Tuesday, 02 July 2019 11:29

“ለዴሞክራሲና ለሰላም ስንል እንታገሳለን፤ ለሀገርና ለህዝብ ስንል መራር ውሳኔን እንወስናለን”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በባሕርዳርና በአዲስ አበባ በግፍ የተገደሉትን ከፍተኛ አመራሮች በተመለከተ ያስተላለፉት የኅዘን መግለጫ

      የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ በቅድሚያና ከሁሉም በፊት በባሕርዳር እና በአዲስ አበባ በሀገራችን ከፍተኛ የጦርና የሲቪል አመራሮች ላይ በተፈፀመው ሕገ ወጥና ዘግናኝ ፋሺስታዊ ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ ልባዊ ኅዘን በራሴና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም እየገለጽኩ፤ ለሟቾች መንግሥተ ሰማያትን፣ ለቤተሰቦችና ለወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን፣ ለመላው የትግል ጓዶችና ለሥራ ባልደረቦ ብርታትን እመኛለሁ፡፡
አንድ ዓመት ባስቆጠረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞና ጐዳና ላይ እያለን በጓዶቻችን ላይ የተፈፀመውን ጥቃትን ሀገራችንን የገጠማችን ብርቱ ፈተና ስናስብ፣ ልባችን በከፍተኛ ኅዘን የሚደማው ያለምክንያት አይደለም፡፡ እነዚህ ሰማዕታት  እንደ አለት የጸኑ፣ እንደ አልማዝ የጠነከሩ፣ ሀገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የማገልገል ዓላማን ያነገቡ፣ ዓላማቸው ሳያሳኩ አንገታቸውን ላለማዞር የቆረጡ፣ ይህንንም በተግባር የረጋገጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ነበሩ፡፡
ከዚያ በላይ ልብን የሚያደማው እነዚህ ሰማዕታት የለውጡ የምስራች ገብቷቸው፣ የሚገኘውን ሀገራዊ ዋጋ ተረድተው፣ ሌሎቻችንን ሁሉ እነርሱ ወደታያቸው ራእይ ሊወስዱን አቅሙ የነበራቸው ግንባር ቀደም የለውጡ ተላሚዎች መሆናቸውን ስናስብ ነው፡፡ ነገሩ ከምንገምተው ጊዜ የቀደመ፣ ከምናስበውም ውጭ ልብ የሚያደማ ሆነብን እንጂ ሀገርን አንድ ማድረግ፣ ሕዝብንም በሰላምና በዲሞክራሲ ጐዳና መውሰድ ከባድ፣ መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅ ተረድተነው ነበር:: ትግሉ ከሰውነት በታች ከወረዱ፣ ከሥልጣን ውጭ ሌላ ከማይታያቸው፣ ከመግደል ውጭ ሌላ ዕውቀት ካልዞረባቸው፣ ከጉልበት ሌላ መፍትሔ ያለ ከማይመስላቸው፣ ከግል ጥቅም ባሻገር ለማየት ከማይችሉ ጋር እንደሚደረግ ተረድተነው ነበረ፡፡
ይህን እኛም ጠላቶቻችንም እናውቃለን፡፡
ታላቂቱን ሀገር ማሳነስ፣ የተከበረውንም ሕዝብ ማዋረድ፤ ለግሥጋሴያችን ልጓም፣ ለመንገዳችን ዕንቅፋት ማኖር ሞያ የሚመስላቸው እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ከዴሞክራሲ ሕዝብ ያተርፋል፤ እነርሱ ግን ይከሥራሉ፤ ከሥልጣኔ ሕዝብ ይጠቀማል፣ እነርሱ ግን ይጐዳሉ፤ ከኅብረ ብሔራዊነት ሀገር ይበለጽጋል፣ እነርሱ ግን ይደኸያሉ፤ በፍቅርና በይቅርታ ኢትዮጵያ ትታከማለች፣ እነርሱ ግን ይታመማሉ፡፡ ይህ ነው የጠላቶቻችን ትልቁ መለያቸው፡፡
ለሕዝብና ለሀገር ለመሥራት የሚችል ብርቱ ልብ፣ ሰብአዊ አንጀት፣ ጠንካራ ክንድ፣ አርቆ አሳቢ አእምሮ፣ አመዛዛኝ ኅሊና፣ ጠቢብ ልቦና የላቸውም:: አርበኝነታቸው ለአሉባልታና ለሐሜት፣ ጀግንነታቸው ለሴራና ለነገር፣ ጉብዝናቸው ለተንኮልና ለጭካኔ ነው፡፡ በአእምሯቸው ካለው ሐሳብ ይልቅ በወገባቸው ያለው ዝናር፣ በልባቸው ካለው ጥበብ ይልቅ በእጃቸው ያለው ሽጉጥ የሁሉም ነገር መፍትሔ ይመስላቸዋል፡፡
ሐሳቡን ማሸነፍ ሲያቅታቸው፣ አሳቢን ለማጥፋት ተነሱ፤ አእምሮ ሲጐድላቸው ባለ አእምሮውን ለማጨናገፍ ቆረጡ፤ ጥበብ ሲጠፋባቸው ጠቢባኑን ለማስወገድ ፈጠኑ፡፡ ሀገር ወደ ዘመነ አብርሆት ስትጓዝ እነርሱ ተቃራኒውን መረጡ፡፡ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ የተጠላውን የጥፋትን መንገድ ተከተሉ::
