Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 09 June 2012 06:28

የመንግስት ወከባ ከፍርሃት የማያላቅቅ የህልም ሩጫ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የያዙ ስራአጦች እየበዙ ነው። ቁጥራቸው በ5 አመት ውስጥ በ3 እጥፍ ጨምሯልየትራንስፎርሜሽን እቅዱ 2 አመት ሊሞላው ነው፤ ነገር ግን በርካታ እቅዶች ተያዘላቸው ጊዜ አልተሰሩምበየአመቱ የስራ ፈላጊ ከተሜዎች ቁጥር በ330ሺ ይጨምራል፤ ሩብ ያህሉ ብቻ መደበኛ የስራ እድል ያገኛሉየገጠር ህዝብ በየአመቱ በ2 ሚ. እየጨመረ ነው፤ የዝናብ እጥረት ሳይኖርም ከ12ሚ. በላይ ሰዎች ተረጂ ናቸውየሰኔ ወር፤ ሂሳብ የሚወራረድበት ወር አይደል? ቢሊዮን ብሮችን ለመደመርና ለመቀነስ የፈለግኩ መስሏችሁ አትደንግጡ። በወረቀት ላይ የተፃፉትን ግዙፍ እቅዶችና በተግባር የታዩትን ስራዎች እያነፃፀርን ሂሳብ ለማወራረድ ብንሞክር በቂ ነው - ለዚያው ጥቂቶቹን ብቻ። በመከረኛው ስኳር እንጀምር መሰለኝ።

ከሁለት አመት በፊት ሶስት ሚ. ኩንታል ገደማ የነበርው የስኳር ምርት፤ ዘንድሮ ወደ 7.3 ሚሊዮን ኩንታል እንዲደርስ ነበር የታቀደው (የእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅድ Growth and Transformation Plan, Policy Matrix ገፅ 9)። ነገር ግን፤ የአዳዲሶቹ ፋብሪካዎች ግንባታ ገና አልተጀመረም። የዛሬ አራት አመት፤ ግንባታቸው እንዲጠናቀቅና ስኳር እንዲያመርቱ እቅድ ተይዞላቸው የነበሩት የስኳር ፕሮጀክቶችም ገና ማምረት አልጀመሩም። እናም የስኳር ምርት፤ ከአምናውና ከአቻምናው በታች ሆኗል - ከ3 ሚ. ኩንታል በታች።

የሲሚንቶ ምርት ትንሽ ይሻላል። ነገር ግን የእቅዱን ያህል አልተሳካም። ከ27 ሚሊዮን ኩንታል በመነሳት ዘንድሮ 136 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ግማሽ ያህሉን ነው ሊያሳካ የቻለው።

በጥቃቅንና በአነስተኛ ተቋማት ብቻ በአመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የስራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ነበር(GTP, Policy Matrix ገፅ 11)። ይሄ ሁሉ የስራ እድል የሚፈጠረው በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በኩል ብቻ ነው። የሌሎች ዘርፎችና ተቋማት ሲጨመርበት የትናየት እንደሚደርስ አስቡት። ግን የትም አልደረሰም። የስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በሁሉም ዘርፎችና ተቋማት ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የስራ እድል በጣም አነስተኛ ነው። በየአመቱ በአማካይ መቶ ሺ የማይሞሉ መደበኛ (formal) የስራ እድሎች ብቻ ይፈጠራሉ።

ከአምስት አመት በፊት በሁሉም ከተሞች መደበኛ ሰራተኞች በአጠቃላይ 2.5 ሚሊዮን እንደነበሩ በ1998 አ.ም የተካሄደው የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት ይጠቁማል ... URBAN EMPLOYMENT UNEMPLOYMENT SURVEY (UEUS) July 2006። ከአምስት አመት በኋላስ? ከቅርብ ጊዜ መረጃዎች ጋር እናነፃፅረዋ። ባለፈው ነሐሴ ወር የወጣው የስታትስቲክስ ባለስልጣን አዲስ ጥናት እንደሚገልፀው፤ የመደበኛ ሰራተኞች ቁጥር ወደ 2.9 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል (UEUS, August 2011, Table 5.30 ገፅ 170)። በአምስት አመታት በሁሉም ከተሞችና በሁሉም ዘርፎች የተፈጠሩት መደበኛ የስራ እድሎች ከ400ሺ በታች ናቸው።

