Saturday, 22 June 2019 11:27

ቃለ ምልልስ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ እርቅና ሽምግልና ከደርግ እስከ ዛሬ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 - ሽምግልናን ያበላሸው የፖለቲከኞች ያልተገባ ትዕቢት ነው
              - እኛ አገር ትልቁ ችግር ቅጥ ያጣ የሥልጣን ፍላጐት ነው


          በአገራችን የተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የእርቅና ሽምግልና ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ናቸው፡፡ የደርግ መንግስትን የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይንና የኤርትራ ህዝቦች ነፃነት ግንባርን ለማቀራረብና ጉዳያቸውን በሽምግልና እንዲፈጽሙ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ለእስር የተዳረጉትን የቅንጅት አመራሮች ከእስር ለማስፈታት በተደረገው የእርቅና ሽምግልና ሂደት ውስጥም ተሳትፈዋል፡፡ የኢህአዴግ መንግስትና የኤርትራ መንግስትን ለማቀራረብና ለማስታረቅም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ በውጪ አገር ለትምህርት በቆዩባቸው ረጅም ዓመታት በሃይማኖቶች ጥናት በታሪክና በፍልስፍና የጠለቀ ዕውቀት ገብይተዋል፡፡ በአገራችን የእርቅና ሽምግልና ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ የሚጠራው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ከደርግ ዘመን ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለፉበትን የአገራችንን የእርቅና ሽምግልና ሂደት ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አጫውተውታል፡፡

                እስከ ዛሬ በሽምግልናው በኩል ምን ተግባራትን አከናውናችኋል?
በ1980 አካባቢ ይመስለኛል… ክቡር ራስ መንገሻ ደውለውልኝ፣ ካናዳ ቶሮንቶ ላይ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ለማቆም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ይሰባሰባሉ አሉኝ፡፡ እዚያ ስብሰባ ላይ ከደርግ በስተቀር ህውሓትን፤ ኦነግን ጨምሮ ብዙዎቹ መጥተው ነበር፡፡ እኛ ደግሞ በስብሰባው ላይ ታዛቢ ነበርን፡፡ በወቅቱ ራስ መንገሻ ስዩም፤ ከስብሰባው የቀሩት፣ የኤርትራ ህዝብ ነፃነት ግንባርና ደርግ እንዲሁም ህውሓት ጋ ሽማግሌ መላክ አለበት ሲሉ አማከሩን፡፡ እኔንም አንድ ሽማግሌ አድርገው ጋበዙኝ፡፡ ካሳሁን ብስራት የሚባል የቀድሞ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረና አቶ አሰፋ የሚባሉ ሰው - ሶስት ሰዎችን ጋበዙን፡፡ በኋላም እኔ የዚያ የሽማግሌ ቡድን መሪ ሆኜ ወደ ህውሓትም፣ ወደ የኤርትራ ህዝቦች ነፃነት ግንባርም፣ ወደ ደርግም ተላክን፡፡ ሽምግልና እንግዲህ የጀመርነው በዚህ መልክ ነው፡፡ እኔ በወቅቱ ብዙዎቹን ተዋጊዎች አውቃቸው ነበር፡፡ ሽምግልናዬንም በሙሉ ልባቸው ተቀብለውት ነበር፡፡ የሌሎቹን ሽምግልና ግን “እገሌን አልቀበልም፤ እገሌን እቀበላለሁ” እያሉ ድርጅቶቹ ሲያስቸግሩን፣ ሌላ ሁሉም የሚቀበለውና ሁሉንም የሚያስማማ የሽምግልና ቡድን ወደ ማቋቋሙ ገባን፡፡ ያኔ እኛ ዝም ብለን የ20 ሰዎች ስም ዝርዝር አውጥተን ለደርግ፣ ለህውሓት፣ ለኢህዴግ ልከን፣ ከእነዚህ መካከል የምትቀበሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን አልናቸው፡፡ እነሱም የወደዷቸውን ጠቆሙን፡፡ ከጠቆሙት መካከል ሶስቱም ተቀናቃኝ ድርጅቶች፣ 12 ያህል ሰዎችን በእኩል መርጠዋቸው ነበር:: እነዚያን 12 ሰዎች መርጠን፣ የሽምግልና ቡድን እንደገና አቋቋምን፡፡ በዚህ የሽምግልና ቡድን ውስጥ ዶ/ር ኃይለ ሥላሴ በላይ፣ ጥላሁን በየነ፣ አህመድ ምሄን፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ፕ/ር አስቴር መንገሻ፣  ፍስሃፅዮን ትኬ፣ ፕ/ር አባይነህ ወርቄ ይጠቀሳሉ፡፡ ሽምግልና ብለን ስንነሳ ስንጀምር፣ የሃገራችን የሽምግልና ባህል ምንድን ነው? ሽማግሌ ሲባል ምን አይነት ሰው ነው? ብለን ተወያይተን ተመካክረን፣ ጥናት አጥንተን ውጤቱ ላይ የጋራ መግባባት ይዘን ነው የጀመርነው፡፡ በኋላም ይህ የተቋቋመውና ሁሉም ያመኑበት የሽማግሌ ቡድን፤ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሽምግልና ደብዳቤ ላከላቸው፡፡
የደብዳቤው ይዘት ምን ነበር?
