Tuesday, 25 June 2019 00:00

የኪሳራ ወዶ ገብ! ለዚያውም ኪሳራው በዶላር ነው!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


- 4,000 GHW ኤሌክትሪክ ለጎረቤት አገራት በመሸጥ፣ 220 ሚ. ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: ወደፊትም በዚሁ ሂሳብ እንዲቀጥል የስምምነት ውል ተፈርሟል፡፡ ጥሩ ነው፡፡
- ለመግዛትስ? በየዓመቱ 4,000 GHW ከውጭ ኩባንያ በ300 ሚ. ዶላር ወጪ ለመግዛት የተዘጋጀ የስምምነት ውል ላይ፣ ካቢኔው ዛሬ ይወስናል? የኢትዮጵያ መንግስት አይኑ እያየ ይገባበታል?
- ትርፉ ምንድነው? ምንም ትርፍ የለውም:: በ7.5 ሳንቲም ሂሳብ ገዘቶ በ5.6 ሳንቲም መሸጥ እርቃኑ በግላጭ የሚታይ ኪሳራ ነው፡፡ ወጪና ገቢ አቀናንሶ ማየት ብቻ ይበቃል! ወደ ሰባት ሳንቲም ቢሻሻል፣ ወደ ስድስት ሳንቲም ቢወርድ እንኳ አያዋጣም::
- ተራ የስምምነት ውል አይደለም፡፡ ዘንድሮ ተፈርሞ፣ ከዓመት በኋላ “አላዋጣኝም” ተብሎ የሚሰረዝና የሚያበቃለት አይደለም፡፡ ለ20 ዓታመት ሳይቋረጥ የሚቀጥል ውል ነው፡፡
- እንደተለመደው፣ መንግስት ዛሬ ተስማምቶ፣ ነገ ሃሳቡን ቢቀይር እንዳሻው የሚሽረው ውል አይደለም፡፡ አለማቀፍ ውል ነው፡፡ አንዴ ተፈርሞ ከፀደቀ፣ መንግስት መፈናፈኛ አይኖረውም፡፡ የተዋዋለውን ካልፈፀመ፣ በአለማቀፍ የዳኝነት ችሎት ይከሰሳል፡፡ ይፈረድበታል:: በውሉ መሰረት እንዲከፍል ይገደዳል፡፡ ካሳ ከነወለዱም ይጨመርበታል፡


           ከገበያው በላይ በውድ ዋጋ፣ ከኡጋንዳ ኩባንያ ቡና ገዝቶ፣ በቅናሽ ዋጋ ወደ አውሮፓ ለመሸጥ እንደመስማማት ነው  - ነገሩ፡፡ ለዚያውም የትራንስፖርት ወጪውንም “በኢትዮጵያ ላይ ጣለው” የሚል፣ ተጨማሪ የኪሳራና የስካር ሀሳብም የያዘ ነው ውሉ፡፡ ለጂኦተርማል ፕሮጀክት የተዘጋጀው ውል፣ ከዚህም የከፋ ነው:: “transmission loss” ይታከልበታል፡፡
ኢትዮጵያ፣ የዚህን ያህል የተሳከረ ትብታብ ውስጥ ለመግባትና፣ መውጫ በሌለው ውል ለመታሰር፣ የገደል አፋፍ ላይ ደርሳለች፡። ወደ ህሊና ሳይመለሱ፣ አፋፍ ደርሰው ገደል የገቡ አገራት ጥቂት አይደሉም፡፡ ውል ተፈራርመው፤ አለማቀፍ ውል በመሆኑም በካቢኔና በፓርላማ አፅድቀው ሲያበቁ፣ ብዙም ሳይቆይ የቆጫቸው፣ ኪሳራውና እዳው የቆጠቆጣቸው አገራት ብዙ ናቸው፡፡
በአፍሪካ፣ በአውሮፓም ጭምር፣ ወደው በድርድር ከገቡበት ጣጣ፣ እንደዋዛ በግርግር ለመውጣት የሚሞክሩ፣ በብልጣብልጥነት ከመዘዙ ለማምለጥ የሚፍጨረጨሩ፣ ኪሳራውን ላለመሸከም፣ ክፍያውን ላለመፈፀም የሚያንገራግሩ፣ ጭርሱን እያመረሩ፣ ያፀደቁትን ውል የሻሩ ሞልተዋል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ምንድነው? በተለይ በአፍሪካ ምድር፣ የአህጉሪቱ መንግስታት፣ አክሳሪ ፕሮጀክቶችን እየተቀበሉ የስምምነት ውል እንዲፈርሙ፣ ከቀድሞው የዩኤን ዋና ፀሐፊ ከባንኪ ሙን ጋር፣ በፊታውራሪነት ሰፊ ዘመቻ ያካሄዱት ባራክ ኦባማ ናቸው - Power Africa በሚል ስያሜ፡፡
የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ወይም የሌላ አገር ኩባንያዎች፣ በአፍሪካ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንዲገነቡ እንደሚያበረታቱ የገለፁት ባራክ ኦባማ፣ ለዚህም የአሜሪካ መንግስት ለኩባንያዎች ብድር በመስጠት ይደግፋል በማለት ነው ዘመቻውን የጀመሩት፡፡