ከሁሉም በላይ የተሻለ ውጤት ተመዝግቦበታል በሚባለው በኤሌክትሪክ ማመንጫ ዘርፍ ሳይቀር፤ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች እስካሁን አልተሳኩም። እቅዱ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ፤ 2000 ሜጋዋት የነበረው የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ማመንጫ አቅም፤ ዘንድሮ ወደ 2600 ገደማ መድረስ ነበረበት (GTP, Policy Matrix ገፅ 14)። ። ግን እንደታቀደው አልሆነም። እዚያው የነበረበት ላይ ቆሟል።

ባለፉት ሁለት አመታት በአዲስ አበባ 60ሺ አዳዲስ የኮንዶምኒዬም ቤቶች፤ በእጣ ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ በእቅዱ ገፅ 17 ላይ ተጠቅሷል - አልተሳካም እንጂ። ከዚህ እቅድ ውስጥ ይሳካል ተብሎ የሚጠበቀው አንድ ሶስተኛው ብቻ ነው። የ20ሺ ኮንዶምኒዬም ቤቶች እጣ በቅርቡ እንደሚወጣ ተነግሮ የለ?

የኤክስፖርት እቅዶችም ግማሽ ያህል ነው የተሳኩት። ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በመነሳት ዘንድሮ ከ 4ቢ. ዶላር በላይ የኤክስፖርት ገቢ ይገኛል ተብሎ ቢታቀድም፤ እውን ሊሆን የሚችለው ወደ 3ቢ. ዶላር ገደማ ብቻ ነው። በተለይ የቡና ኤክስፖርት ንቅንቅ አላለም። ከሁለት አመት በፊት በቡና ኤክስፖርት 530 ቢ. ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህንን ገቢ ዘንድሮ ወደ 900 ዶላር ለማድረስ ነበር የታቀደው (GTP,PM ገፅ 6)። ግን፤ የዘንድሮ የቡና ኤክስፖርት ከካቻምናው ብዙም የሚራራቅ እንደማይሆን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሰነዱ ገፅ 16 ላይ የሰፈረው ሌላው ትልቁ እቅድ፤ የባቡር ሃዲስ ግንባታ ነው። አምናና ዘንድሮ 930 ኪ.ሜ የባቡር ሃዲድ ተዘርግቶ እንደሚጠናቀቅ በእቅዱ ውስጥ ተገልጿል። ይህም እውን አልሆነም።

በርካታዎቹ እቅዶች አለመሳካታቸው አስገራሚ አይደለም። አንደኛ ነገር፤ የመንግስት እቅዶች ብዙውን ጊዜ አይሳኩም። ለዚህኮ ነው፤ መንግስት በየጊዜው የሚነግረን ተአምራዊ የኢኮኖሚ እድገት፤ ኑሯችን ውስጥ ግባ ስንለው የውሃ ሽታ የሚሆንብን። የጥናት ውጤቶችም ይመሰክራሉ። ለተከታታይ አመታት ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት እንደተመዘገበ መንግስት ቢናገርም፤ በአይኤምኤፍና በአለም ባንክ ስሌት ግን፤ የኢኮኖሚ እድገቱ ከ8 በመቶ በታች ነው። የአለም ባንክ ለውይይት ያቀረበውን ሰነድ መመልከት ይቻላል - Ethiopia Country Partnership Strategy (CPS) FY13-16 ገፅ 4። ለነገሩ፤ በ1997 ወረቀት ላይ የተፃፉ የአምስት አመት እቅዶች፤ በተለይ እንደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ትልልቆቹ እቅዶችኮ ለአመታት እየተተጓተቱ እስከ ዛሬ መዝለቃቸውን ራሱ መንግስት አይክደውም። የእድገትና የትራንስፎርሜሽ እቅድ ተብለው የተነደፉት አዳዲሶቹ እቅዶችም በአብዛኛው ባይሳኩ አይገርምም።