አሁን ሁሉንም ማስታወስ ቢቸግረኝም፤ “ወንድሞቻችን እህቶቻችን፤ ሃገራችን በረሃብም በጦርነትም በርካታ ህዝብ እያለቀባት ነው:: እኛ የሃገር ወዳጅ ሽማግሌዎች፤ የእናንተው ወዳጆቻችሁ፣ አስተማሪዎቻችሁ የሆንነው ሁሉ፣ እናንተ አንድ ላይ ተሰብስባችሁ፣ በኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ እንድታደርጉ ስለምንፈልግ፣ እንድትመጡልን” ብለን ነበር የላክንላቸው፡፡ በጣም ደስ የሚያሰኘው ሁላቸውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በጎ መልስ ሰጡን፡፡ ደርግ ግን አሁንም መልስ አልሰጠንም፡፡ በመጀመሪያ መልስ የሰጡን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ ቀጥሎ የኦነግ ቡድን፣ በኋላም የኤርትራ ቡድኖች ነበሩ መልስ የሰጡን፡፡ ሁሉም እንመጣለን ብለው ቃል ገቡልን፡፡ በደርግ በኩል መልስ ሳናገኝ ስንቀር፣ ዋሽንግተን ለነበሩት አምባሳደር ተስፋዬ ስልክ ደወልኩላቸው፡፡ ለምንድን ነው ደርግ ምላሽ የማይሰጠን? ስላቸው፣ ደርግ እሺ ብሏል፤ ችግር የለውም አሉን፡፡ ነገር ግን በደብዳቤ እሺታቸውን አልገለፁልንም ነበር፡፡ በኋላ በሰኔ ለመሰብሰብ እቅድ አወጣን፤ ነገር ግን ከእነ አቶ መለስ በኩል “ከሰኔ ይልቅ ቀደም ብሎ በግንቦት ይሁን፤ ምክንያቱም እኛ ወደ መሃል ሃገር እየገባን ስለሆነ መዘግየቱ መልካም አይሆንም” አሉን፡፡ እኛም ፕሮግራማችንን ወደ ግንቦት አዘዋውረን ቀጠሮ ያዝን፡፡
እነ ኾኸን የሚመሩት የለንደኑ ስብሰባ ደግሞ እኛ ከያዝነው ቀን ቀደም ብሎ ፕሮግራም ተይዞ ነበር፡፡ በኋላ የለንደኑ ስብሰባ ሲካሄድ፣ እኔም አቶ መለስን ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ተዋወቅኋቸው፡፡ አቶ ኢሳያስን እንኳ ቀድሞም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ያውቁኝ ነበር፡፡ የለንደኑ ስብሰባ ላይ እኛ አልገባንም፤ የሄድነው ሰዎቹን አግኝቶ ለእርቅ ለማግባባት ነበር:: አሜሪካኖቹ የሰበሰቧቸው ጦርነቱ እንዲቆም በሚል አጀንዳ ነበር፡፡ የኛ ስብሰባ ደግሞ በቀጣይ እ.ኤ.አ ጁን 5 እንዲካሄድ ነበር ቀጠሯችን፡፡ በዚህ መሃል ነው አዲስ አበባ ተይዞ፣ ሁሉም ነገር ያበቃው፡፡
ኤርትራና ኢትዮጵያን ለማሸማገል ጥረት አድርጋችሁ ነበር … እንዴት ነበር ሂደቱ
ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ለሁለቱም መሪዎች ደብዳቤ ፃፍን፡፡ አቶ ኢሳያስ ሽምግልናችንን በደስታ ነበር የተቀበሉን፡፡ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ትንሽ ነገሩ ተጓቶብን ነበር፡፡ በኋላ ተነጋግረን ፍቃደኝነትን ስናገኝ፣ ወደ ኤርትራ ማቅናት ነበረብን፡፡ ያኔ ደግሞ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የአየር ጉዞ ተቋርጦ ነበር፡፡ እኛም ትንሽ አውሮፕላን ተከራይተን፣ በጅቡቲ ዞረን፣ ኤርትራ ሄደን፣ አቶ ኢሳያስን አገኘናቸው፡፡ በእውነቱ በወቅቱ አቶ ኢሳያስ፤ በጨዋ ደንብ በጥሩ መልኩ ተቀብለውን፣ ለ5 ሰአታት ያህል ነበር ያነጋገሩን፡፡ እንደውም የእናንተን ሽምግልና ነው እንጂ የውጪ ሃገር ሰዎችን አልፈልግም ይሉ ነበር፡፡ በኋላ ግን አልጀርስ ላይ ውሳኔው ወደ እነሱ ሲያደላ፣ የውጭ ሃገሩን መረጡና እኛን ችላ አሉን፡፡ እኔ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ሁለት ሶስት ጊዜ ሄጃለሁ፡፡ አቶ ኢሳያስ እኮ ከባድመ ለመውጣት ሁሉ ፍቃደኛ ሆነው ነበር፡፡ ይሄን ጉዳይ እስካሁን ማንም ሰው አያውቅም፤ ነገር ግን ፍቃደኛ የነበሩበት ደብዳቤ እኔ ጋ አለ፡፡ ነገር ግን የመውጣቱ ቦታ ብያኔ ላይ ትንሽ ችግር ተፈጠረ፤ በኋላም የመጨረሻው ጦርነት ፈንድቶ ነገሩ ሁሉ ከሸፈብን ማለት ነው፡፡ ነገሩ በአልጀርስ ውሳኔ ሲቋጭ፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ በኢትዮጵያ በኩል የኛ ሽምግልና እንዲጠናከር ተፈለገ፡፡ በኤርትራ በኩል ደግሞ ቸልተኝነት መጣ ማለት ነው፡፡ እኔ ከአቶ ኢሳያስ ጋር እስከ አምና ድረስ እንፃፃፍ ነበር፡፡ ጥሩ ወዳጅነት አለን፡፡
ጦርነቱ ካለቀ በኋላስ ….
ጦርነቱ ካለቀ በኋላ በቀጥታ “እስረኞች ይፈቱ” ወደሚለው ሽምግልናችን ገባን፡፡ ግን የሚፈለገው ውጤት አልመጣም፡፡ በኋላም የ1997 ምርጫ ጉዳይ መጣ፡፡ ምርጫው ተካሂዶ ሲያልቅ፣ ያ ሁሉም የሚያውቀው ችግር ተፈጠረ፡፡
ችግሩ ሲፈጠር እናንተ መጀመሪያ ምን ነበር ያደረጋችሁት?
እኛ እንቅስቃሴ የጀመርነው የቅንጅት ሰዎች ሳይታሰሩ በፊት ነበር፡፡ እንደውም እኔ ለአቶ መለስ በፃፍኩት የመጀመሪያ ደብዳቤ፤ ለቅንጅት ሰዎች በመንግስት ስልጣን ውስጥ ቦታ ይሰጣቸውና ችግሩ ይፈታ ብያቸው ነበር፡፡
አቶ መለስ ለዚህ ምን ምላሽ ሰጡዎት?
እሳቸው መልስ የሰጡኝ በመጀመሪያ ያገኙትን ድምፅ ይዘው ፓርላማ ይግቡና ቀሪውን ጉዳይ ለመነጋገር እንችላለን ነው ያሉኝ፡። በኋላ አቶ መለስ “እባክዎ ይምከሯቸው፤ እኛ በኢትዮጵያ አጠቃላይ አሸንፈናል፤ እነሱ ደግሞ አዲስ አበባን አሸንፈዋል፤ ወደ ፓርላማው ይግቡልን፤ ምከሯቸው” ብለውኝ ደብዳቤ ፃፉልኝ፡፡ እኔም ለእነ ዶ/ር ያዕቆብ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ብለዋልና “እባካችሁ ፓርላማ ግቡና ስራችሁን ስሩ” አልኳቸው፡፡ እነሱ አሁንም ነገሩን ችላ አሉት፡፡ እንደገና ከሁለት ሳምንት በኋላ ከአቶ መለስ ሌላ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ “ቅንጅቶች ፓርላማ በመግባት ፈንታ ህዝቡን ወዳልተገባ አቅጣጫ እየቀሰቀሱት ነው፤ እባክዎ ይምከሯቸው” አሉኝ፡፡ እኔም እንደገና ደወልኩላቸው፡፡ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስንም እንዲሁ አነጋገርኩ፤ “እባካችሁ ችግር እንዳይፈጠር ፓርላማ ግቡ” ብዬ ለመንኩ፡፡ አሁንም ሰሚ አላገኘሁም:: በኋላ ወደ ውጪ ሃገር በወጣሁበት አጋጣሚ፣ እዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ብዙ ሰው ሞተ፡፡ በኋላ ወደ ሃገር ቤት ስመለስ ነው ሰልፍ ተደርጎ፣ በርካቶች መሞታቸውን፣ ፖለቲከኞቹም መታሰራቸውን የነገሩኝ፡፡ ከአሜሪካ አብረውኝ የመጡት ጥቁር አሜሪካውያን የኢትዮጵያ ወዳጆች፤ ጠ/ሚኒስትሩን ለማግኘት፣ ወደ ፅ/ቤታቸው ባቀኑበት ወቅት አብሬ ሄጄ ነበር፡፡ ውይይቱ ካለቀ በኋላ ወደ ኋላ ቀርቼ “እባክዎ ላነጋግርዎ” ስላቸው፤ “በሰፊው ከሆነ በቀጠሮ ይሁን” አሉኝ፡፡ “አይ ሄጄ እንኳ ባያቸው ይፈቀድልኝ” አልኩ፡፡ “እሺ ሂድና እያቸው” አሉኝ፡፡ ማዕከላዊ ነበር  የታሰሩት፡፡ በኋላ አንድ ሰው ደውሎልኝ፣ ሻለቃ ወርቅነህ ይመስለኛል “መጥተን እንወስድሃለን፤ ሌላ ፓስተር ዳንኤል የሚባል ሰውም አለ፤ ሊተዋወቅህ ይፈልጋል” አሉኝ፡፡ መልሰው “እሱ መጥቶ ይውሰድህ ወይ” ሲሉኝ፡፡ ይቻላል አልኳቸው፡፡ ከፓስተር ዳንኤል ጋር የተዋወቅነው ያን ጊዜ ነው፡፡