ዓላማቸው ሦስት ነገሮችን ማስከተል መሆኑ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ በአንድ በኩል የለውጡን ሐዋርያት በመግደል ለውጡን ማስቆም፣ በሌላ በኩል ሕዝባችንን በተሳሳተ ምስል እርስ በርሱ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ማድረግ፣ በሦስተኛ ደረጃም የፀጥታ አካሎቻችንን ሞራልና ክብር በመንካትና አንድነቱን በጐጥ በመከፋፈል ሀገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነበር፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ለቅዠታቸውና ለእኩይ ተግባራቸው አሳልፎ አልሰጠንም፡፡
ወደፊትም አይሰጠንም፡፡
እነዚያን ጀግኖች እንዲህ በቀላሉ ማጣት እንደ እግር እሳት ይለበልባል፣ እንደ ጐን ውጋት ያስቃስታል፡፡ ኢትዮጵያ እነርሱን ለማግኘት ስንት ደክማለች፣ ስንት ተስላለች፣ ስንት ወጥታ ወርዳለች፤ ይህን በማይረዱ የገዛ ልጆቿ ልጆቿን አጥታለች፡፡ በሀገር እየኖሩ፣ በሀገር እየከበሩ ሀገር በማይገባቸው የልጅ ደመኞች ውድ ልጆቿን ተቀምታለች፡፡ ያን መሰል ሀገርን የካደ ሠንካላ ክፉ ምኞት ሲጀመርም የከሸፈና የተሸነፈ አስተሳሰብ በመሆኑ ሕዝባችን በተለመደ ሀገር ወዳድነትና በጽኑ የዐርበኝነት መንፈስ በእንጭጩ አምክኖታል፡፡ በሀገሩና በወገኖቹ ጥቃት የማይደራደርው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ከአባቶቹ እንደለመደው ከሀገሩ ልጆችና ከጀግኖቹ ጋር በአንድነት በመቆም ክፉውን ሴራ አክሽፎታል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ፖለቲከኞቻችን፤ በአብሮነትና በጽናት በመቆም፣ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሬ ወርቅ ተፈትኖ፣ እንደ ጥሩ ወርቅ ነጥሮ እንደሚወጣ ዳግም ለዓለም አረጋግጠዋል፡፡
ክልሎች በጋራ በመቆም በትብብርና በመደጋገፍ የመኖርን ፋይዳ አልቀው አሳይተዋል፡፡ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፖሊስ ኃይላችንና የፀጥታ አካሎቻችን እዝና ተዋረዳቸውን በላቀ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ጠብቀው ተልዕኳቸውን በከፍተኛ ደረጃ በመወጣት አኩሪ ገድል በመፈፀም፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ እንድንኮራና እንድንመካባቸው አድርገዋል:: በዚህም የተሰማኝን ክብርና ለእነርሱም ያለኘን አድናቆት እየገለጽኩ በዚሁ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በቀጣይነት ይወጡ ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፡-
ሀገር በተስፋና በደስታ ዘመናት ብቻ ሳይሆን በመከራና በችግር ዘመናትም ውስጥ እንደምታልፍ ከታሪክ ብቻ ሳይሆን ከመኖርም የምንረዳው ሐቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሃሳበ ስንኩላን ሲነገራቸው ባይሰሙም፤ ሲመከሩ ባያደምጡም፣ ምሕረትና ይቅርታ ባይገባቸውም፤ የሀገራችን ጠላቶች ደግመው ደጋግመው መገንዘብ የሚኖርባቸው አንድ ዘለዓለማዊ እውነት አለ፡፡ ሀገራችን አእላፋት አዝማናትን አልፋ አሁን ከምትገኝበት የታሪክ ምዕራፍ የደረሰችው ጉዞዋ በፀጥታና በላም ውስጥ ብቻ ስለነበር አይደለም፤ ጨለማውን እየገለጠች፣ ጉድባውን እየተሻገረች፣ ማዕበሉን እያለፈች፣ አቀበቱን እየዳኸች በእሳትና በአውሎ ነፋስ መካከል እየሰነጠቀች በመጓዝ ጭምር ነው፡፡
በየዘመናቱ እኩያን እየተነሱ ከመንገዷ ሊገቷት፣ ከግስጋሤዋ ሊመልሷት፣ ከክብሯ ሊያወርዷት ሲዳዳቸውና ሲውተረተሩ ዝም ብላ ተቀብላ አታውቅም፡፡ እንደገና እየተነሳች፣ እንደገናም እየገሰገሰች፣ እንደገናም ወደ ገናናነቷና ወደ ክብሯ እየተመለሰች ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ እናቶቻችንና አባቶቻችን ትተውልን ያለፉት ቅርሶች ይህንን ሃቅ ደጋግመው ይነግሩናል፡፡
