Tuesday, 02 July 2019 12:28

የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካንና ዘረኝነትን መግታት አቃተን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

   አገር እስኪያሳጣን ድረስ ነው? መመለሻው እስኪጠፋን ድረስ?
                   
       እውነት ከሃሰት ተምታታብን፡፡ ሃራም ከሃላል ጠፋብን፡፡ ክብር ከነውር ተመሳሰለብን፡፡ ምን ቀረን!
ግድያው፣ በጥቃቱ ለሞቱ፣ ሃዘኑም ለቤተሰብና ለወዳጅ ዱብዳ ነው፡፡ ተመልሶ የማይገኝ የሰው ህይወት በግድያ ዘመቻ ጠፋ፡፡ በአጠቃላይ ለአገርም ከባድ ድንጋጤና ጭንቀት ነው፡፡ የአስደንጋጭነቱና የአደገኛነቱ ያህል ድንገተኛ መሆኑ ባይካድም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ እየጦዘ፣ ዘረኝነት እየተራገበ፣ አሳፋሪ የነበሩ አባባሎች መፈክር እስከመሆን እየደረሱ፣ ሐራም የነባሩ ሃላል እየሆኑ መምጣታቸው ግን ዱብዳ አይደለም፡፡
በብሔር ብሔረሰብ የሚያቧድን ፖለቲካ ካልተገዘተና የግለሰብ ህልውና ላይ በተመሠረተ፣ የእያንዳንዱን ግለሰብ ነፃነት በሚያስከብር ስልጡን ፖለቲካ ለመተካት ጤናማ ጉዞ ካልጀመርን፣ እንጦርጦስ እንደሚያወርደን አልተረዳንም? የዘረኝነት አስተሳሰብና ቅስቀሳ ነውረኛና ክፉ ሃጥያት መሆኑን ተገንዝበን ካልገታነው፣ መዘዙ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የሚያጠፋ፣ አገርን የሚያሳጣ እንደሆነ አልገባንም?  ከቅርብ እስከ ሩቅ፣ ከጐረቤት እስከ ባሕር ማዶ፣ በየእለቱ የስንቱን አገራት የመርዶ ዜና እያየን፣ እንዴት አይገባንም?
ሌላው ቢቀር፣ በራሳችን አገር በዘረኝነት ምክንያት የተፈፀመውን የጥፋት አይነትና ብዛት፣ በየቦታው የሚደርሰውን መዓት ማየትስ እንዴት ያቅተናል? በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና በዘረኝነት ምክንያት ብዙዎች ሞተዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፡፡
ይህን ሁሉ እያየን ምን አደረግን? አዎ፣ የተወሰኑ አዋቂዎችና አስተዋዮች፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ እያሳሰባቸው፣ ከብሔር ፖለቲካና ከዘረኝነት በሽታ እንድናመልጥ፣ በየጊዜው ምክራቸውን ተናግረዋል፡፡ ግን ጥቂት ናቸው፣ ብዙ ሰሚም አላገኙም፡፡ በተቃራኒው፣ በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈ የሚያቀጣጥል ቅስቀሳ ነው፣ ነጋ ጠባ በጩኸት የሚራገበው፡፡
በዚህ መሃል፤ እንደ አውቶማቶን፣ ለውይይት በተጠሩ ቁጥር፣ “ውይይት አስፈላጊ ነው” ከማለት ውጭ ሌላ ሃሳብ የማይወጣቸው፤ እንዲናገሩ በተጋበዙ ቁጥር፣ “መነጋገር አስፈላጊ ነው” ማለት ብቻ በቂ የሚመስላቸው ሞልተዋል፡፡
“መነጋገር፣ መወያየት፣ መደማመጥ፣ ዲሞክራሲ…” እነዚህ ቃላት ብቻ፣ የሁሉም ችግር መፍትሔ፣ የሁሉም ጥያቄ ምላሽ የሚሆኑ ይመስል፣ …ይሄውና ስንት አመት ሲደጋገሙ ሰማን፡፡
ዲሞክራሲ እሺ፣ መልካም፡፡ ነገር ግን፣ ከዲሞክራሲ በፊት የሚቀድሙና የሚልቁ ነገሮች መኖራቸውን መናገር አያስፈልግም እንዴ? አገር እና ሕግ ሳይኖር፣ ዲሞክራሲ ትርጉም የለውም - ከቀውስና ከትርምስ በቀር፡፡
ከዲሞክራሲ በላይና በፊት፣ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነትና መብት በአዎንታ መቀበል፣ ህግ አክባሪነትና የህግ የበላይነትንም ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ሁሉ ከአመት ዓመት፣ ሳይዘናጉና ሳይሰላቹ ለመገንባት እንዴት መትጋት እንደሚቻልም ጭምር ማወቅና መማር ያስፈልጋል፡፡
መሰረታዊውንና ዋናውን ግንድ ከነቅርንጫፎቹ እየዘነጋን፣ ዲሞክራሲ የምትል አንዷን ቅጠል ብቻ ቆንጽለን መናገር፣ አዋቂነት አይደለም፣ መፍትሔም አይሆንም፤ ከዘረኝነት ጥፋትና ከትርምስም አያድንም፡፡
መነጋገርና መወያየትስ?  ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ የሚሆነው ግን፣ የምንናገረውን የምናውቅ ከሆነ ነው፡፡ ለማወቅ ደንታ ካለን ነው፡፡
እውነትን ከሃሰት፣ ትክክልን ከስህተት ለይተን የማወቅ ፍላጐት ካለን ነው፣ መነጋገርና መወያየት ትርጉም የሚኖረው፡፡
አልያማ፣ መነጋገር፣ እንዲሁ በባዶ መሸነጋገል ይሆናል፡፡ “መነጋገር ያስፈልጋል” የምትል አባባልን ብቻ እየደጋገሙ መድከምና ሰሚን ማድከም፤ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ለምን?
ክፋት ነው ማለቴ አይደለም፡፡ እንዲያውም “መነጋገር ያስፈልጋል” የሚለው አባባል፣  የጨዋዎቹ ፈሊጥ ነው፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ጨዋዎቹ እንዲህ “መነጋገርን”፣ ባዶ “መሸነጋገል” እንዲሆን ሲያደርጉት፣ ሜዳውን ለክፉዎች አመቻችተው ለቀቁ ማለት ነው፡፡ እናም መወያየት ማለት በባዶ መወነጃጀል ሆኖ ያርፈዋል፡፡ የክፉዎች መጫወቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ መነጋገር ማለት ውሸትን መፈልፈል፣ አሉቧልታን ማራባት፣ መሰዳደብና መበሻሸቅ፣ ማንቋሸሽና ማዋረድ፣ መወነጃጀልና እየዛቱ ማስፈራራት፣ ለጥላቻና ለጥቃት ዘመቻ መቀስቀስ ሲሆንብን፣ እንዴት መከላከልና ማስተካከል አቃተን?
“መነጋገር ያስፈልጋል” የሚለው ፈሊጥ በቂ አይደለም፡፡ የምንናገረውንም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እውነትን መመስከር፣ ትክክለኛ ሃሳብን መናገር፣ ነው ቁምነገር፡፡     

Read 423 times