Tuesday, 02 July 2019 12:14

ሮቦቶች በ10 አመታት 20 ሚሊዮን ሰራተኞችን ያፈናቅላሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


      በፋብሪካዎችና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሰዎችን ቦታ እየተኩ የሚሰሩ ሮቦቶች ቁጥር እየተበራከተ እንደሚገኝና ሮቦቶች በመጪዎቹ 10 አመታት ጊዜ ውስጥ በመላው አለም 20 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስራ መደብ በመውሰድ ከስራ ያፈናቅላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ የተባለው ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በመጪዎቹ 10 ያህል አመታት ጊዜ ውስጥ 14 ሚሊዮን ያህል ሮቦቶች ወደ ኢንዱስትሪዎች በማሰማራት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከስራ ገበታቸው በማፈናቀል ቀዳሚዋ አገር ቻይና እንደምትሆንና በእንግሊዝም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሮቦቶች ሳቢያ ስራ ያጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በበርካታ አገራት የአውቶሞቲቭ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ሰዎችን ተክተው የሚሰሩ ሮቦቶች ቁጥር  እያደገ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በቻይና እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2016 በነበሩት አመታት በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሰሩ ሮቦቶች ቁጥር በ199 በመቶ፣ በሌሎች ዘርፎች ደግሞ በ267 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም አመልክቷል፡፡
ባለፉት 19 አመታት ጊዜ ውስጥ በአለማቀፍ ደረጃ 1.7 ሚሊዮን ያህል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰራተኞች ስራቸውን በሮቦቶች መነጠቃቸውንና   ከእነዚህም መካከል 550 ሺህ ያህሉ የቻይና ሰራተኞች መሆናቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1313 times