ቀጥና የማትበጠስ፣ ተዳፍና እሷቷ የማይጠፋ፣ ተናግታ የማትፈርስ፣ ተናውጣ ሥሯ የማይበጠስ ሀገር ናት ኢትዮጵያ፣ ሕግ አክባሪ ዜጐቻችን ደግመው ደጋግመው በተለያዩ መድረኮች የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ሲመክሩ በጥሞና አድምጠናል፡፡ መግደል መሸነፍ ነው ስንል፣ የሐሳብና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሉዓላዊ ሐሳብ እንጂ በጥይት እንደማይሸነፍ በመረዳታችን ነበር፡፡
መግደል መሸነፍ ነው፤ እንደ እነርሱ የፀብ ብረት መወልወልና ባሩድ መቀመም ስለማንችልበት አይደለም፡፡ ታላቁ ጀግንነት ፍቅርና ይቅርታ፣ ዕርቅና ሰላም ስለሆነ እንጂ፡፡ መግደልና መገዳደል፣ ጦርነትና ግጭት ምን ዓይነት መቀመቅ ውስጥ ሀገርን እንደሚከት ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚረዳው የለም ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ውረድ እንውረድ፣ ግደል ተጋደል የት እንዳደራረሰን ከኛ በላይ ምስክር ስለሌለ ነው፡፡
በተመሳሳይ መንገድ እየሄድን የተለየ ውጤት አናመጣም ብለን አመንን፡፡ ከመግደልና ከመጨፍጨፍ፣ ከማሠርና ከማሳደድ የተለየ መንገድ እንከተል ብለን ወሰንን፡፡ አግላይና ዝግ የነበረውን የፖለቲካ ምኅዳር አሰፋን፣ ክፍትና አካታች በማድረግ፣ አቃፊና ደጋፊነቱን ለማረጋገጥ ጥረት አደረግን፡፡ የወኅኒ በሮቻችን ተከፍተው አእላፍ እሥረኞች የነጻነትን አየር ተነፈሱ፤ በሀገር ቤትና በዳያስፖራ መካከል ያለውን ድልድይ ሠርተን ሺዎች ወደ ሀገራቸው ገቡ፤ ብረት አንግበው የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሀገር ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ተቀላቀሉ፡፡
አንዳንዶቹን ረጅም ምዕራፍ ተጉዘን ከጐናችን ተሰለፍው አብረውን እንዲሠሩ ስንፈቅድ፤ ዴሞክራሲን አምጦ መውለድ ብቻውን እንደማይበቃ አምነን ነው፡፡ … ትዕግሥታችንና ሆደ ሰፊነታችን ብዙ ትችትና ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ጫናም እንድናስተናግድ አድርጐን ነበር፡፡ አዲስ መንገድ አዲስ ፈተና ያመጣል፡፡ በምክንያት የማይመሩት የሥልጣን ጥመኞች፣ ይህ ስለማይገባቸው በጀብደኛና በእብሪተኛ እርምጃ የጥፋት ሰይፋቸውን በጠራራ ፀሐይ፣ በአደባባይ መዘው የደማቅ ጌጦቻችንን ውድና ክቡር ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡
የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲሲቱ የተስፋ አድማስ፣ የአፍሪካ ፈርጥና ተምሳሌት ማድረግ እንጂ ኢትዮጵያን የኅዘን ማቅ ማልበስ አይደለም፡፡ ሀገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር እስከረዳን ድረስ እየመረረንም ቢሆን የምንቀበለው ሐሳብ ይኖራል፡፡ በሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ዘላቂ ጥቅምና ክብር ላይ ግን ድርድርም ሆነ ትእ
ግሥት ፈጽሞ አይኖረንም፡፡
ከኢትዮጵያ የሚበልጥ፣ ከሕዝባችን የሚቀድም ምንም ነገር የለም፡፡ ለዴሞክራሲና ለሰላም ስንል እንታገሳለን፤ ለሀገርና ለሕዝብ ስንል ደግሞ መራር ውሳኔን እንወስናለን፡፡ እያለቀስን ብንቀጥል የጓዶቻችንን ዓላማ አናሳካም፤ ተስፋ ብንቆርጥ የጓዶቻችንን ሰንደቅ ከፍ አናደርገውም፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ? ድክመታችን ምን ነበር? ምንስ ማድረግ ነበረብን የሚሉትን በትክክለኛ ጥናት እንለያለን፡፡ ካጋጠመን ፈተና እንማራለን፤ እንዳይደገም አድርገን የሕገ ወጥነት በሮችን ሁሉ እንዘጋለን፡፡ ለአፍታም ግን ከጉዟችን አንገታም፡፡
ከዓላማችንም አንዛነፍም፡፡ መንገዳችንንም አንቀይርም፡፡ በመጨረሻም በፈተናችን ወቅት ከጐናችን በመቆም ድጋፋችሁንና ማጽናናታችሁ ላልተለየን ወዳጅ ሀገራት በራሴና በኢፌዲሪ መንግሥት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ለመከላከያ ሠራዊታችን፣ ለሟቾች የሥራ አጋሮችና ለሟች ቤተሰቦች ፈጣሪ መጽናናትን እንዲሰጥ እመኛለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ!    

Read 1264 times