በእርግጥ፣ በአፍሪካም ይሁን በአሜሪካ፣ … የመንግስት እጅ የገባበት የቢዝነስ ፕሮጀክት፣ ውሎ አድሮ ከችግር፣ ዞሮ ዞሮ ከመዘዝ ባያመልጥም፣ የግል ኢንቨስትመንት በመንግስት ጣልቃ ገብነት ተበርዞም ቢሆን፣ ይብዛም ይነስ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አይካድም፡፡ በተለይ በአፍሪካ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የተጠማችና በኢንዱስትሪ እጦት የኋሊት የቀረች ድሃ አህጉር ውስጥ፣ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚሰማሩ ኩባንያዎች ከተገኙ፣ የግል ኢንቨስትመንት ከመጣ፣ እሰየው ነው ሊባል ይችላል፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? ለአክሳሪ ፕሮጀክት ብቻ ነው፣ የብድር ድጋፍ የተፈቀደው፡፡ የመንግስት ነገር!
የኤሌክትሪክ ማመንጫ ለመገንባት የሚፈልግ ኢንቨስተር ወይም ኩባንያ፣ ገንዘቡን ለግንባታ ከማዋሉ በፊት፣ ስኬታማና አትራፊ እንደሚሆንለት ጠንቅቆ ማሰብ፣ አስልቶ ማረጋገጥ አለበት፡፡ በአነስተኛ ወጪ፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ካልቻለ፣ ተጨማሪ ሃብት ሊያገኝ ይቅርና የነበረውንም ሀብት ያጣል፡፡ የግንባታና የእለት ተእለት ወጪው ዝቅተኛ፣ የሚያመነጨው ኤሌክትሪክ ደግሞ አስተማማኝና እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡
በናፍጣ የሚሰራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ አስተማማኝ ነው፡፡ በተፈለገው ሰዓት በሙሉ አቅሙ ለመስራት በቂ ነዳጅ አጠራቅሞ መጠበቅ ይችላል፡፡ ሁነኛ መጠባበቂያ የሚሆንልንም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የእለት ተእለት ወጪው ግን፣ ቀላል አይደለም፡፡ የነዳጅ ወጪ ከባድ ነው፡።
በነፋስ ተርባይን ወይም በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ደግሞ፣ ሌሎች የባሱ ችግሮች አሉበት፡፡ የግንባታ ወጪው ቀላል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ፣ በተፈለገው ሰዓት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያገለግል፣ ተጠራቅሞ የሚጠብቅ “ነፋስ” ወይም “ፀሐይ” የለም፡፡ ለዚህም ነው፤ በኢትዮጵያ፣ የነፋስ ተርባይኖችን ለመትከል ከዋለው 770 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ግማሹ በከንቱ የባከነ፣ ለነፋስ የተበተነ የድሃ አገር ሃብት ሆኖ የጠፋው፡፡
በከርሰ ምድር እንፋሎት የሚሰራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ደግሞ፣ የግንባታ ወጪው አይቀመስም፡፡ በዚያ ላይ ለተደጋጋሚ ብልሽት የተጋለጠ ስለሆነ ለከፍተኛ የጥገና ወጪ ይዳርጋል፡፡
በሌላ አነጋገር፣ በተለይ በአፍሪካ፣ በሌሎች አገራትም እንደታየው፣ ተመራጮቹ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ የውሃ ግድብ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በከሰል ድንጋይ የሚሰሩ ማመንጫዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር ሲነፃፀሩ፣ … በፀሐይ እና በነፋስ፣ እንዲሁም በከርሰ ምድር እንፋሎት የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች አክሳሪ ናቸው፡፡
አሳዛኙ ነገር፣ የአፍሪካ መንግስታት አክሳሪዎቹን ፕሮጀክቶች ተቀብለው ውል እንዲፈራረሙ ያደረገ ነው የባራክ ኦባማ ዘመቻ:: ኢትዮጵያም እንዲሁ ውል ፈርማ ለማፅደቅ፣ አፋፍ ላይ ደርሳለች - የኪሳራ ወዶ ገብ ለመሆን::   