ሁለተኛ ነገር፤ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ በተፈጥሮው ለስኬት የታደለ አይነት እቅድ አይደለም። የግል ኢንቨስትመንትን ቸል በማለት፤ በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ ይበልጥ ገናና እንዲሆን ለማድረግ የወጣው እቅድ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል፤ ቀደም ብለው የተናገሩና ምክር የለገሱ ወገኖች መኖራቸውን አትርሱ። በመጪዎቹ አመታት ሊመዘገብ የሚችለው የኢኮኖሚ እድገትም ከ8 በመቶ እንደሆነ የአይኤምኤፍ እና የአለምባንክ ኤክስፐርቶች 101 ገፅ በያዘ ሪፖርታቸው ገልፀዋል (Report No. 63592-ET, JOINT IDA-IMF STAFF ADVISORY NOTE ገፅ 3)።

ብዙዎቹ የመንግስት እቅዶች ብዙ ገንዘብ እንደሚፈጁና በርካታዎቹም እየተጓተቱ ለውጤት እንደማይበቁ የሚገልፀው ይሄው ሪፖርት፤ የግል ኢንቨስትመንትን የሚቀጭጭ እቅድ ነው በማለት ትችቱን ይቀጥላል። መንግስት እቅዶቹን እንዲያለዝብ በማሳሰብ ምክራቸውን የለገሱት የሁለቱ ተቋማት ኤክስፐርቶች፤ የግል ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መንግስት ቢጥር የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ይገኛል ብለዋል (ገፅ 4)።

በእርግጥ፤ በትናንሽ የገበሬ እርሻ ላይ በማተኮር ብዙ ገንዘብ ያፈሰሰው መንግስት፤ አሁን ፊቱን ወደ ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች እንዲሁ ወደ ኢንዱስትሪ በማዞር በርካታ ግዙፍ እቅዶችን ለማውጣት የተዋከበው አለምክንያት አይደለም። ቢጨንቀው ነው።

ትናንሽ የገበሬ እርሻዎች የሚያዛልቁ አልሆኑም፤ የፈሰሰባቸው ገንዘብ ለውጥ አላስገኘም። እንኳንስ እድገትን ሊያስገኙ ይቅርና፤ በልቶ ለማደርም አስተማማኝ እንዳልሆኑ ከአመት አመት ታይቷል። በሚሊዮን የሞቆጠሩ ገበሬዎች ያለ እርዳታ ህይወታቸውን ማሰንበት አይችሉም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የገጠር ወጣቶች፤ የሚረባ እንሰሳም ሆነ የሚታረስ መሬት የላቸውም።

ትናንሽ የገበሬ እርሻዎች ከእንግዲህ በተለይ ለገጠር ወጣቶች የኑሮ ዋስትና ሊሆኑ እንደማይችሉ በመጥቀስ የችግሩን ስፋት ለመዘርዘር የሚሞክር አንድ የአለምባንክ ሪፖርት፤ በየአመቱ እስከ 2.5 ሚ. የሚደርሱ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እየተፈጠሩ እንደሆነ ይገልፃል (CPS FY13-16 ገፅ 9)። ሁለት ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች በገጠር፤ ግማሽ ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች በከተማ... በጣም የሚያስጨንቅ ፈተና ነው።

እስካሁን ባለው የስራ አጦች ቁጥር ላይ፤ በአምስት አመት ውስጥ 10 ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ሲጨመሩበት፤ ምን አይነት ችግር እንደሚፈጠር ለመገመት ያስቸግራል።