ከዚያስ የሽምግልና ሂደቱ እንዴት ቀጠለ?
በኔ ሽምግልና አቶ መለስ ከተስማሙ በኋላ “እስረኞቹን ማነጋገር ያለብህ ለብቻህ ነው፤ እንዲያውም እስረኞቹን ለየብቻ አነጋግር” አሉኝ:: እኔም ተስማምቼ፣ ሁሉንም በየተራ፣ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል፣ ፕ/ር መስፍን፣ ዶ/ር ብርሃኑ፣ ዶ/ር ያዕቆብ፣ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፣ ወ/ት ብርቱካን … እያንዳንዳቸውን ለየብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ አነጋገርኳቸው፡፡ እነሱም በጐ ፍቃደኛነታቸውን ገለፁልኝ፡፡ እኔም ወደ አቶ መለስ ተመልሼ ሄጄ “እነዚህ ሰዎች፣ ሀገራቸውን ማገልገል ይፈልጋሉ፤ በተፈጠረውም ነገር እያዘኑ ነው፤ ምናለበት የሚወጡበት ቀና መንገድ ቢፈለግ” አልኳቸው፡፡
እሳቸው ምን አሉ ታዲያ?
“እሺ ይሁን፤ መልካም ነው” ብለው አራት ነጥቦችን ጽፈው ሰጡኝ፡፡ አንደኛው፣ ለተደረገው ነገር ሁሉ ኃላፊነት እንወስዳለን የሚል፣ ሁለተኛው መንግስት ራሱ አጥፍቶ እንደሆነ ምርመራ ይደረጋል፤ ሶስተኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሁሉ በሠላም ለመፍታት ፍቃደኝነት እንዳላቸው፤ አራተኛውን አሁን በሚገባ አላስታውስም፡፡ ይሄን ሰጡኝ፡፡ እኔም “በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር፣ ሁሉንም እስረኞች አንድ ላይ እንዳገኛቸው ይፈቀድልኝ” አልኳቸው፡፡ እሺ አሉኝ፡፡ አገኘኋቸውና ወረቀቱን (የአቶ መለስ አራት ነጥቦችን) አሳየኋቸው፡፡ በወቅቱ ፓስተር ዳንኤል ነበሩ በመኪናቸው የወሰዱኝ፡፡  ሽምግልና ውስጥ አልገቡም ነበር፡፡ በኋላ ግን ሂደቱ በቀጠለ ጊዜ አቶ መለስ ጋር ቀርቤ፣ “ሽምግልናውን ለማከናወን ምስክሮች ያስፈልጉኛል፤ በሃሳብም ይረዱኛል” አልኳቸው፡፡
እሣቸውም እነማን ይሁንልዎ አሉኝ፡፡ አንደኛ አምባሳደር በቀለ እንደሻው (በወቅቱ የሠላምና እድገት ማህበር ዳይሬክተር ነበሩ)፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለዚህ ጉዳይ ስመጣ በቲኬት የረዱኝ አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ፣ ሶስተኛ ወደ እስር ቤት በማመላለስ የረዱኝ ፓስተር ዳንኤል አልኳቸው፡፡ እሣቸውም ቆይ ላስብበት ካሉኝ በኋላ በሁለተኛው ቀን ይሁን አሉኝ፡፡ በዚህ መንገድ ነው የሽምግልና ቡድኑ ወደ መዋቀር የመጣው፡፡ ይሄ ሁሉ ጥረት ይካሄድ የነበረው፣ የታሣሪዎቹ ጉዳይ ገና ወደ ፍ/ቤት ሳይሄድ ነው፡፡ አቶ መለስም በወቅቱ “ጉዳዩ ፍ/ቤት ከሄደ በኋላ ከኛ አቅም በላይ ይሆናል፤ በእርቁ የሚስማሙ ከሆነ አሁን ቶሎ ይፈርሙ” ብለውን ነበር፡፡ ታሳሪዎቹ ደግሞ በአንድ በኩል እሺ ይላሉ፤ በሌላ በኩል “አንዳንድ ጉዳዮች ካልተሻሻለ አንፈርምም” አሉኝ፡፡
ምን አይነት ጉዳዮች ነበሩ እንዲሻሻል የሚጠይቁት?
