Saturday, 22 June 2019 11:26

የኢትዮ-ኬንያ 55ኛ ወርቃማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዓመታት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የእንግሊዛዊው ጆን ሄንሪ ቴምፕል “ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም” የሚለው አባባል በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ የተለመደ ነው። ወዳጅ ጠላት ይሆናል። ጠላትም ወዳጅ ሊሆን ይችላል። የማይቀየረው የአገራት ጥቅም ነው እንደማለት ነው። ይህ መርህ እንዳለ ሆኖ፣ የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት በዚህ ሚዛን ሲታቀን፣ በመንግስታት መለዋወጥ ውስጥ የማይዋዥቅ ሆኖ እናገኘዋለን። የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአካባቢው አገሮች ካለን ምሳሌያዊ ነው። ኬንያ ነፃ ከመውጣቷ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ጋር ግንኙነት ነበራት።
ግንኙነቱ ወጥና በሁኔታዎች መለዋወጥ የማይዋዥቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሠላማዊ ነው። አንጃ-ግራንጃ አልነበረውም። ይህ ጉርብትና ዕድሜ ጠገብ ነው። ሃምሳ አምስት ዓመት በያዝነው ሰኔ ወር ደፍኗል። ግንኙነቱ በይፋ የተጀመረበት ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በ35ኛው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ በዓለ ሲመት ላይ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል ነበር። ስራቸውን እንዘክራለን፤ ስለ አስተዋፅኦዋቸው አክብሮት አለን። ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። ባለወር ተረኛውስ? ጊዜው የሁለቱ አገራት መሪዎች ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከተለመደው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ባለፈ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ አትኩረው መስራት የጀመሩበት ነው።
 ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መሠረቱ ከተጣለ በኋላ በየጊዜው እየተመላለሱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንዲያልቅ ያደረጉት ጆሞ ኬንያታ ነበሩ። ከቤተ መንግስታቸው በመቶ ሜትሮች  ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ኤምባሲ፤ ዛሬም የመሪዎቹ ቅርስ፤ የአገሪቱ ወዳጅነት ማሳያ ሃውልት ነው። የኢትዮጵያውያን ቤት /Ethiopian House/ ሊባል ይችላል። ይገባዋልም።
የኢትዮጵያ ኬንያ ግንኙነት ወዳጅነት ሌላው ማሳያ በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው ወመዘክር (National Archives) ነው። ከየትኛውም የአካባቢው አገሮች ተለይታ ኢትዮጵያ ብቻ የምትዘከርበት፤ የኢትዮጵያውያን ቅርሶችና ድርሳናት ለዕይታ የሚበቁበት ክፍል ወመዘክሩ አለው። ለአክባሪ ክብረት ይስጠው ይላሉ፤ ወላጆቻችን።
ናይሮቢ እምብርት በሚገኘው በዚህ ማዕከል ውስጥ እኛ ሳይቀር የሌሉን የኢትዮጵያ መሪዎች ታሪካዊ ፎቶዎች፣ ጥንታዊ ፅሁፎች፣ አልባሳትና የተሰባሰቡ ጌጣጌጦች አሉ። በኬንያታ ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩት ጆሴፍ ሙሩምቢ ናቸው። ማዕከሉን የጎበኘ፣ ናይሮቢን የረገጠ ቱሪስት፤ የኢትዮጵያን ናሙና ጀጎልም አክሱምም ሳይሄድ ናይሮቢ ውስጥ ያያል። የኢትዮጵያ ኤምባሲና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንዲሁም ዜጎች አገራችንን የበለጠ ለማስተዋወቅ ሊጠቀሙበት ይገባል። አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ፤ ተመሳሳይ የኢትዮጵያን ባህል የሚያሳይ አካል ሩስያ ውስጥ ይገኛል። ከየአገራቱ ጋር ለሚካሄደው የባህል ዲፕሎማሲ መነሻ ይሆናል። ያለምንም ወጪና ውጣ ውረድ አገርን ያስተዋውቃል። ይህን ይህን ሳስብ፣ አንዳንዴ ሌሎች ለእኛና ለኢትዮጵያ ያላቸውን ክብር ትብያ የጣልነው ሆኖ ይሰማኛል። ነገር ላብርድ?
የጀመሩትን መቀጠል። የኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነት ሠላማዊና የማይዋዥቅ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ሆኑ ጀሞ ኬንያታ ለአንድ አፍታ ቀና ቢሉ፤ ጉርብትናውን በተመለከተ ምን ይሉ ይሆን ብዬ አስባለሁ? ወዳጅነቱ በብዙ መስኮት መልካም ውጤት የተመዘገቡበት ብቻ ሳይሆን ብዙ ተግዳሮቶችም፣ ተስፋዎችም ያሉት ነው።
በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በኃይል ማመንጨት በአካባቢያዊ የሠላምና ደህንነት መስኮች መሪዎች ካስቀመጡት ራዕይ አንፃር አገሮቻችን ብዙ ተራምደዋል። ድህነት፣ አካባቢያዊ ግጭት፣ አሸባሪነት አሁንም  የሁለቱም አገራት  ስጋቶች ናቸው።
ያም ቢሆን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ግንኙነቱ ብዙ ተስፋዎች ያሉት ነው። የላሙ ፕሮጀክት፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ፕሮጀክቱ ባዶ ህልም አይደለም። በመንገድና የወደብ ልማት በኩል ብዙ ርቀት ተኪዷል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ለውጥ አንፃር፣ ወደ አገራችን መግባት የሚፈልጉ ባለሃብቶች (በተለይም የሌላ አገር ተወላጆች) ብዙ ናቸው። ብዙ የኬንያ ባንኮች፣ ጽ/ቤት አዲስ አበባ መክፈት ጀምረዋል። ይህ ዕድልም ፈተናዎችም እንዳሉት ሳንዘነጋ  መዘጋጀት ነው።
ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች፤ የኬንያ ከተሞች ከናይሮቢ - ሞምባሳ፣ ከኪሱሙ -ናይቫሻ የኬንያ ገበያ ሊሸጡ የሚችሉ ብዙ የኢትዮጵያ ምርቶች መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኬንያ የአፍሪካ ሲልከንቫሊ ናት። ልብ ይሏል። እንግዳ መጥቶ የማያፍርበት የአገልግሎት ዘርፍ፤ ጉብኚዎች የሚጎርፉለት ቱሪዝም አላቸው። ከጎረቤታችን የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የግንኙነታችንን 55ኛ ዓመት ስናስብ፤ የምንማረውም የምናስተምረውም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከሩጫ ባለፈ የማናውቃቸውን ያህል፣ እነሱም አያውቁንም። የፖለቲካ ወዳጅነቱ ትርጉም የሚኖረው፤ለእኛ እንጀራ፣ ለእነሱ ደግሞ ኡጋሊ እንዲኖረው ካደረግን ብቻ ነው። መልካም 55ኛ ዓመት ለህዝቦቻችን!!

Read 1939 times