Saturday, 22 June 2019 11:10

ከምስራቅ አፍሪካ አገራት አገራቸውን ጥለው በመሰደድ ኢትዮጵያውያን ያመራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሃገራቸውን ጥለው በመሰደድ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ዋነኛ የስደት መዳረሻቸውም ሳውዲ አረቢያ መሆኗ ተገለፀ፡፡
የአለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በሚያዚያ ወር 2011 ብቻ ወደተለያዩ ሀገራት በህገወጥ መንገድ ከተሰደዱ የምስራቅ አፍሪካ ዜጐች መካከል ኢትዮጵያውያን 68 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ተጠቁሟል፡፡
በስደት በሁለተኛነት የተቀመጡት ሶማሊያውያን ሲሆኑ 27 በመቶ ድርሻ አላቸው ብሏል - ሪፖርቱ::  ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ የተለያዩ የስደት መስመሮችን የሚጠቀሙ ሲሆን አንዱና ዋነኛው በሆነው የጅቡቲ መስመር ከሚጓዙ ስደተኞች መካከል 84.3 በመቶ ያህሉ መዳረሻቸውን ሳውዲ አረቢያ ያደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡ ጅቡቲም ከምታስተናግዳቸው ስደተኞች ውስጥ  99.6 በመቶ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
ጅቡቲን መሸጋገሪያ አድርገው ከሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል 58.8 በመቶዎቹ ወንዶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 18.5 በመቶዎቹ ለወጣትነት እድሜ ያልደረሱ ታዳጊዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
96 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች፤ የስደታቸው ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን የጠቆመው አይ ኦ ኤም፤ 4 በመቶዎቹ “በግጭት ምክንያት ነው የምንሰደደው” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል ብሏል፡፡ ከእነዚህ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን 83 በመቶ የሚሆኑት በእግራቸው ለበርካታ ቀናት ተጉዘው ጅቡቲ እንደሚደርሱ፣ በመኪና የሚጓዙት 10 በመቶ ያህል ብቻ እንደሆኑም ተመልክተናል ብሏል - ተቋሙ በሪፖርቱ፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙት ሌላኛው የስደት መስመር በኤልዳሃር አድርጐ ሱዳን የሚደርሰው ሲሆን በዚህ መስመር ከሚጓጓዙ የምስራቅ አፍሪካ ዜጐች 82 በመቶ ድርሻ ኢትዮጵያውያን ሲወስዱ፤ 7 በመቶ ሶማሊያውያን፣ 4 በመቶ ደግሞ ኤርትራውያን ቀሪዎቹ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዜጐች እንደሆኑ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

Read 11029 times