Tuesday, 02 July 2019 12:25

ጠ/ሚኒስትሩ በአጥፊዎች ላይ ጨከን መረር ይበሉ (ሌላ ምርጫ የለም)

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

  ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ መቶ ሚሊዮን ህዝብ መቶ ሚሊዮን ፍላጎት፣ መቶ ሚሊዮን ባህሪ፣ መቶ ሚሊዮን ዐመል፣ መቶ ሚሊዮን አመለካከት፣ መቶ ሚሊዮን አስተሳሰብ … ያለው ህዝብ ነው:: ልዩነታችን ብዙ ነው፡፡ የጋራ ያደረግነው ድህነትን ብቻ ይመስለኛል፡፡ የተማረውም ያልተማረውም ኢትዮጵያዊ ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ይህ መቶ ሚሊዮን ህዝብ (መቶ በመቶ ሊባል በሚቻል ደረጃ) ያልሰለጠነ አመለካከትና አስተሳሰብ ያለው መሆኑ በግልጽ ይንጸባረቃል፡፡ የሰለጠነ አመለካከትና አስተሳሰብ የሌለውን ህዝብ መምራት ደግሞ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ፣ የፀሐይ ብርሃንን ያህል ግልጽ የሆነ እውነታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሰለጠነ አመለካከትና አስተሳሰብ የሌለው ህዝብ ለሕይወት ዋጋ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ለህይወት ዋጋ የማይሰጥ ሰው ደግሞ ለመግደልም፣ ለመሞትም ርህራሄ ሊኖረው አይችልም፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍቅር ሲያስተምር፣ ስለ ሰላም ሲሰብክ እንደነበር የክርስትና እምነት አባቶች ይናገራሉ፡፡ በወንጌሉም ላይ የተጻፈው ይኸው ነው፡፡ እሱ ፍቅር፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ሰላም፣… ሲል አይሁዶች “ሀሳዊ መሲህ ነው” ብለው “ሰቀሉት”፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ላለፉት አስራ አምስት ወራት ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “ፍቅር - ሰላም - መደመር” እያሉ ሲወተውቱ፤ ስልጣን ላይ በወጡ በሦስተኛው ወር የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ በዓመቱ ሰኔ ደግሞ አንድ የክልል መሪ፣ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና ሌሎች ባለስልጣናት ተገደሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሰለጠነ አመለካከትና አስተሳሰብ የሌለው ህዝብ መሀል ቆመው “ፍቅርና መደመር” የሚል ፍልስፍናቸውን በየመድረኩ ሲያስተጋቡ፣ ነገ ከነገ ወዲያ እርሳቸውንም እንደ ኢየሱስ “ስቀሎ ስቀሎ” የሚል ኃይል አይመጣም ብሎ መደምደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረስን በመሆኑ ነው ይህቺን ማስታወሻ ለመከተብ ብዕሬን ያነሳሁት፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰው ናቸው፡፡ አንድ ቀን መሞታቸውም እርግጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠላቷ የበዛ፣ ከመስራት ማውራት የሚቀናው መቶ ሚሊዮን ህዝብ የሚመሩ ሰው ናቸው፡፡ እናም የዶ/ር ዐቢይ ሞት የአንድ ሰው ሞት ብቻ አይሆንም፡፡ በዚህ ወቅት የእርሳቸው ሞት የመቶ ሚሊዮን ህዝብን መጨራረስ፣ መበታተን፣ ዋይታና ሰቆቃ… ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ዶ/ር ዐቢይ፤ ከልባቸው ሀገራቸውን የሚወዱ ከሆነ፣ ካንጀታቸው ህዝባቸውን የሚያፈቅሩ ከሆነ፣ “ፍቅር - መደመር” የሚሉትን “ፍልስፍና” ለጊዜው ተወት አድርገው፣ ሀገራቸውንም ህዝባቸውንም የሚታደግ ሥራ መስራት ይገባቸዋል፡፡
የማህበራዊ ውል ንድፈ ሃሳብን (Social Contract Theory) የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚነግሩን ከሆነ፤በዓለም ላይ መንግስት የሚባለው ነገር ያስፈለገው በዋናነት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ነው፡፡ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ሃይማኖትን መስበክና ማስተማር የመንግስት ሥራ አይደለም፡፡
