Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 07:03

ሞኝ የተቆረጠ እሸት ይጠብቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የተራቡ ጅቦች በቡድን ሆነው በጠፍ ጨረቃ ምግብ ፍለጋ ይዘዋወራሉ፡፡ ብዙ ከተጓዙ በኋላ

አንድ ትልቅ ገደል ውስጥ ተንሸራቶ ወድቆ የሞተ ዝሆን ያያሉ፡፡ ገደሉ እጅግ አዘቅት የሆነ ገደል ነው፡፡

ጅቦቹ መመካከር ጀመሩ፡፡

ከፊሎቹ፤

“በረሃብ ከምናልቅ እንግባና ዝሆኑን በልተን ረሀባችንን እናስታግስ” አሉ፡፡

ከፊሎቹ ደግሞ፤

“የለም ጐበዝ! አሁን ስለራበን የሚታየን ሆዳችን ብቻ ነው፡፡ ስንገባ ቁልቁለት ስለሆነ ያለችግር ልንገባ እንችላለን

፡ ገብተን ዝሆኑን ከበላን በኋላ ግን ሆዳችን ይሞላና ቀጥ ያለውን የገደል ዳገት ለመውጣት ፈጽሞ አንችልም፡፡

ይቅርብን፡፡ ሌላ የሚበላ እንስሳ ብንፈልግ ይሻላል” አሉ፡፡

በመጀመሪያ እንግባና እንብላ ያለው ጅብ አሁንም ሙግቱን ቀጠለ:-

“እንግባ ነው እኔ የምለው፡፡ እንዲያውም ከበላን በኋላ ጉልበት እናገኛለን፡፡ ዳገቱ አያቅተንም” አለ፡፡

ቀስ በቀስ እንግባና እንብላ የሚሉት እየበዙ መጡና በድምጽ ብልጫ ገብተው ሊበሉ ተስማሙ፡፡

ሁሉም እየተንደረደሩ ገቡና ያንን ዝሆን መብላት ጀመሩ፡፡ እጅግ ግዙፍ ዝሆን ነበረና ቶሎ ጠገቡ፡፡ የተረፋቸውን

ሥጋ አስቀመጡ፡፡ ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ሌሊቱን ሲዘፍኑ፤ ሲጨፍሩ አደሩ፡፡

በሚቀጥለው ሌሊትም እንደዚሁ የተረፋቸውን እየተቀራመቱ ጠገቡና ዘፈኑ፡፡ ጨፈሩ፡፡

በሦስተኛው ቀን የተረፋቸውን አጥንት ሳይቀር እየቆረጠሙ ጠገቡ፡፡

አንደኛው ጅብ:-

“ጐበዝ! እንግዲህ ዝሆናችንን ጨርሰናል፡፡ እንውጣ” አለ፡፡

ቀና ብለው ያንን ገደል ሲያዩት ግን በጭራሽ የሚሞከር አልሆነም፡፡

”ግዴለም፡፡ ዛሬን እዚሁ እንደርና ነገ እናስብበታለን” ተባባሉ፡፡

ዳገቱ ግን በነጋታውም ያው ነው፡፡ የተመገቡት ጐደለና ረሃብ ይሰማቸው ጀመር፡፡

“አንዳችን በአንዳችን ትከሻ ላይ እየረገጥን ተደራርበን ብንወጣስ?” አለ፡፡

አንደኛው፡፡ ሆኖም ከሥር ሆኖ ሌሎቹን የሚያሻግር ፈቃደኛ ግን ጠፋ፡፡

ስለዚህ እዚያው ተኙ፡፡ ረሃቡ እየመዘለጋቸው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ቀናት እንደገፉ፣ አንድ ሌሊት አንድ

የነቃ ጅብ ጐኑ ያሉትን ጅቦች ተራ በተራ ይቀሰቅስና አንዱን ጅብ ግን እዚያው እንደተኛ ይተወዋል፡፡ ከዚያም፤

“ጐበዝ! በርሃብ ከምንሞት ይህን ያልነቃውን ጅብ ብንበላ ይሻላል” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡

ሌሎቹ ወዲያው ተስማሙ፡፡ ተቀራመቱት፡፡ ጠገቡ፡፡ ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ጭፈራቸውን ቀጠሉ፡፡

በነጋታው ግን የማይቀረው ረሃብ መጣ፡፡

ደሞ አንዱ ያንቀላፋ ጅብ ላይ ዶለቱና ተቀራመቱት፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ በመጨረሻ ሁለት ብቻ ቀሩ፡፡

አንዱ አንዱን እንዳይበላው እየፈራ ሁለቱም እንደፋጠጡ ያድራሉ፡፡ ረሀባቸው እየበረታ፣ አቅማቸው እየደከመ

መጣ፡፡

አንድ ሌሊት አንደኛው ጅብ ሸለብ እንዳደረገው በዛው ደክሞት ተኛ፡፡ ያልተኛው ወዲያውኑ በጫጭቆ እራቱ

አደረገው፡፡

የመጨረሻው ቀሪ ጅብ ከገደሉም መውጣት ሳይችል በረሃብ እንደተሰቃየ ሞተ!

