Saturday, 22 June 2019 15:21

ኢዜማ፤ በትግራይ የተከለከለው ህዝባዊ ስብሰባ ተፈቀደለት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

•    ከክልሉ አስተዳደር ጋር ውይይት ለማድረግም አቅዷል

ኢዜማ፤ "ህጋዊ እውቅና የለህም" በሚል በትግራይ ክልል የተከለከለው ህዝባዊ ስብሰባና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንደተፈቀደለት አስታወቀ፡፡ ባለፈው እሁድ ሰኔ 8 ፣ በኢዜማ ም/መሪ አቶ አንዷለም አራጌ የሚመራ ቡድን፣ በትግራይ ክልል ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድና ከክልሉ አስተዳደር ጋር ለመወያየት የያዘው ዕቅድ፣ "ህጋዊ ፍቃድ  የላችሁም" በሚል በመቐሌ ከተማ አስተዳደር ተከልክሎ የነበረ ሲሆን፣ በሳምንቱ መጨረሻ ግን ስብሰባውን በመጪው እሁድ ሰኔ 23 እንዲያደርግ ፈቃድ ማግኘቱን  ለአዲስ አድማስ ገልጧል፡፡  
ህዝባዊ ስብሰባው መከልከሉን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ፣ ፓርቲው በመላው አገሪቱ  የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚችል የሚገልጽ ድጋፍ ከምርጫ ቦርድ ለክልሉ መንግስት ማጻፉን የጠቆመው ኢዜማ፤በአጭር ቀናት ውስጥ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በጋምቤላና ሱማሌ ክልል፣ ህዝባዊ ውይይቶች በተሳካ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑንና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም  መሠረቱን የማስፋት እንቅስቃሴ ያለ ብዙ ችግር እያደረገ እንደሚገኝ ፓርቲው አመልክቷል፡፡ ኢዜማ፤ በ2012 በሚደረገው አገራዊ  ምርጫ ላይ ለመወዳደር የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለፁት የፓርቲው ሃላፊዎች፤ በአሁኑ ወቅት፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 360 የምርጫ ወረዳዎች ጽ/ቤቶቹን ማደራጀቱን አስታውቀዋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል በሚል ታሣቢ ፓርቲው  መጠነ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁሞ፤ በቀጣይም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ውይይቶችን ለማካሄድ እቅድ መንደፉን አስታውቋል፤ፓርቲው፡፡  ይህ በዚህ እንዳለ፤ የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ያደረጉትን ጉብኝትና የደጋፊዎች ውይይት አጠናቀው ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሜሪካ ሶስት ከተሞች ከደጋፊዎች ጋር የተገናኙት መሪዎቹ፤ የፓርቲውን አላማና የአላማ ማስፈፀሚያ ስልቶች ማስተዋወቃቸውንና ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታ ማስረዳታቸውን ፓርቲው ጠቁሟል፡፡ ጐን ለጐንም፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፓርቲው እንቅስቃሴ መሳተፍ የሚችሉበትን የደጋፊዎች ቻርተር ለማቋቋም ጥረት መደረጉን የገለጸው ኢዜማ፤ በሶስቱ ከተሞች በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 50ሺህ ዶላር መገኘቱን አስታውቋል፡፡

Read 13666 times