አሁን ሁሉንም አላስታውስም ግን አንዱ “እኛ ብቻ ሳንሆን መንግስትም ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ኃላፊነቱን ይውሰድ” የሚል ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ያው ጊዜው ተጓተተና መንግስት ወደ ክስ ገባ ማለት ነው፡፡
በኋላ ላይ እኔ ኬንያ ስብሰባ ላይ ሆኜ፣ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ማምራቱን ሰማሁ፡፡ ወዲያው ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ፣ አቶ መለስ ጋ ሄድኩ፡፡ ነገሩ ምንድን ነው ስላቸው፣ ያው እርስዎ እንደሚያውቁት፣ እኛ እስከቻልነው በሩን ከፍተንላቸዋል፡፡ አልተቀበሉንም፤ ስለዚህ እኔ ከዚህ በላይ ነገሩን መቆጣጠር አልችልም፤ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ሄዷል፡፡ ማድረግ እችል የነበረው አቃቤ ህጉ ክሱን እንዲተው ነበር፡፡ አሁን ፍ/ቤቱ ጋ ደርሷል፡፡ ዳኞችን ማዘዝ አልችልም፤ አይፈቀድልኝም፡፡ ዳኛውን አቋርጥ ማለት አልችልም፤” አሉኝ፡፡ “ፍርዱ ከታወቀ በኋላ ጥረቶችን ይቀጥሉ፤ ተመልሰው ይምጡ” አሉኝና ተሰነባበትን፡፡ ፍርዱ ተፈርዶባቸው ካበቃ በኋላ ነው፣ ሁለተኛውን ጥረት የጀመርነው፡፡ በእውነቱ የመጀመሪያው እድል በመበላሸቱ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ በሩ ተከፍቶ ያለምንም የፍርድ ሂደት በነፃ መውጣት ይቻል ነበር፡፡ መጀመሪያውኑ ወደ ፍ/ቤት ባይኬድ ኖሮ፣ ወ/ት ብርቱካን ላይ የደረሰው ችግርም ባላጋጠመ ነበር፡፡
ከተፈረደባቸው በኋላ ምን አደረጋችሁ?
ፍርድ ከተፈረደባቸው በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመልሼ መጣሁና እንደገና ጥረቱን ቀጠልኩ፡፡ ዶ/ር ኃይለስላሴ በላይ፣ ዶ/ር ጥላሁን በየነና ዶ/ር አህመድ ጋር ሆነን እስረኞቹን ከፍርዱ በኋላ ሄጄ አነጋገርኳቸው፡፡ ከእነ ፕ/ር መስፍን፣ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ጋር ጥሩ ውሎ አሳለፍን፡፡ ነገር ግን በኋላም ይሄው የቃላት አተረጓጐም ክርክሩ ቀጥሎ ነበር፡፡
በኋላ ፈርመው የወጡትን አወዛጋቢ የይቅርታ ሰነድ ማን ነው ያረቀቀው?