እስከ ዛሬ ከነበረው የመንግስት ተግባር ውስጥ ህዝቡ የጠላው፤ የጅምላ ጭፍጨፋን፣ ነፃ እርምጃን፣ ቀይ ሽብርን፣… እንጂ የብዙሃኑን ህዝብ ሰላምና ደህንነት፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር የመንግስት ጦር፣ የመንግስት ፖሊስና የፀጥታ ኃይል ምንም ዓይነት “ህጋዊ እርምጃ” አይውሰድ፣ ሰላም አያስከብር፣ ወንጀልን አይከላከል የሚል ገልቱ የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደ ቤት መመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ገበሬው ማረስ፣ ነጋዴው መነገድ፣ ተማሪው መማር፣ መምህሩ ማስተማር፣ ወዛደሩ ማምረት፣ የመንግስት ሰራተኛው መደበኛ ተግባሩን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እየፈራንና እየተሳቀቅን የቆቅ ኑሮ መኖር እጣ ፈንታችን እየሆነ ነው፡፡ ሀገር የሚፈርሰው በምክክር፣ በእቅድ፣ በውይይትና በአፈርሳታ አይደለም፡፡ ማታ በሰላም ተኝተን ጧት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ሀገር ፈርሶ ሊጠብቀን ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ ምን እየተጠበቀ ነው? ሀገሪቱ (በከተማም በገጠርም) የሽፍታ መናኸሪያ እስክትሆን ነው እንዴ የሚጠበቀው?
በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ኑሯችን ተመሰቃቅሏል:: በሰላማችን መታጣት ምክንያት ባለ ሁለት ዲጂት ኢኮኖሚያዊ እድገታችን እንቅፋት ገጥሞታል:: ኢንቨስትመንት ተሰነካክሏል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት እንኳን አዳዲስ ኢንቨስተር ሊመጣ ያሉት ኢንቨስተሮች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ጥቃትና የንብረት ውድመት ተማረው ብዙዎቹ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ መጡበት ተመልሰዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ባለ ሃብቶችም የባንክ ብድር ተሸክመው በእዳ ተሽመድምደዋል፡፡ አንዳንዶቹ የጎሣ ፖለቲካው ሰለባ ሆነው ተሸማቀው ተቀምጠዋል፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ላይ በወጡ በሦስተኛው ወር (ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ል) በመስቀል አደባባይ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ ይህንን የፈጸመው ማን እንደሆነ በመጣራት ላይ እንዳለ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ል ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከቡራዩ ተነስተው ጠመንጃቸውን እንደ ያዙ ቤተ መንግስት መግባታቸውን ሰማን፡፡ ነገሩ ምንድነው? የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው ወይስ ሌላ? እያልን ስንወያይ፣ ወታደሮቹ እስፖርታዊ ቅጣት (Push Up) ተቀጥተው “ሁለተኛ እንዳይለመዳችሁ” ተብለው ተሰናበቱ፡፡ ነገሩ ሲታይ ከበስተጀርባቸው ያሰማራቸው ኃይል እንዳለ ሲታወቅ፣ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው መቀጣታቸው ተነገረን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ በተፈጠረው የፀጥታና ደህንነት መስሪያ ቤት መናጋት በተፈጠረው ክፍተት ምክንያት በእርሳቸው ላይ የግድያ ሙከራና መፈንቅለ መንግስት ከመሞከሩ በተጨማሪ በሌሎች አካላት ላይ አሳዛኝና አሰቃቂ ግድያዎች ተፈጽመዋል:: አንዳንዶቹን ልጥቀስ፡፡ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ መነቃቃት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለው አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ዋነኛው ግብዓት ደግሞ ሲሚንቶ ነው፡፡ ይህንን የተገነዘቡ የጥፋት ኃይሎች፤ ዋነኛ የሲሚንቶ አምራች የሆነው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሥራ ባልደረቦቻቸውን በጠራራ ፀሐይ ገደሉ፡፡ (ደግነቱ ዳንጎቴ ጓዙን ጠቅልሎ አልወጣም)
