Saturday, 22 June 2019 11:10

ምርጫው የማይካሄድ ከሆነ የመከላከያ ሠራዊት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ተገለፀ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በመጪው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በህገ መንግስቱ  በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የማይካሄድ ከሆነ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የትግራይ ክልል መስተዳድር፣ የህግ አማካሪ አቶ ዘርአይ ወ/ሰንበት ሰሞኑን ገለፁ፡፡
በህገመንግስቱ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 3፣ በአንቀጽ 58 እና 54 መሠረት፤ ምርጫ ባለማድረግ ህገመንግስቱ ከተጣሰ፣ የክልልና የፌደራል አስፈፃሚ አካላት ህገመንግስቱን አክብረው ምርጫውን ማካሄድ ካልቻሉና እንዲካሄድ የማያደርጉ ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 87 መሠረት፤ የመከላከያ ሠራዊቱ ሃይል ተጠቅሞ፣ ህገመንግስቱን የማስከበር ግዴታ እንዳለበት አቶ ዘርአይ አስገንዝበዋል፡፡
ህገመንግስት የሚጣሠው አስፈፃሚ አካላቶች ስልጣናቸውን ለማራዘም በማሰብ ነው ያሉት የህግ አማካሪው፤ ህዝባዊ መንግስት ነን እያሉ፣ ሠላምና መረጋጋትን አመጣለሁ በሚል ሰበብ  ከህገመንግስቱ ውጭ ምርጫ እንዳይካሄድ ዳር ዳር ማለት ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፤ “ምርጫው በጊዜው የማይካሄድ ከሆነ አገሪቱ የመፈራረስ አደጋ ይገጥማታል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

Read 13404 times