ወረቀቱንማ መንግስት ነው “እንዲህ ብለው ይፈርሙ” ብሎ የሰጠን እንጂ እኛ ያረቀቅነው አይደለም፡፡  ግን አንድ ሰኞ ቀን ብቻዬን ሄጄ ሃይሉ ሻውልን በጉዳዩ ላይ አነጋገርኳቸው፡፡ በእርቁ አስፈላጊነት ተማከርን፡፡ በንግግራችን ወቅት በፍፁም መግባባት “እሺ ፈርመን እንወጣለን” አሉኝ፡፡ ሁሉም ታሣሪዎች ይጠሩ ተብሎ ውይይት በጋራ አደረግን፡፡ በውይይቱ ወቅት ኢ/ር ሃይሉ ሻውል “እኛ ብንወጣ በኛ ምክንያት ብዙ የታሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ እኛ ወጥተን እነሱ ምን ይሆናሉ” አሉኝ፡፡ “ግደለም በሱ በኩል ያለውን ኃላፊነት እኔ እወስዳለሁ፡፡ እናንተ ዋናዎቹ ወጥታችሁ እነሱ የሚቀሩበት ምክንያት የለም” አልኳቸው፡፡ “እንደዚያ ከሆነ እሺ” አሉኝ፡፡ “እንፈርማለን በቃ” አሉ ሁሉም:: ለመፈረም መስማማታቸውን ኢ/ር ኃይሉ እና ዶ/ር ብርሃኑ በፊርማቸው አረጋገጡልኝ፡፡ እሱን ይዤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሄድኩ፡፡ እሣቸውም የቀድሞ የስምምነት ነጥቦች ላይ ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ እንደገና አርቅቀው ሰጡኝ፤ መፈረሚያውን፡፡
የተለወጠው “እኛ” ይል የነበረው ቃል “እኔ እገሌ” በሚል መተካቱ ነበር፡፡ በበነጋታው ለማስፈረም ወደ እስር ቤት ብቻዬን ስሄድ፣ ሁሉም ቁጭ ብለው እየተጠባበቁ ነበር፡፡ በኋላ ወረቀቱን ሲያነቡት፤ እኛ የሚለው እኔ በሚለው ተለውጧል፡፡ ትናንት የፈረምንበት በድርጅታችን በኩል “እኛ የፈፀምነው የሚል ነው፤ ይሄኛው እኔ የፈፀምኩት የሚል ነው፤ አንቀበለውም እንዲያስተካክሉ ንገር” አሉኝ፡፡ እኔ በእውነት የሚያሳዝነኝ፣ አሜሪካ የራሴ ቤተሰብና ህይወት እያለኝ፣ ድካሜን የሚገነዘብ መጥፋቱ ነው፡፡
ከዚያ “እንዲህ አድርግ” ከዚህ ደግሞ “እንዲያ አድርግ” እያሉ እንደ ኳስ ነው የተጫወቱብኝ፡፡ በጣም ድካም ነበረው፡፡ አንደኛ ከአሜሪካ ወደዚህ መመላለስ በጣም አድካሚ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ እሺ ብዬ “እኔ የሚለው በእኛ ይለወጥልን” ብለዋል አልኩ ለጠ/ሚኒስትሩ፡፡ እሳቸውም “ይሄን የሚፈርሙ ከሆነ ይፈርሙ አይለወጥም” አሉኝ፡፡ በቃ ምንም ማድረግ አይቻልም ብዬ ወደ አሜሪካ ተመለስኩ፡፡ ወደ አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ “እስረኞቹ ይፈልጉሃል” ተባልኩ እንደገና መጣሁ፡፡ ከመጣሁ በኋላ አንድ የቅንጅት ሃብታም ደጋፊ፤ የኢ/ር ሃይሉ ሻውልን ልጅ ይዞ መጥቶ፤ ሂልተን ቁጭ ብለን መነጋገር ጀመርን፡፡ በወቅቱ ልጁ ያነሳው “እኔ የሚለው ለነሱ አደገኛ ነው ብሎኛል፤ ጠበቃቸው ይለኛል፡፡ ማን ነው ጠበቃው ስለው፤ አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁ አለን፡፡ እስቲ አቶ ታምሩ ይጠሩ አልኳቸው፡፡ በእውነቱ አቶ ታምሩ በጣም ጥሩ ሰው ነበሩ፡፡ እንደውም ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ የነበረውን የሽምግልና ሂደት ነፍስ የዘሩበት እሣቸው ናቸው፡፡