ከአውሮፓ ኩባንያ፣ በየዓመቱ 4ሺህ GWH የኤሌክትሪክ ኃይል በ300 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ነው፣ ውል የተዘጋጀው:: ከዚያስ? ያንኑን ለጎረቤት አገራት፣ ለነ ኬንያ በ220 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ! በሌላ አነጋገር፣ በፈቃደኝነት፣ በየዓመቱ፣ 80 ሚሊዮን ዶላር ለመክሰር! በየዓመቱ፣ ለአውሮፓ ኩባንያ የ80 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ለመስጠት፣ በገዛ እጅ ለ20 ዓመታት የሚቀጥል እዳ ለመሸከም፡፡
ኪሳራው ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር እስከ ኬንያ ድንበር ድረስ የተዘረጋው፣ በ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ነው - “ትርፍ ያስገኛል” ተብሎ፡፡ ኤሌክትሪክ ወደ ኬንያ ለመሸጥና፣ “የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት ይጠቅማል”፣ “የዶላር እጥረትን ለማቃለል ያገለግላል” ተብሎ ነው፣ የኤሌክትሪክ መስመር የተዘረጋው፣ … አገሪቱም የ500 ሚሊዮን ዶላር እዳ ውስጥ የገባችው፡፡ አሁን እዳ ብቻ ሆኖ ሊቀር ነው? (የ15 ቢሊዮን ብር እዳ!)፡፡
እንዲህ ዓይነት የተሳከረ የኪሳራ ውል፣ ፈፅሞ እንደማያዋጣና እንደማያዛልቅ እየታወቀ፣ እንዴት ነው የስምምነት ውል ተዘጋጅቶለት፣ ተፈርሞ፣ እንዲፀድቅ ወደ ሚኒስትሮች ካቢኔ ለመድረስ የበቃው?
ግን፣ በሌሎች የአፍሪካ አገራትም፣ ተመሳሳይ የኪሳራ ውሎች ተፈርመው፣ በመንግስታት ፀድቀዋል፡፡ የሚያዛልቁ አልሆኑም፡፡ ለዚህም ነው፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግስታት፣ በቃል ተስማምተው፣ ውል ላለመፈረም የሚያንገራግሩት፡፡ ውል የፈረሙም፣ በይፋ ላለማፅደቅ የወሰኑት፡፡ ውል ያፀደቁ መንግስታትም፣ በተግባር ላለመፈፀምና ውል ለማፍረስ የሚፍጨረጨሩት፡፡ የፓወር አፍሪካ ዋና ኃላፊ፣ ይህንን አልካዱም፡፡ የአፍሪካ መንግስታት ውል የማያከብሩና የሚያፈርሱ ሆነዋል በማለት የተናገሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የምስራቅ አውሮፓ አገራትም፣ የተፈራረሙትን ውል ላለመፈፀም ከማንገራገር አልፈው፣ አምርረው ውል እስከማፍረስ እየደረሱ መሆናቸውን፣ ዘ ኢኮኖሚስት መፅሔት በጁን 8 እትሙ ዘግቧል፡፡
ታዲያ፣ እንዲህ ዓይነት ውል፣ እንደ ዘበት የሚሽሩት፣ የሚሰርዙት አይደለም፡፡ አለማቀፍ ውል ስለሆነ፣ ‹ተሰረዘ›፣ ‹ተቋረጠ› ተብሎ በዚያው ተረሳስቶ አይቀርም፡፡ ፖላንድ ውስጥ በ580 ሚሊዮን ዶላር የነፋስ ተርባይኖችን ለመትከል ተስማምቶ ስራ የጀመረ ኩባንያ፣ የስምምነት ውል በመንግስት ተቋረጠብኝ ብሎ ዝም አላለም፡፡ በአለማቀፍ የዳኝነት ችሎት፣ የ700 ሚሊዮን ዶላር ክስ መስርቷል፡፡ ችሎቱ በፖላንድ መንግስት ላይ ከፈረደበት፣ ማምለጫ ቀዳዳ አይኖረውም - የተፈረደበትን ይከፍላል፡፡
ለኢትዮጵያ የተዘጋጀላት የጂኦተርማል ውል ከዚህ የከፋ ነው፡፡ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ፕሮጀክት ላይ፣ የውል ስምምነት ከተፋረሰ፣ ለቢሊዮን ዶላሮች ክስ፣ ለፍርድና ለእዳ ይዳርጋል፡፡ በቅርቡ፣ ጅቡቲ ውል ጥሳለች ተብላ የተወሰነውን ፍርድ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡
ታዲያ፣ እንዲህ ዓይነት መዘዝ ውስጥ በገዛ እጁ መግባት ያዋጣል?

Read 8378 times