Tuesday, 02 July 2019 11:29

የአሀዱ ሬዲዮ ጣቢያን ክስ የበኬ ወረዳ ፍ/ቤት ሊዳኝ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)


     በኦሮሚያ ክልል የሰንዳፋ ከተማ በኬ ወረዳ ፍ/ቤት፣ በአሀዱ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የቀረበውን ክስ ሊዳኝ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ ጉዳዩ መታየት ያለበት የሬዲዮ ጣቢያው በሚገኝበት የፌደራል ከተማ ፍ/ቤቶች ነው በሚል ተከሳሾቹ ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍ/ቤቱ ውድቅ አድርጐታል፡፡
ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተፈፀመውን የመልካም አስተዳደር ችግርና ህገወጥ የሙስና ተግባር የተመለከተ ዘገባ በሬዲዮ ጣቢያው መሰራጨቱ፣ “የስም ማጥፋት ወንጀል ፈጽሞብናል” ያለው ፍ/ቤቱ፤ በሬዲዮ ጣቢያው ዋና ስራ አስኪያጁ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሊዲያ አበበ፣ በዜና ክፍል ኃላፊው ጋዜጠኛ ሱራፌል ዘለዓለም እንዲሁም ዘገባውን በሰራው ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ላይ ላይ ክስ መስርቷል፡፡ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ለፍ/ቤቱ መቃወሚያቸውን ቢያስገቡም ፍ/ቤቱ መቃወሚያቸውን ውድቅ አድርጐ፣ የወረዳው ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ስልጣን አለው ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹም ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ እንዲሰጡ ለሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው የነበሩት አራቱ ተከሳሾች፣ ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ ሬዲዮ ጣቢያው የሚገኘው በፌደራሉ ዋና ከተማ ውስጥ በመሆኑና ዘገባው የተሰራጨውም በዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ ስለሆነ ጉዳዩ መታየት ያለበት በፌደራሉ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ፍ/ቤቶች ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የብሮድካስት ባለስልጣን ስለ ጉዳዩ አንዳችም መረጃ ባላገኘበትና እኛም ስለ ዘገባው በዚሁ ባለስልጣን መ/ቤት በኩል የደረሰን ምንም አይነት ቅሬታና ማሳሰቢያ ሳይኖር ጉዳዩን ማየት በማይችል ፍ/ቤት በኩል ክስ ሊመሰረትብን አይገባም ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዘገባው ስሜ ጠፍቷል የሚለው ፍ/ቤቱ ስለሆነና ፍ/ቤቱ ራሱ ከሳሽ በሆነበት ጉዳይ ፈራጅም ሊሆን ስለማይገባ ክሳችን በሌላ ፍ/ቤት ሊቀርብና ፍትህ ልናገኝ ይገባል የሚል መቃወሚያ ለፍ/ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጐ፣ ጉዳዩ በወረዳው ፍ/ቤት ሊታይ ይችላል የሚል ብይን በመስጠቱ ተከሳሾቹ በሃያ ሺ ብር ዋስትና እንዲለቀቁና ለሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ምላሻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ አዟል፡፡
በፍ/ቤቱ ውሣኔ በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና የመረጃ ነፃነት ህጉ በዚህ መጠን እየተጣሰ መሄዱ መጪውን ጊዜ አስፈሪና ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባቸው የጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 856 times