Print this page
Tuesday, 02 July 2019 12:30

አድማስ ትውስታ ኢህአዴግ የዘራውን እያጨደ ነው

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

  (የዛሬ 17 ዓመት በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አደገኝነትና አጥፊነት ላይ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣ ጽሁፍ)
              ዮሐንስ ሰ.

       ቀደም ሲል በአምቦና በነቀምት አሁን ደግሞ በአምቦ የታዩት ህይወትን፣ አካልንና ንብረትን ለጥፋት የዳረጉ አሳዛኝ ክስተቶች ግራ ያጋባሉ፡፡ ከወር በፊት “ገበሬው ተበደለ መብቱ ተጣሰ፣ ብድር እንዲከፍል እየተገደደ ተቸገረ” የሚል ተቃውሞ ከወጣት ተማሪዎች ተሰማ - በነቀምት፣ አምቦ --:: ባለፈው ሳምንት ደግሞ፣ “የብሔር ብሔረሰብ መብት ተደፈረ፣ መሬቱና ከተማው ተነጠቀ” የሚል ተቃውሞ ከገበሬዎች ተሰነዘረ- በአዋሳ፡፡ ተቃውሞው ያነጣጠረው ኢህአዴግ ላይ መሆኑ ነው ግራ ሊያጋባ የሚችለው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲወጣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይዞ እንደመጣ አለም ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ሁለቱ ዋነኛ የኢህአዴግ መለያዎች፡-
የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካ
ገበሬንና ገጠርን ማዕከል ያደረገ ኢኮኖሚ የሚሉ ብሔርተኛ (ዘረኛ) እና ሶሻሊስታዊ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡
በአስተሳሰብ ብቻም ሳይወሰን ለ11 አመታት በትጋት ሲተገብራቸው እንደቆየ ለማንም ቀና ኢትዮጵያዊ አከራካሪ አይደለም - የኢህአዴግ ፖሊሲዎች፣ ህጐችና ተግባራት የሚመሰክሩት ነገር ቢኖር፣ የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካና ገጠርን ማዕከል ያደረገ ኢኮኖሚ ከሞላ ጐደል ተግባራዊ መሆናቸውን ነውና፡፡ ለነገሩ ለውጭው አለም ሳይቀር ግልጽ ሆኗል፡፡ ዋና ጽ/ቤቱ ለንደን የሆነው ማይኖሪቲ ራይትስ ኢንተርናሽናል ስለ ኢትዮጵያ ባሳተመው ሰፊ ዘገባ፤ ኢህአዴግ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ሙሉ ለሙሉ በህገ መንግስትና በሌሎች ህጐች አስፍሮ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በአለም “ተወዳዳሪ” እንደሌለው አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩልም ኢህአዴግ፣ የሚከተለውን ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲቀይር ከIMF እንዲሁም ከአሜሪካና ከአውሮፓ መንግስታት ለሚመጣበት ግፊት ሳይንበረከክ፣ ገበሬን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚተገብር ብቸኛው “ጀግና” መንግስት መሆኑ በስፋት ተነግሮለታል፡፡
እንዲህ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አራማጅነት አንደኛ የወጣ ለገበሬ ያደላ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተሉ “ስሙ የገነነ” ፓርቲ፤ “ገበሬን በደልክ፤ ብድር መልስ እያልክ ገበሬን አሰቃየህ፤ ለገበሬ ድጐማ ከለከልክ”፤ “የብሔር - ብሔረሰብ መብት ጣስክ፤ መሬታቸውንና ከተማቸውን ነጠቅህ” የሚል ተቃውሞ ሲሰነዘርበት አይገርምም? እሱም በተራው እንዲህ “ለገበሬና ለብሔር - ብሔረሰብ ተቆርቋሪ” ሆነው የሚቃወሙትን ወገኖች በከፍተኛ ጥላቻ ሲፈርጃቸው ግራ አያጋባም? በእርግጥም ላይ ላዩን ሲመለከቱት ክስተቱ ሊገርም እንዲሁም ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ በሚገባ ከተመረመረ ግን አሁን የምናያቸው ነገሮች የግድ መከሰት የሚኖርባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ “የዘራኸውን ታጭዳለህ” ነውና፡፡ የተሳሳተ፣ መርዘኛ እንዲሁም አጥፊ የሆነ የብሔር - ብሔረሰብ ዘረኛ ፖለቲካንና አጥፊ የሆነ ገጠርን ማዕከል ያደረገ ሶሻሊስታዊ ኢኮኖሚን መከተል ጤንነትንና ልምላሜን አያመጣም፡፡ በሰፈሩበት ቁና መሰፈር ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካንና ገጠርን ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ ፖሊሲን መስበክ የሚያመጣውን መዘዝ በዝርዝር ከማየቴ በፊት አንድ ነገር ላስቀድም:: መቸም የሰው ልጅን ለስልጣኔ ለማብቃት ወይም ለኋላቀርነት ለመዳረግ ተወዳዳሪ የሌለው ተጽዕኖ የሚያደርጉት በቁጥር ጥቂት የሆኑ ጥሩና መጥፎ ፈላስፎች ናቸው፡፡
ከመጥፎዎቹ ጋር የሚመደብ አንድ ፈላስፋ ነበር ይባላል፤ “ሰው ስለ ራሱም ሆነ ስለ አካባቢው እውቀት ሊኖረው አይችል፤ ሰው ስለምንም ነገር በእርግጠኛነት መናገር አይችልም” እያለ ያስተምር ነበር - ፈላስፋው፡፡ እንዲህ አይነት ፍልስፍና እርስ በርሱ እንደሚቃረን ግልጽ ነው፤ “እውቀት የሚባል ነገር እንደሌለ አውቃለሁ” እያለ ሲያስተርም “ሰው ስለ ምንም ነገር እንደማያውቅ አውቃለሁ” ብሎ ሲናገር፤ “ስለ ምንም ነገር በእርግጠኛነት መናገር አይቻልም” ብሎ በእርግጠኛነት ሲሰብክ፤ በተዘዋዋሪ ፍልስፍናው ስህተት እንደሆነ እየተናዘዘ ነው፡፡ እናም ብዙ ሰዎች የፈላስፋውን ትምህርት አልተቀበሉትም፤ በተለይ የፈላስፋው ጐረቤት የሆነ አንድ ገበሬ በጣም ይቃወመው ነበር፡፡ ይሁንና ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኘ መጣ፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ ጥፋት ከሰሩ በኋላ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የፈላስፋውን ትምህርት እንደ ማመካኛ ይጠቀሙበት ጀመር፤ “እንዲህ አይነት ወንጀል ሰርተሃል፤ እንዲያ ዓይነት ስህተት ፈጽመሃል” የሚል ክስና ነቀፋ ቢሰነዘርባቸው፤ “እንዴት አወቃችሁ? እርግጠኛስ ናችሁ? ሰው ማወቅ አይችልም፤ ስለ ምንም ነገር በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም” ብለው መከራከር እንደሚያዋጣቸው አስበዋልና፡፡ የፈላስፋው ደጋፊ ሆኑ ማለት ነው፡፡ ገበሬው ጐረቤቱም እንዲሁ “እውቀት የለም፤ እርግጠኝነት የለም” ማለት ጀመረ:: በዚህም በዚያም የፈላስፋው መርዘኛ አስተሳሰብ በስፋት ተቀባይነት አገኘና አሸናፊ ሆነ፡፡ ድል አደረገ፡፡ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሰረፀ፤ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ቋንቋ የፈላስፋው አስቀያሚ አስተሳሰብ “ገቢ” ሆነ - (Garbage in እንዲሉ)፡፡ ብዙም ሳይቆይ አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ ፈላስፋው ከጐረቤቱ ከገበሬው ፍየል ሰረቀና ወደ ገበያ ወስዶ ሸጠው፡፡ ነገሩ፤ በብዙ ሰው ስለታየ ከገበሬው ጆሮ ለመድረስ ጊዜ አልፈጀበትም፤ ገበሬውም መርዶውን እንደሰማ የፍየሉን ዋጋ ለማስመለስ ወደ ፈላስፋው ቤት ገሰገሰ:: “ፍየሌን ሰርቀህ ሸጠሃል፤ ካሳ ትከፍላለህ፤ ከዚያም ለፈፀምከው ወንጀል ትቀጣለህ” አለ - ገበሬው፡፡ ፈላስፋው ግን ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በዝምታ አየውና በፌዝ ሳቀ፡፡ ባለ ፍየሉ ገበሬ ተናድዶ፤ “የፍየሌን ዋጋ ትከፍላለህ” በማለት ሲያንባርቅበት፣ ፈላስፋው ተረጋግቶ “ለምን እከፍላለሁ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ፍየሌን ሰርቀህ ሸጠሃል”
“እርግጠኛ ነህ? ለመሆኑ እንዴት አወቅህ?”
