Print this page
Tuesday, 02 July 2019 12:23

እሷ በበላችው፣ በእኔ ላከከችው…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ልጆቹ ቤት ለቤት ይሯሯጣሉ፡፡ እግረ መንገድ ‘ዳድ’ ኮመዲኖው ላይ ያስቀመጠው ሸላይ መነጽሩ ይወድቅና ብርጭቆው ይሰነጠቃል፡፡ ‘ዳድ’ ነብር ይሆናል፡፡
“ማነው መነጽሬን እንዲህ ያደረገው! ዛሬ አናታችሁን ሳልላችሁ ተናገሩ፣ ማንኛችሁ ናችሁ የጣላችሁት?”
አንደኛው ሌላኛው ላይ ጣቱን ይቀስራል “እሱ ነው!”
ሌላኛውም አፀፋውን ይመልሳል… “እሱ ራሱ ነው!”
‘ዳድ’ ወይ ተራግሞ… “ለእንቁጣጣሽ አይደለም ኮትና ሱሪ ካልሲ እንኳን አይገዛላችሁም፣” የሚል የሰበር ሰሚ ጅምላ ፍርድ ይበይናል፤ ከባሰበትም ወደ “ሱሪ ዝቅ አድርግ…” ይገባል፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገድ… “ሱሪ ዝቅ አድርግ…” የሚሏት ነገር አሁንም አለች እንዴ! ግራ ስለገባን ነው…እንደ አንዳንድ የዘመኑ ወጣቶች አዝማሚያ… አለ አይደል…  “ሱሪ ዝቅ አድርግ…” የሚለው የቤተሰብ አባል የትኛው እንደሆነ ግራ ስለገባን ነው፡፡
እኔ የምለው…ዘንድሮ ይሄ ሁሉንም ነገር ‘እዛኛው ወገን’ ላይ የማላከክ ነገር እንዲህ አገሩን የሞላው ለጤፉ የተጠቀሙበት ማዳበሪያ ውስጥ የሆነ ኬሚካል ምናምን ነገር ተጨምሮበት ይሆን እንዴ! ልክ ነዋ... ከሁለት ሰዎች አንዱን እንደሚይዝ የጉንፋን ወረርሽኝ እንዲህ የሰፈረብን የሆነ ምክንያት ቢኖረው ነዋ! አመልካች ጣት ሥራ በዛባት እኮ!
 እናላችሁ…ለሁሉም የተበላሹ ነገሮች፣ በጎ ላልሆኑ ነገሮች፣ ፍጻሜያቸው ላላማሩ ነገሮች  ውጪያዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… እሷዬዋ የጋገረችው እንጀራ ጣዕም ከታጣበት ችግሩ ያለው እሷ ሙያ ላይ አይደለም፡፡ “እንጀራ ስጋግር ያቺ ክልፍልፍ ዘው ብላ ኩችና ገብታ ነበር፡፡ በምን ዓይኗ እንደበላችብኝ ምን አውቃለሁ!” ትላለች፡፡
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የ‘ቦተሊካችን’ ትልቁ ችግር ምን መሰላችሁ...ለ‘ኩኩ መለኮቴ’ አለመውጣቱ፡፡ ሁሉንም የተበላሸ የሚባል ነገር የ‘ትናንቶቹ’ ናቸው ያደረጉት...ኸረ የሰዉ  እንኳን ቢቀር፣ ገልጦ የሚያይ ፈጣሪስ ምን ይላል! እንዴ… ያ ሁሉ አብረን ‘ብትን’ ስንልበት የነበረው ብላክ ሌብል “የሚጠጣው ጠፍቶ እንደ ውሀ ሲፈስ አደረ፣” ይባል የነበረው ግብዣስ! (የ‘ውስኪ ጡር’ ካለው ሹክ በሉንማ!)  “ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው…” አይነት ሌላውን ረስተን በራሳችን ዓለም አብረን ‘ቡጊ፣ ዉጊ’ ስንል የነበረውስ! “ደግፌያለሁ፣ ተስማምቻለሁ…” እያልን እንደ ትራፊክ አስተናባሪ አብረን እጃችንን ሽቅብ ስንሰቅል የኖርነውስ! እናላችሁ “የደገፍኩ እመስል የነበረው በውስጤ ሆዴ እየቆሰለ ነበር፣” አይነት የምን የ‘ኩኩ መለኮቴ’ እሽቅድድም ነው!    (“ሆድህ መቁሰሉንና የቆሰለበትን ምክንያት የሚያስረዳ የሀኪም ወረቀት አምጣ” አይባል ነገር ሆኖብን ነው፡፡) እናላችሁ…ነጋ ጠባ ‘ትናንት፣’ ‘የትናንቶቹ’ ስንል ነገ እኮ ሁሉም ‘የትናንቶቹ፣’’ ይሆናል፡፡
አስቸጋሪ ነው ይህ አይነት ጣጣ
ነገሩስ በእኔ ድንገት ቢመጣ
ሁሉ እየሣቀ እጁን ሊያወጣ
ተብሎም ተዘፍኖ ነበር፡፡ እናማ… ዘንድሮ እየሳቅን እጃችንን ያወጣነውን ቤቱ ይቁጠረን አንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በፊት፣ በፊት ኳሳችን ላይ ያም ሲያጠጣን፣ ያም ሲረመርመን ቁጥር አንድ የተለመደች ምክንያት ነበረች፡፡ “አየሩ ከብዶን ነው” ይባል  ነበር፡፡ እናላችሁ አየሩ መክበዱን አልተወም፣ እኛም መጠጣታችን አልቀረም፡፡
እናላችሁ…በበፊት ጊዜ አንድ የልጆች ጨዋታ ነበረች…
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው፣ በእኔ ላከከችው
የምትል ነገር ነበረች፡፡ አሁን ‘ኩኩ መለኮቴ’ ምንም ትሁን ምንም… “እሷ በበላችው፣ በእኔ ላከከችው” አብዛኞቻችንን እያዳረሰች ነው…ትንሽ አርትኦት ነገር ተሰርቶባት…
ኩኩ መለኮቴ
እነሱ በበሉት በእኛ ላይ ላከኩት
ነገር ነው፡፡
“ለምንድነው የማትነጋገሩት?”
“ከእሷ...ከደመኛ ጠላቴ ጋር! ያኔ ያደረገችኝን መቼም አልረሳውም!”
“ምን ብታደርግሽ ነው ይሄን ያህል የጠላሻት!”
“ያደረገችኝንማ እኔ አውቀዋለሁ…”
“እኮ ንገሪኛ፣ እንዲህ የጠላሻት ይሄን ያህል ምን ብትበድልሽ ነው!”
“እሷ መድሀኒት አስነክታኝ አይደል እንዴ ሎተሪ እንኳን አልደርስ ያለኝ…”
(ምን! ከሰጡ አይቀር እንዲህ ‘ፕላቲኒየም’ የሆነ ምክንያት መስጠት ነው፡፡)
 “ምነው ይሄን እስከዛሬ አልነገርሽኝም!”
“እኔም በኋላ ነው ያወቅሁት፡፡ የቆረጥኩት ሎተሪ ሁሉ አልደርስ ሲለኝ የሆነች አክስቴ አዋቂ ቤት ወሰደችኝ፡፡ እሱ እውነቱን ነገረኝ፡፡ ዞማ ጸጉር ያላት ጠይም ጓደኛሽ አስቋጥራብሽ ነው አልደርስ ያለሽ አለኝ፤ ዞማ ጸጉር ያላት ጠይም ጓደኛ ደግሞ እሷ ብቻ ነች ያለችኝ፡፡”
ቦተሊካችንን ‘አዋቂ ቤት’ ውሰዱልንማ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ፣ አንዲት ልጅ ሥራ መሥራት ስልችት ይላትና አባቷ ፊት ደጋግማ ትነጫነጫለች፡፡ ምግብ አብሳይ የሆነው አባቷ፤ ሶስት ድስቶች አምጥቶ ውሀ ይጨምርና አንደኛው ውስጥ ድንች፣ አንደኛው ውስጥ እንቁላል፣ አንደኛው ውስጥ የተፈጨ ቡና ከትቶ ሶስቱንም ይጥዳቸዋል፡፡ ከሀያ ደቂቃ በኋላም ያወጣቸውና ድንቹን አንድ ሳህን ላይ፣ እንቁላሉን ሌላ ሳህን ላይ ያደርግና ቡናውን ኩባያ ውስጥ ይቀዳዋል፡፡