አቶ ታምሩ ሰነዱን ካዩ በኋላ “ይሄ ምንም ልዩነት አያመጣም፤ እኛም ብላችሁ እኔም ብላችሁ ብትፈርሙ ያው ነው፡፡ ልዩነት የለውም” ብለው የገላገሉንና ሽምግልናውን ያስቀጠሉት እሳቸው ናቸው፡፡
በኋላ አቶ ታምሩን እስር ቤት ይዤ መሄድ እንዳለብኝ በመገንዘብ፣ እንቅልፍ ሳይወስድኝ ከ3 ቀን በኋላ ጠ/ሚኒስትሩ ጋ ደውዬ “አቶ ታምሩን ይዤ እንድሄድ ይፈቀድልኝ” አልኩ፤ ተስማሙ፡፡ እሁድ ቀን አብረን ተያይዘን ወደ እስር ቤት አመራን፤ ነገር ግን አሁንም አልተስማሙልንም፡፡ እኔ እና አቶ ታምሩ በተደጋጋሚ ነበር የተመላለስነው፡፡ ሁኔታው እጅግ አሰልቺ ነበር፡፡ በኋላ “እኛ ተሰባስበን እንወስን፤ አስፈቅዱልን” አሉኝ እስረኞቹ፡፡ እኔም ጠ/ሚኒስትሩን እንዲሰበሰቡ ይፈቀድላቸው ዘንድ ጠየቅሁ፡፡ “ፖለቲከኞች ናቸው፣ እንዲሰበሰቡ አንፈቅድላቸውም” አሉኝ፡፡ በጣም ለመንኳቸው፡፡ በኋላ “እሺ ለ1 ሰዓት ብቻ ይሰብሰቡ” አሉኝ፡፡ እኔና አቶ ታምሩ “1 ሰዓት ብቻ ተሰብሰቡና ውሣኔያችሁን አሳውቁን” ብለን ውጪ ተቀምጠን መጠባበቅ ጀመርን፡፡ ነገር ግን ስብሰባቸውን ለ4 ሰዓት ነበር የቀጠሉት፡፡ ከዚያ በኋላ ፕ/ር መስፍን “እኔ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፤ አማካሪ ነኝ ስለዚህ መፈረም አያስፈልገኝም” አሉኝ፡፡ ኢ/ር ሃይሉ ደግሞ “እኔ ታምሜያለሁ” ብለው ከስብሰባውም ቀርተው ነበር፡፡ በኋላ ኢ/ር ሃይሉ ሽማግሌ ይላክባቸውና ይለመኑ ተባለ፡፡ ከእስረኞቹ መካከል ሶስት ሰዎች ተላከባቸው፡፡ ወደሳቸው የተላኩት ሰዎች እዚያው ቁጭ ብለን ይዘዋቸው መጡ፡፡ በኋላ መጠነኛ የጋራ ስብሰባ አድርገን እንፈርማለን ብለው ተስማሙ:: ለዚህ እውነቱን ለመናገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት ጠበቃው አቶ ታምሩ ናቸው፡፡ ብዙ ሰው ይሄን አያውቅም፡፡ በኋላ የፊርማ ስነስርአቱ ይከናወን ተባለና ፊርማውን ኢ/ር ሃይሉ እና ወ/ት ብርቱካን ይፈርሙ ተባሉ፡፡ ሁለቱ ከፊት ለፊት ተቀምጠው፣ እኛ በታዛቢነት ተቀምጠን ነበር፡፡
ኢ/ር ሃይሉ “ፕ/ር ኤፍሬም ወዲህ ና” አሉኝ፡፡ እኔም በአክብሮት ወዳሉበት መቀመጫ ሄድኩ፡፡
እሣቸውም፣ በማረሚያ ቤቱ በእንጨት የተሠራ፣ የአክሱም ሃውልትና የላሊበላ ቅርጽ “ስለደከምክ ስለለፋህ” ብለው ስጦታ ሰጡኝ፡፡ ለአቶ ታምሩም ስጦታ ተበረከተላቸው፡፡ ያቺ ስጦታ አሁንም አለች:: በኋላ በቃ ሁሉም እየተነሳ ተራ በተራ ፊርማውን አኖረ፡፡
“ከመንግስት ጋር ተሻርካችሁ የሽምግልና ባህልን ጭምር አበላሽታችኋል” የሚሉ ወቀሳዎች ግን ይቀርብቡባችሁ ነበር፡፡ ምናልባት በወቅቱ የሠራችሁት ስህተት ይኖር ይሆን? አሁን ሲያስቡት በሂደቱ የሚቆጭዎት ጉዳይ አለ?