ገበሬው ተደናገጠ፡፡
“ብዙ ሰዎች አንተ ሰርቀህ እንደሸጥህ ነግረውኛል”
“እነሱስ እንዴት አወቁ?”
“አይተውሃላ”
“እንዳዩኝ እርግጠኛ ናቸው? ሰው ማወቅ አይችልም፤ ስለ ምንም ነገር በእርግጠኛነት መናገርም አይችልም፡፡ አይደለም እንዴ?”
ገበሬው ይህን ሲሰማ ተስፋ ቆረጠ፤ የፈላስፋውን ትምህርት ተቀብሎ “እውቀት የለም፤ እርግጠኛነት የለም” ሲል ሰንብቷልና፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ እንደማይችል በማሰብ እጅግ ተበሳጭቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ጉዞ ሲጀምር፣ አዲስ ሃሳብ ብልጭ አለለትና እየተንደረደረ ወደ ፈላስፋው ተመለሰ፤ ዘልሎ ተከመረበትና እጁን ጠመዘዘው፡፡
ፈላስፋው ራሱን ለመከላከልም ሆነ ለመሸሽ ጊዜ አልነበረውም፡፡
“ጤና የለህም፤ እጄን ጠመዘዝከኝኮ” ሲል ግራ በመጋባት ጮኸ፡፡
ገበሬውም በፌዝ፤ “እጅህን ጠመዘዝኩህ? እርግጠኛ ነህ?” እያለ ይበልጥ ጠመዘዘው፡፡
“ኧረ…ኧረ በጣም ያማል”
“ያማል?...እንዴት አወቅህ?”