የኤሌክትሪክ ኃይል ለአንድ ሀገር ያለው ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው፡፡ የሀገር የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን የህዝብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ከመብራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንን የተገነዘቡ የጥፋት ኃይሎች፤ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ምንጭ በእጥፍ እንደሚጨምር እቅድ ተይዞ፣ መላው ህዝብ እየተረባረበ እየገነባው ያለው የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሀገሪቱ ዋና ከተማ፣ በጠራራ ፀሐይ፣ በመስቀል አደባባይ ተገደለ፡፡ እነዚህን ግድያዎች የፈጸሙ ወንጀለኞች እነ ማን እንደሆኑ ተጣርቶ፣ ጥፋተኞቹ ሳይቀጡ ዛሬ ደግሞ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም በመኖሪያ ቤታቸው ተሰው፡፡ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና ሌሎች ባለስልጣናት በቢሯቸው ተገደሉ፡፡
ይሄ ሁሉ ግድያ የሀገሪቱ ደህንነት መላላት ውጤት ነው፡፡ ሌላ ምንም ዓይነት ስም ልንሰጠው አንችልም፡፡ እዚህ ላይ ለመሆኑ የሀገሪቱ የደህንነትና የፀጥታ መላላት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ፤ የዚች ሀገር ትልቁ ችግር የተቋማት ቀጣይነት ማጣት ነው፡፡ የአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ተወግዶ ደርግ ስልጣን ሲይዝ የመጀመሪያ ተግባሩ ያደረገው በወቅቱ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሰራተኞችን “አድኃሪያን፣ የፊውዳል ርዝራዦች፣ አቆርቋዦች፣ ንዑስ ከበርቴ፣…” የሚሉ ስሞችን በመለጠፍ እነሱን ካባረሩ በኋላ “ተራማጅ” የሚሏቸውን ጀሌዎች በየመ/ቤቱ በመመደብ ቢሮክራሲው ቀጣይነት እንዳይኖረውና ለዓመታት የተገነቡ ተቋማት እንዲፈርሱ አደረጉ:: የፈረሰው መልሶ እስኪገነባ በርካታ ክፍተቶች ተፈጠሩ፡፡
ደርግ የሀገሪቱን ሀብት ተጠቅሞ ለ17 ዓመታት የገነባቸው በተለይም የመከላከያ፣ የደህንነትና ሌሎች ወሳኝ ተቋማት ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ አፈራረሳቸው፡፡ የኢህአዴግ ጥፋት ማፍረሱ ብቻ ሳይሆን እንደገና የማደራጀት ሥራ ባለመስራቱ እምቦቀቅለዋ ኤርትራ “አገር” በሆነች በማግስቱ ኢትዮጵያን በመውረሯ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር የምናስታውሰው ነው:: ከእነዚህ ተከታታይ ስህተቶች ያልተማረው መንግስታችን፤ የዛሬ 15 ወር ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስልጣን ከያዙ በኋላ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ የደህንነት መስሪያ ቤትን አፍርሶ እንደገና መገንባት ነው፡፡
የሀገሪቱ የፀጥታና የደህንነት መስሪያ ቤት ላለፉት 26 ዓመታት ጥሩም መጥፎም ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ይህ መስሪያ ቤት ከደርጉ ዘመን የባሰ ህዝብን ያንገላታ፣ ሰብዓዊ መብትን የገፈፈ፣ በዜጎች ላይ አያሌ አሰቃቂ ተግባራትን የፈጸመ መሆኑ አሌ የማይባል ነው፡፡ እናም እንዲህ ያለ ህዝብን የበደለ የአፈና ተቋም መስተካከል የሚገባው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ በደሉን ያደረሱት በዚህ መስሪያ ቤት ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እንጂ ተቋሙ እንደ ተቋም ለሀገሪቱ አስፈላጊ መሆኑም ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
እንዲህ ያለ፣ ከሀገር ህልውና እና ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ጋር ጥብቅ ትስስር ያለውን መስሪያ ቤት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ አቋርጦና ሽባ አድርጎ እንደገና “ሀ” ብሎ ለመጀመር መነሳት ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ያየነውን የሀገሪቱን ቁልፍ ሰዎች ያሳጣ ግድያ እንዲፈጸም በር ከፍቷል፡፡ በዚህ አያያዝ ከካይሮ የሚመጣ ኃይል ጓዳችን ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ፣ የሚፈልገውን ሰርቶ ለመመለስ የሚያግደው ነገር ሊኖር ይችላል?