አንድም የተሠራ ስህተትም ሆነ የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ እኔ አንድ ነገር ከተናገርኩ አልክድም:: ፈጣሪዬን የማምንና የማከብር፣ የምፈራ ሰው ነኝ:: የፈረሙት ራሣቸው ፈቅደው በእጃቸው ነው:: እኔ በግድ እጃቸውን ይዤ አላስፈረምኳቸውም:: እንዲህ ያለ ጥርጣሬ ካለባቸው፣ ለምን ፈረሙ? የእነሱም ጭንቀት ይገባኛል፤ እንዲህ አድረግናል ብለው መፈረማቸው ምቾት እንደማይሰጥ እረዳለሁ:: ግን አሻፈረኝ ብለው በአቋማቸው መጽናትን ማንም አልከለከላቸውም፡፡ እኔ ከሁለቱም ወገን እየተቀበልኩ መልዕክት ከማመላለስ በቀር ያስገደድኩት ነገር የለም፡፡ በሀገራችን ባህል ዋናው እርቁ ነው፤ ዋሽቶም ማስታረቅ ይቻላል የሚለውን አልተቀበልኩም፤ በእውነት በሀቅ ነው ያስታረቅሁት፤ ዋሽቼ እንኳ አላስታረቅሁም፡፡
እኔና እግዚሃር መካከል ያለውን እግዚሃር ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እኔ ለሀገራችን ሠላም ነው የለፋሁት፡፡ የኔ ችግር ፖለቲከኞቹ አይደሉም፤ የኔ ችግር ድሃው ህዝብ፣ የታመመው ህዝብ  የተቸገረው ወገኔ ሠላም ማጣቱ፣ በፖለቲካ ምክንያት መሞቱ ነው፡፡ እኔ ጥረት ሳደርግ የነበረው ማናቸውንም አይቼ ሳይሆን ደጉንና የዋሁን የኢትዮጵያ ህዝብ አይቼ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ የሚነፉትን ጥሩንባ ድሃው ገበሬ እኮ አያውቅም፡፡ ነገር ግን እኛ የምንዘፍን ያለነው በየዋሁ ደም ላይ ነው፡፡ ይሄን እግዚብሔርም ይፈርድብናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት ይማር፣ ከበሽታ ይዳን፣ ከድህነት ይውጣ በሚል ነበር ከልጅነቴ ጀምሮ ስጣጣር የነበረው፡፡ በፊደል ሰራዊት ስራዬ የምኮራው ለዚህ ነው፡፡ 2.5 ሚሊዮን ዜጋ ነው ያስተማርነው፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ጽ/ቤት ከፍተን ነበር በዘመቻ ያስተማርነው፡፡ አሁን እኮ የውጭ ሀገር ትምህርት ተምረን ነው አንጐላችን ተሳክሮ፣ ተመርዞ፣ ህዝቡ ላይ ችግር የምንፈጥረው:: እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ግሩም ህዝብ ነው፡፡ እኔ እጄን ታጥቤ ሁሉን እተዋለሁ እልና ህዝቡን ሳስብ ስቃዩ መከራው ያሳዝነኛል፡፡ እኛ ፖለቲከኞቹ ውስኪ እየጠጣን፣ የፈለግነውን እየተናገርን፣ እሱ ሲብሰለሰል እኛ እንደምንጨፍር አያውቅም፡፡ እኛን የጐዳን ልሂቅ ነኝ የሚለው አካል ከህዝቡ ባህል፣ ወግና ልማድ ያፈነገጠ፣ የአውቅልሃለሁ ባይነት ነው፡፡ ያደረጉትን ነገር በዚህ መልኩ መካድም ምንጩ ይሄው ነው፡፡ አንዳንዶቹን እኮ እግራቸው ላይ ሁሉ ወድቄያለሁ:: እውነቱን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ዳኛው እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞ በኢትዮጵያ ባህል ይቅርታ መጠየቅ ያስከብራል እንጂ አያሳፍርም:: እኔ እንደውም አንዳንዴ ባላደረግሁት ነገርም ይቅርታ ጠይቄ እደሰታለሁ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ፤ ደስታን የውስጥ ሠላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ አሁን እነሱንም በወቅቱ አጥፍቼ እንደሆነ፣ ከልብ ይቅርታ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ክብር ነው፡፡
በአንድ ወቅት ለአቶ ኢሳያስም ለአቶ መለስም፤ “ወታደሮች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጉ” ብዬ ደብዳቤ ጽፌላቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን አላደረጉትም:: ቢያደርጉት ኖሮ ትልቁ ጀግንነት እሱ ነበር፡፡ መሠንዘርማ ሁሉም ያደርገዋል፡፡ እሱ ጀግንነት አይደለም፡፡ ይቅርታ መጠየቅም እንደዚሁ ነው፤ ጀግንነት!!
አሁን ያለውን የሀገራችንን እርቅና ሽምግልና እንዴት ያዩታል?
ትልቁ ችግር ቅጥ ያጣ የስልጣን ፍላጐት ነው:: እንዴት ይሄን ገደብ የለሽ ፍላጐት፤ ከፖለቲከኞች አዕምሮ አጥበን እናወጣለን የሚለው ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡ እንዴት ማገልገል የሚለው በልባቸው ይታተም ነው ትልቁ ጭንቀት፡፡
የኛ ፖለቲከኞችም ራስ ወዳድ ናቸው፡፡ የድሃው ደም ምናቸውም አይደለም፡፡ ፖለቲከኞቻችን ይህቺ ሀገር እንድትለወጥ ከፈለጉ፣ በመጀመሪያ ትዕቢት ይተው፡፡ እብሪትና ትዕቢት ምንጩ ራስ ወዳድነት ነው፡፡  

Read 3409 times