛት አካባቢ የተከሰተውና እየተባባሰ የመጣው እጅግ ከፍተኛ ሙቀት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ 180 ሰዎችን ለሞት መዳረጉ ተዘግቧል፡፡
ባሂር በተባለችው የአገሪቱ ግዛት የተከሰተውና ከዚህ በፊት ታይቶ ለማይታወቅ የተራዘመ ጊዜ የቆየው 113 ዲግሪ ፋራናይት የሚደርስ ሃይለኛ ሙቀት፣ በርካታ ሰዎችን ለልብ ድካምና ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝና ሆስፒታሎች ራሳቸውን በሳቱ ሰዎች መጥለቅለቃቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በግዛቲቱ በሚገኙ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ከተወሰነ ሰዓት ውጪ ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ያለው ዘገባው፤ የውሃ እጥረት ችግሩን እያባባሰው እንደሚገኝና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ህንዳውያን ሙቀቱን በመሸሽ ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሰደድ ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
በመላ ህንድ ላለፉት 32 ተከታታይ ቀናት የሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱንና ባማካይ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ ከአራት አመታት በፊት በህንድና በፓኪስታን የተከሰተ ከፍተኛ ሙቀት በድምሩ ከ3 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ለሞት እንደዳረገም  አስታውሷል፡፡

Read 7319 times