“ልጄ፣ ምን ይታይሻል?” ይላታል፡፡
“ድንች፣ እንቁላልና ቡና” ትለዋለች፡፡
“ጠጋ ብለሽ ተመልከችና ድንቹን ንኪው” ይላታል፡፡ ድንቹን ትነካዋለች፡፡ ለስላሳ ሆኖ ታገኘዋለች፡፡ የእንቁላሉን ቅርፊት ላጪው ብሏት ከላጠችው በኋላ ውስጥ አስኳሉና ነጩ ፈሳሽ ጥጥር ብሎ የበሰለ እንቁላል ይገጥማታል፡፡ በመጨረሻ ቡናውን እንድትቀምሰው ይነግራትና ቀምሳው በጣእሙ ተደስታ ፈገግ ትላለች፡፡
“አባዬ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም” ትለዋለች፡፡ ሶስቱንም ማለትም ድንቹንም፣ እንቁላሉንም፣ ቡናውንም ተመሳሳይ ነገር፣ ማለትም የፈላ ውሀ ውስጥ እንደከተታቸው ነገራት፡፡ “ግን የሁሉም ምላሽ እንደየጠባያቸው ነው” አላት፡፡ “ድንቹ ውሀ ውስጥ ሲገባ ጠንካራና ጠጣር ነበር፡፡ ግን የፈላው ውሀ ውስጥ ልስልስና ደካማ ሆነ፡፡ የእንቁላሉ ቅርፊት ቢሰበር ውስጥ ያለው በቀላሉ የሚፈስ ነው፡፡ የፈላ ውሃ ውስጥ ሲገባ ግን የውስጠኛው ፈሳሽ ጠጣርና ጠንካራ ሆነ፡፡ ቡናው ግን ከሁሉም ይለያል፡፡ ዱቄቱ የፈላ ውሀ ውስጥ ሲገባ ውሀውን ለወጠውና አዲሰ ነገር ፈጠረ፣” ይላታል፡፡ እሷም በጥሞና አዳመጠችው፡፡
“አንቺ ከሶስቱ የትኛው ነሽ? አንድ ሰው በአስቸጋሪ ሁኔታ በርሽን ሲያንኳኳ ምን አይነት ምላሽ ነው የምትሰጪው? ድንች ነሽ፣ እንቁላል ነሽ ወይስ ቡና?”  ልጅቱ መልስ አልነበራትም፡፡ እንዲህም፣ አላት… “በህይወት ውስጥ ዙሪያችንን በርካታ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ብዙ ነገሮችም ይገጥሙናል፡፡ ዋናው ነገር ግን ከውጭ የሚደርስብን ነገር ሳይሆን የውስጣችን ምላሽ ነው፡፡”
የምር፣ አሪፍ አይደል! በየእለቱ አንድ ሺ አንድ ነገሮች የሚገጥሙን በሚመስሉበት በአሁኑ ጊዜ ይሄ በጣም አሪፍ ምክር ነው፡፡ የምር እኮ…ነገሮችን በጥሞና ማሰላሰል ካልቻልን፣ ሁለትና ሁለትን ደምረን ሶስትና አምስት ሳይሆን ባይጥመንም እንኳን ትክክለኛውን መልስ ለመጋፈጥ ካልቻልን ቅርፊታችን በቀላሉ እንክሽ ብሎ አስኳላችን የምንለውም፣ ምናችን የምንለውም  ይዘረገፋል፡፡ በማላከክና አመልካች ጣትን እዚህኛውና እዚያኛው ላይ በመቀሰር የትም አይደረስም፡፡
አንዱ አላራምድ እያለ የሚያደነቃቅፈን ነገር ቢኖር “አዎ እኔ ነኝ የበላሁት” ከማለት ይልቅ በሌላ የማላከክ ‘ኩኩ መለኮቴ’ ነገራችን ነው፡፡ ልቦናውንም ይስጠን፣ ምህረቱንም ያፍጥንልንማ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2247 times