*   *   *

አርቀን ባለማሰብ ወይም አርቀው የሚያሰቡ የሚነግሩንን ባለመስማት “ገብተን እንብላ” የምንልበት አካሄድ፤ ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ ከሚለው ተረት ውጪ አይደለም - እርስ በርስ ከመበላላት ይሰውረን! በጊዜያዊ ጥጋብና ፈንጠዝያ ያሸነፍነው የሚመስለን ርሃብ፣ ችግርና ፈተና፤ ነገ ፊታችን የሚደቀን የከፋ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ እየተቧደኑ በመዶለት ያልነቃውን ማጥፋት፤ “ነገስ በእኔ ቢደርስ?” ብሎ አለመጠየቅ፤ የሀገራችን ትልቅ አባዜ መሆኑን መመርመር ይገባናል፡፡ መንገኛ አስተሳሰብ የሃሳብ ልዩነትን እንዳናይና በአንድ ዓይነት አመለካከት ብቻ የዕለት የዕለቱ ላይ በማተኮር እንድንቀየድ ያደርገናል፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደጋሪ ፈረስ እንድንጓዝ ይከልለናል፡፡ ሀገራችን ከአንድ ርሃብ ወደሌላ ርሃብ እንዳትዞር አሳቢ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ ያገራችን ፀሐፌ - ተውኔት እንዳለው፤ “የአብዮት ጊዜ አይደለም እንዴ መጠፋፋት መች ገደደ?” ከምንባባልበት ምፀታዊ የፖለቲካ አረንቋ የምንወጣበት መድህን ያስፈልገናል፡፡

“የምንሠራው ነገር ለማን ይጠቅማል?” የምንልበት ሀገር ተኮር ህሊና ሊኖረን ይገባል፡፡ አንድን ግብ ለማሳካት ብለን አያሌ ስህተት እንዳንፈጽም በጥንቃቄ መራመድ ይኖርብናል፡፡ ከህዝብ ጋር የምንማከርበት ህዝብን የምናሳትፍበት፣ ልዩነቶችን የምናደንቅበት፣ ችግሮቻችንን በሠለጠነ መንገድ የምንፈታበት፣ መፍትሔው እኔ ብቻ ነኝ የማንልበት ዘመን ያምጣልን፡፡

የወደቀ ላይ መረባረብ ክፉ አባዜ ነው፡፡ የራስን ጥንካሬ አግዝፎ ማየት ሌላ ክፉ አባዜ ነው፡፡ የዛሬውን አግነን ለማሳየት በመሞከር ህዝብ ትላንትናን ናፋቂ እንዲሆን እንዳናደርገው መጠንቀቅ ዋና ተግባር ነው፡፡ የፖለቲካ መከፋት፣ የኢኮኖሚ መንኮታኮትና የባህል ዕሴቶች መሸርሸር ማህበራዊ ንቅዘት (degeneration) ማስከተሉን ለደቂቃም ቢሆን አለመዘንጋት ነው፡፡

ንቅዘት ቁልቁለት ነው፡፡ እያደር ዙሪያ ገባውን ሊያጥለቀልቅ የሚችል የተስፋ መቁረጥ አዘቅት ውስጥ ሊከት የሚችል አደጋ መሆኑን በለሆሳስ ማሰብ ያሻል፡፡ የእስካሁኑ አሉታዊነት (negativism) ሳያንስ ከንቅዘት ጋር የተዋሃደ አሉታዊነት ከታከለበት “ኦሮማይ!“ የሚያሰኝ ውድቀት ላይ ይጥለናል፡፡

አዝጋሚ የህብረተሰብ አስተሳሰብ መሸርሸር፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ምሬት፣ ግብረገብነት ማጣት፣ ጽንፈኝነት..ወዘተ የንቅዘት ልጅ - ልጆች ናቸው፡፡ አንዴ እዚህ አዙሪት ውስጥ የገባን ማህበረሰብ ወደነበረበት መመለስ ማህበራዊ ድርና ማጉን (Social fabric) እንደገና ወደ ጥሬው ጥጥ የመመለስ ያህል ከባድ ነው፡፡

ያለ እየመሰለን የሚያብረቀርቅ ዘመናዊነት እንዳያሞኘን ዐይናችንን መክፈት አለብን፡፡ አለበለዚያ “ሞኝ የተቆረጠ እሸት ይጠብቃል” የሚለው ተረት ዓይነት ይሆናል፡፡

 

 

Read 3678 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 07:18