እንኳንስ በየአመቱ እየተጨመረበት ይቅርና፤ የእስከዛሬውም ችግር ለሸክም ከባድ ሆኗል። በአለማቀፍ መመዘኛ መሰረት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 78 በመቶ ያህሉ ከድህነት ወለል በታች ተቀብሮ እንደሚኖር የዩኤንዲፒ ጥናት ይገልፃል። በኦክስፎርድ አመታዊ የኑሮ ደረጃ ጥናት ደግሞ፤ የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉ ሁለት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች - ከኒጀር ጋር። በ1997አ.ም የምግብ እጦት ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 27ሚ እንደነበረና በአምስት አመታትም ቁጥሩ በ1.5 ሚ እንደጨመረ የአለምባንክ መረጃ ያሳያል።

በዚህም ብታዩት... ድህነት፤ በዚያ በኩል ስታዩትም ችጋር ነው። ድርቅ በሌለባቸው አመታት ስምንት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ግን የተረጂዎቹ ቁጥር ከ12ሚ. አልቀንስ ብሏል (CPS FY13-16 ገፅ 8)።

የእርሻ ምርት እንዲህ ተስፋ የማይሰጥ ሲሆን፤ የገጠሩ ኑሮ እንዲህ በጨለማ ሲከበብ ... ያስፈራል። ታዲያ፤ መንግስትስ ስጋት ገብቶት “ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ይሻለኛል” ብሎ መአት እቅድ ቢያወጣና መዋከብ ቢያበዛ ምኑ ይገርማል!

ደግሞምኮ፤ የገጠሩ ችግር በከተሞችም አለ - ድህነትና ስራ አጥነት። የሚታረስ መሬት ያጡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የገጠር ወጣቶች፤ ኑሮ ፍለጋ ወደ ከተሞች ይፈልሳሉ፤ በየአመቱ ቢያንስ 400ሺ የገጠር ነዋሪዎች ወደ ከተማ ይጎርፋሉ።

በመዋለድም ሆነ በፍልሰት፤ የከተሞች የህዝብ ቁጥር በአማካይ በየአመቱ በ700ሺ ገደማ እየጨመረ ነው። ከሰባት አመት በፊት 8.5 ሚሊዮን የነበረው የከተሞች ህዝብ ቁጥር፤ ዛሬ 13.5 ሚ. በላይ ሆኗል። ከዚሁ ጋርም የስራ ፈላጊዎች ቁጥር ሽቅብ ይጨምራል።

በ1998 አ.ም በአገራችን ከተሞች ውስጥ፤ 4.6 ሚ. ያህል ስራ ፈላጊዎች ነበሩ (UEUS, July 2006 ገፅ 15)። በ2003 ግን የስራ ፈላጊዎቹ ብዛት ወደ 6.3 ጨምሯል (UEUS, August 2011, Table 4.1. ገፅ 41)። በእርግጥ በእነዚህ አመታት ውስጥ ተጨማሪ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል፤ ተጨማሪ ሰራተኞች ተቀጥረዋል ወይም የራሳቸውን ስራ ጀምረዋል። በዚህም ምክንያት፤ ከአምስት አመት በፊት 2.5 ሚ. የነበረው የመደበኛ ሰራተኞች ቁጥር፤ አሁን ወደ 2.9 ሚ. ተጠግቷል። ወደ አራት መቶ ሺ ገደማ አዳዲስ መደበኛ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል ማለት ነው።

ነገር ግን በቂ አልሆነም። በእነዚያ አምስት አመታት ውስጥኮ፤ የዚህን አራት እጥፍ ስራ ፈላጊዎች ተፈጥረዋል። ሩብ ያህሉ ብቻ ስራ ያገኛሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ተባራሪ ስራ ላይ ይሰማራሉ።

