Monday, 24 June 2019 00:00

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ ላይ የቀረበ ሒሳዊ አስተያየት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

 “--በእርግጥ እጓለ ይሄንን ሐሳብ ያመጣው፣ ሀገር በቀሉን ትምህርት ትቶ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓውያን ትምህርት ብቻ የመወሰዱን አካሄድ መታረም እንዳለበት ለማሳሰብ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ እጓለ እዚህ ጋ ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡--”
                     
               በክፍል-3 ፅሁፌ፣ እጓለ ከዘረዘራቸው አምስት የሥልጣኔ መሪ አኃዞች ውስጥ የአውሮፓ ሥልጣኔ ሁሉንም የሚያሟላ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ግን አንዱ (የተጠቃሚነት እሴት (ቴክኖሎጂ)) እንደሚጎለው እጓለን በመጥቀስ ተመልክተናል:: ሐሳባችንን የቋጨነውም፣ የያሬዳዊውን ሥልጣኔ ጉድለት እጓለ ለማስረዳት የሄደበት መንገድ ላይ አምስት ሒሳዊ አስተያየቶችን በማንሳት ነበር፡፡
በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› እንደ መፍትሔ የቀረበበት ወቅት ትክክለኛ ነበር ወይ? ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ውስጥ ምንና ምንድን ናቸው የሚዋኻዱት? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ እናፈላልጋለን፡፡
‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› - የረፈደ ሐሳብ
እጓለ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ውስጥ ትልቅ ትኩረትና ጥንቃቄ ሰጥቶ የሚያወራው የአውሮፓ ትምህርት እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ፣ ከያሬዳዊው ሥልጣኔ (እምነት) ጋር እንደሚዋኻድ ነው፡፡ የውህደቱን አፈፃፀም ሲናገርም ሁለት ነገሮችን ያስቀምጣል፡፡
የመጀመሪያው፣ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ ይሄንንም ቅድመ ዝግጅት ‹‹በመጀመሪያ የገዛ ራሳችንን በደንብ አላምጦ መዋጥ›› (ገፅ 79) በማለት ይጠቅሰዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ከውጭ የመጣውን የእኛኑ ባላመጥንበት መንገድ አሳልፎ መደባለቀና ማዋሃድ ነው (ገፅ 79)፡፡ የውጭውን ከእኛ ጋር የምናዋህድበት መንገድ ደግሞ ልክ የሌላ ዛፍ ቅርንጫፍ የዘይትነት ባህሪ ካለው ግን ጋር እንደሚቀጠል አድርገን ነው መሆን ያለበት (ገፅ 79)::
ሆኖም ግን፣ እነዚህ የእጓለ ሐሳቦች የረፈደባቸው ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም፣ እጓለ ይሄንን ሐሳብ በሚያቀርብበት ወቅት (1954-5 የመፈንቅለ መንግስቱ ማግስት) የሀገራችንን ጥንታዊ ትምህርት በመግፋት የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት፣ የ50 ዓመታት ዕድሜ አስቆጥሯል፤ እጓለም በግልፅ እንዳመነው (ገፅ 58)፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፤ ባህላዊ ተቋማትን በመሻር በርካታ ዘመናዊ ተቋማት ተተክለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሀገራቸውን ነባሩን ትምህርት የማያውቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለዘመናዊ ትምህርት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ተልከዋል፤ በርካቶችም ተምረው መጥተው ከትውፊታዊው እሴት ጋር መጣላት ጀምረዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ፣ እጓለ የ‹‹በተዋህዶ ከበረ››ን ሐሳብ በሚያቀርብበት ወቅት የትውልድ ክፍተት መታየት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
በእርግጥ እጓለ ይሄንን ሐሳብ ያመጣው፣ ሀገር በቀሉን ትምህርት ትቶ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓውያን ትምህርት ብቻ የመወሰዱን አካሄድ መታረም እንዳለበት ለማሳሰብ ነው (ገፅ 58)፡፡ ሆኖም ግን፣ እጓለ እዚህ ጋ ግራ የተጋባ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል፣ ‹‹የአውሮፓ ሥልጣኔ በንፁህ የህሊና ጥረት (Pure Reason) የተገኘና የጠቅላላው የሰው መንፈስ ህግ ስለሆነ በሁሉም ህዝቦች ዘንድ የሚፀና ነው፤ እስያውያንና አፍሪካውያንም በትምህርት የራሳቸው ንብረት ሊያደርጓቸው ይችላሉ›› (ገፅ 58) በማለት የአውሮፓውያንን ዕውቀት ሁለንተናዊ (Universal) ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ‹‹የአውሮፓውያንን ትምህርት እንደወረደ መቀበል የለብንም›› ይላል (ገፅ 58፣ 78-83)፡፡
‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ውስጥ ምንና ምንድን ናቸው የሚዋኻዱት?