በአንዳንድ ሀገሮች አንድ ባለስልጣን ሹመት ሲሰጠው የፀጥታው መስሪያ ቤት የመጀመሪያ ተግባር በተጠና መልኩ አጃቢ መመደብ ነው፡፡ ተሿሚው “እምቢ፣ አትመድቡልኝ” ማለት አይችልም:: እምቢ ካለ “አንተ ነገ ከነገ ወዲያ ከስልጣንህ ትነሳለህ፡፡ ሀገሪቱ ግን ትቀጥላለች፡፡ የሚያሳስበን የአንተ ደህንነት ብቻ አይደለም፡፡ የሚያሳስበን የሀገሪቱ ደህንነት ነው፡፡ የሀገሪቱን ጥቅም አሳልፈህ ላለመስጠትህ ምን ዋስትና አለ?” የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ በእኛም ሀገር የባለስልጣናት የቤት ሰራተኞች ሳይቀሩ ስለላ እንደሚደረግባቸው ይነገራል፡፡ ከማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ወዘተ. ክትትል ይደረጋል፡፡ የባህሪ ለውጥ ከታየ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ታዲያ ይህ አሰራር ለምን እንዲቀየር ተደረገ?
ሃሳቤን ለማጠቃለል አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የደህንነት መዋቅር በተገቢው መንገድ ሥራውን እየሰራ እንዳልሆነ በዶ/ር ዐቢይ የስልጣን ዘመን በትልልቅ ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች በግልጽ እንደሚያሳዩ ይታመናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እና መንግስታቸው ይህንን ክፍተት በአስቸኳይ እንዲሞላ ካላደረጉ ከእስካሁኑም የከፋ ጥፋት ወደፊት ሊፈጸም እንደሚችል መገመት ነብይነትን የሚጠይቅ አይደለም፡፡
በዶ/ር ዐቢይ የስልጣን ወራት የታየው መዘናጋት፣ በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ አለመቻል ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በዝምታ ማስታመም መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ህፃን ማባበልና እሹሩሩ ማለት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ለአጥፊዎች መቀጣጫ ሊሆኑ የሚችሉ ጠበቅ ያሉ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡
በመጨረሻም፤ እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ አንድ ነገር ለማለት ወደድሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይዘውት የመጡት መሪ መፈክር (Motto) “መደመር” የሚል ነው፡፡ ይህም የጠቅላይ ሚኒስትራችን ፍልስፍና መሆኑ ተነግሮናል፡፡ መልካም! ፍልስፍና ሀገርን የመምሪያ፣ ህዝብን የማስተዳደሪያ ስልት ሊሆን የሚችልበት መንገድ ግን አይታየኝም፡፡ ጥንታዊ የግሪክ ሊቃውንትም፤ “ፈላስፋዎች የሀገር መሪ ሊሆኑ ይገባል” (Philosopher King) አሉ እንጂ ሀገር በፍልስፍና ይመራል አላሉም፡፡ ምናልባት “አንድ መሪ ሀገሩን የመራበት ዘዬ ጥናት ቢደረግበት ፍልስፍና ሊኖረው ይችላል” የሚባል ከሆነ፣ በዚህ መስማማት ይቻላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::


Read 521 times