ከወላጆች ቤት ሳይወጡ ያለ ክፍያ የሚሰሩ ወይም በቤት ሰራተኝነት የሚቀጠሩም በርካታ ናቸው። ብዙዎቹ ደግሞ ስራ አጥ ይሆናሉ። ለዚህም ነው፤ በ1998 አ.ም 770ሺ ገደማ የነበረው የከተሜ ስራ አጥ ቁጥር፤ በአምስት አመታት ውስጥ በ50 በመቶ ገደማ የጨመረው። 360ሺ ተጨማሪ ስራ አጦች ተፈጥረዋላ። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ፤ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የከተሜ ስራአጥ ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ይሆናል።

የስራ አጥነት ችግር እጅግ አስፈሪ እንደሆነ ይበልጥ ለመገንዘብ ከፈለጋችሁ የአዲስ አበባን ሁኔታ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ባለወጣው ሪፖርት ውስጥ ማየት ትችላላችሁ (UEUS August 2011)። በአዲስ አበባ፤ ከ1.53 ሚ በላይ ስራ ፈላጊዎች አሉ (ገፅ 51)። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል ክፍያ የሚያስገኝ ስራ ላይ ለመሰማራት የቻሉት 770ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው (ገፅ 41)። ቀሪው 760ሺ የአዲስ አበባ ስራ ፈላጊ፤ ... በቃ፤ ያለ ክፍያ የሚሰራ አልያም ከነጭራሹ ስራ አጥ ነው። የስራ አጡ ቁጥር፤ 385ሺ ገደማ ይሆናል (ገፅ 53)። የስራ አጦች ብዛት ብቻ አይደለም አስፈሪው ነገር ። ከስራ አጦቹ መካከል በርካታዎቹ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ የያዙ መሆናቸውም አሳሳቢ ነው።

ከአምስት አመት በፊት፤ የሁሉም ከተሞች ተደማምሮ፤ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ የያዙ ስራ አጦች 30ሺ ገደማ ነበሩ። አሁን ቁጥራቸው ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል። 115ሺ ባለዲግሪና ባለዲፕሎማ ስራ አጦች አሉ (46ሺ ያህሉ በአዲስ አበባ)። ብዙዎቹም ወጣቶች ናቸው። 90ሺ ያህሉ፤ እድሜያቸው 30 አመት በታች ነው።

እንግዲህ፤ መንግስት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ገናናነቱን ለማግዘፍ ዘመቻ የጀመረው፤ የገጠሩ ረሃብና የከተማው ስራአጥነት አስፈርቶት ከሆነ፤ ይሄው እንደምናየው አስፈሪዎቹ ነገሮች እየቀነሱ ሳይሆን እየገዘፉ መጥተዋል። መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይዞ መግነን ሲጀምር፤ ብዙም ስኬታማ እንደማይሆን፤ የእስከዛሬዎቹ አመታት ጥሩ ምስክር ናቸው። በደርግ ዘመንም፤ ከውድቀት የተለየ ውጤት አልታየም። በኢህአዴግ ዘመን፤ ለግል ኢንቨስትመንትና ለግል ቢዝነስ በተወሰነ ደረጃ ነፃነት ስለተፈቀደ፤ በዚያችው መጠን የኢኮኖሚ መነቃቃት ታይቷል። ነገር ግን፤ ባለፉት አራት አምስት አመታት እንደገና ገናና የመሆን አባዜ ተነስቶበታል - “የስራ አጥነት ነገር አስግቶኝ፤ የድህነት ጉዳይ አስፈርቶኝ ነው” እያለ ግዙፍ የቢዝነስና የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶችን ያውጃል። ምን ዋጋ አለው? ውጤቱ፤ ያው ተጨማሪ ስራ አጥነትና ድህነት ነው። ሩጫው፤ ከአስፈሪ ነገር ለማምለጥ የማይጠቅም የህልም ሩጫ ነው።

 

 

Read 3690 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 06:42

Latest from