እጓለ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› የሚለውን ፍልስፍናዊ ፕሮጀክት ያመጣው፣ የያሬዳዊውን ሥልጣኔና የአውሮፓን ሥልጣኔ ለማዋኻድ እንደሆነ ቢነግረንም፣ ከሁለቱ ሥልጣኔዎች የትኛው ክፍላቸው ነው የሚዋኻደው? ለሚለው ጥያቄ የተገላለጠና የተተነተነ መልስ አላቀረበልንም፡፡
እጓለ የነገረን ቢኖር፣ የአውሮፓ ሥልጣኔ በህሊና መንገድ እንደተገኘና፣ ያሬዳዊው ሥልጣኔ ደግሞ በመንፈስ ልዕልና የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ነገር፣ ምናልባት እጓለ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሲል ሊያዋህድ የፈለገው ሁለቱ ሥልጣኔዎች የተመሰረቱበትን አምዶች ሊሆን ይችላል - ህሊናንና መንፈስን፣ አመክንዮንና እምነትን፣ ፍልስፍናንና ሃይማኖትን፡፡
የ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ሐሳብ ይሄ ከሆነ ‹‹የአዲስነት (Originality)›› ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ምክንያቱም ህሊናንና መንፈስን፣ አመክንዮንና እምነትን የማስታረቅ፣ በ3ኛውና በ4ኛው ክ/ዘመን  በክርስትያን ፈላስፎችና የሃይማኖቱ ልሂቃን ሲካሄድ ነበር፡፡ እጓለ የፍልስፍናና የሃይማኖት ሰው ስለሆነ ይሄንን ታሪክ በደንብ ያውቀዋል፡፡
ህሊናንና መንፈስን፣ አመክንዮንና እምነትን፣ ፍልስፍናንና ክርስትናን ማስታረቅ ይቻላል? ወይስ አይቻልም? በሚለው ጥንታዊ ጥያቄ ላይ፣ በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዘመነ ሊቃውንት ጊዜ የነበሩ የመጀመሪያዎቹ አባቶች (ለምሳሌ፡- ኦሪገን፣ ቅሌመንጦስና ኦገስቲን) ለጥያቄው አዎንታዊ መልስ በመስጠት አመክንዮንና እምነትን፣ ፍልስፍናን ናክርስትናን በማስታረቅ ይጓዙ ነበር፡፡
በተቃራኒው፣ አንዳንድ አባቶች ግን (ለምሳሌ፡- ተርቱሊያንና አትናቲዎስ) የሁለቱን ጥምረት አጥብቆ በመኮነን ‹‹እየሩሳሌም ከአቴንስ ጋር፣ መፅሐፍ ቅዱስ ከሪፐብሊክ መፅሐፍ ጋር፣ ቤተ ክርስቲያን ከአካዳሚ ጋር፣ ክርስትያን ከመናፍቃን ጋርም ህብረት አላቸው?!›› የሚል ትምህርት ይዘው ተነሱ፡፡
ካቶሊካውያን የመጀመሪያውን (የእነ ኦገስቲንን) መንገድ ሲከተሉ፣ የምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ደግሞ (ኢትዮጵያን ጨምሮ) የእነ አትናቲዎስን ትምህርት ተከትለው ሄዱ፡፡ በዚህም የተነሳ በሀገራችን ጥንታዊ ትምህርት ውስጥ የህሊና፣ የአመክንዮና የፍልስፍና መንገድ ስፍራ የሌለው ሆነ፡፡ እንግዲህ፣ የረጅም ጊዜ ታሪካችን በእንደዚህ ዓይነት የህሊናና የመንፈስ ተቃርኖ ውስጥ የኖረ ሆኖ እያለ ነው፣ እጓለ ህሊናንና መንፈስን፣ አመክንዮንና እምነትን፣ ፍልስፍናንና ሃይማኖትን ከ 1600 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ለማስታረቅ የተነሳው፡፡
እጓለ ይሄንን ሐሳብ ከ 1600 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲያነሳው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የጥንት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የእነ አትናቲዎስን መንገድ መከተላቸው ስህተት የነበረ መሆኑን በማመን ሲሆን፤ ውይይቱንም በድጋሚ ማንሳት ያስፈለገው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነውን የእነ አትናቴዎስን ውሳኔ አሁን ላይ ለማረም ይመስላል፡፡
ሆኖም ግን፣ እጓለ ይሄንን ሙግት በድጋሚ ለውይይት ሲያመጣው ሁለት ነገሮችን ማድረግ ነበረበት፡፡ የመጀመሪያው፣ የጥንቱን ሙግት ታሪካዊ ሂደቱን መዳሰስ ነበረበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ፣ የእሱ ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ከቀደምቶቹ ሐሳብ በምን እንደሚለይ ሊነግረን ይገባ ነበር፡፡
ምናልባት፣ ‹‹እጓለ ይሄንን ለምን አላደረገም?›› የሚል ጥያቄ ከተነሳ ሁለት መላምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውና የዋሁ መላምት፣ እጓለ ይሄንን ያላደረገው የእሱ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ በእነ አትናቲዎስ ዘመን ከተነሳው ሙግት ጋር ያለውን የመንፈስ ዝምድና ስላላጤነው ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው መላምት ደግሞ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለው ሐሳብ በእነ አትናቲዎስ ዘመን የነበረው ሙግት ቅጥያ እንደሆነ በግልፅ ቢፅፍ ኖሮ፣ ‹‹መንፍቋል››፣ ‹‹ኮትልኳል›› በሚል የተለመደ ፍረጃ መገለልና መወገዝ እንዳይደርስበት ፈርቶ ሊሆን ይችላል፡፡
በክፍል-5 እና በማጠቃለያ ፅሁፌ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፖለቲካዊ ወይስ ፍልስፍናዊ መፍትሔ? የሐሳቡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንደምታዎቹስ ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች እንዳስሳለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 9199 times