“ኧረ…ኧረ…” በሚል የፈለላስፋው የስቃይ ጩኸት መሀል “ቋ፤ ቀሽ” የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡
“ኦ…እጄን እጄን…ሰበርከው”
“እርግጠኛ ነህ? አስታውስ እውቀት የለም፤ እርግጠኛነት የለም” አለ ገበሬው፡፡
“አ..አ፣ እሱስ አዎ…የለም” አለ - ፈላስፋው፡፡ የሰበከው መርዘኛ አስተሳሰብ ድል አድርጐ በሌሎች ሰዎችም ታምኖበት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ፤ ሰዎቹ ያስተማራቸውን ነገር ሲተገብሩ ውጤቱ ሽንፈት ሆነበት፤ አስተሳሰቡ አጥፊ ከሆነ “በድል ወቅት ከሚመጣ ሽንፈት” አያመልጥም፡፡ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ቋንቋ `Garbage in garbage out (Gigo)` ይሉታል - በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም እንደሚባለው፡፡ የዘራኸውን ታጭዳለህ ነው ነገሩ፡፡ ፈላስፋው የዘራውን እንዳጨደ ሁሉ፤ ኢህአዴግም ለአስር አመታት ሲዘራ የነበረውን ማጨድ ከጀመረ ከራርሟል፡፡
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ
በእርግጥ የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካ የኢህአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ በ1960ዎቹ በአገራችን፤ አብዮተኛ የተባለ ምሁር ሁሉ፤ ኢህአፓን፣ ህወሓትን ደርግን ጨምሮ አብዮተኛ ተብለው የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች  በሙሉ “የብሔር ጭቆና” ሲፈፀም ቆይቷል ይላሉ፡፡  “የብሔር ጭቆና” ሲሉ “ስልጣን ላይ የነበሩ ነገስታት ወይም ሌሎች ገዢዎች፣ ሰዎችን በተግባራቸውና በባህርያቸው ሳይሆን በዘር መዝነው እየለዩ አድልዎና በደል ይፈጽሙ ነበር፤ ማለትም በዘረኝነት አስተሳሰብ እየተመሩ የሰው መብትን ይጥሱ ነበር” ለማለት ከሆነ ትክክል ናቸው:: ይሁንና “የችግሩ መፍትሔ የዘር ግንድን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ፤ ደምና አጥንትን መመዘኛ የሚያደርግ ዘረኛ የፖለቲካ አስተሳሰብንና አሰራርን ማስወገድ” እንደሆነ አያምኑም፤ አብዮተኞቹ፡፡
የዘር ግንድን የማያይ አስተሳሰብ
“ሁሉም ሰው አንድ አይነት መብት አንድ አይነት የመኖር፤ የማሰብ፣ በነፃ የመንቀሳቀስ፤ የመናገርና የመጻፍ፣ የመስራት፣ ንብረት የማፍራትና በብቸኝነት የመጠቀም የንብረት ባለቤትነት መብቶች አሉት፡፡ የመንግስት ተግባርም በህግ መሰረት የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ መብት ማስከበርና ማክበር ነው - የዚህ ወይም የዚያ ዘር ተወላጅ ነው ሳይል፡፡ ያኔ ዘረኝነት ወይም (“የብሔር ጭቆና” የሚባለው ነገር) ከፖለቲካ ይጠፋል፡፡ መንግስት በማንኛውም መስክ ለሁሉም ሰው በሚሰራ ህግ የሚመራና የሰዎችን የቆዳ ቀለም የማያይ (Color blind) መሆን አለበት እንደሚባለው ሁሉ፣ የዘር ግንድንም የማያይ መሆን ይገባዋል፡፡ “ይሄ ሰውዬ የየትኛው ብሔር ተወላጅ ነው?” እያለ የማይጠይቅ መሆን አለበት -
እያንዳንዱ ሰው የዚህ ብሔረሰብ ወይም የዚያ ዘር በመሆኑ የሚጨምርለትም ሆነ የሚቀንስበት መብት እስከሌለ ድረስ ወይም በሌላ አነጋገር በዘረኛ አስተሳሰብ፤ ሰውን በዘር መዝኖ አድልዎ ለመፈፀም እስካልታሰበ ድረስ መንግስት ዘርን የሚያይበት፣ የብሔር- ብሔረሰብ ተወላጅነትን  የሚጠይቅበት አንዳች ምክንያት የለውም፡፡ እናም ዘረኝነት የማያውቀው ስርዓት ይፈጠራል፡፡”  
የ1960ዎቹ አብዮተኞች ግን እንዲህ አይነት ዘርን የማያይ የፖለቲካ አስተሳሰብን ለመከተል አልመረጡም፡፡ “የብሔር - ብሔረሰብ መብት፤ የብሔር - ብሔረሰብ እኩልነት” የሚሉ መፈክሮችን ነው ያነገቡት፡፡ የመፈክራቸው ትርጉም ምን እንደሆነ በቀላሉ ማየት ይቻላል፡፡ አንድ ሰው ዘር እየቆጠረ ጓደኞችን ለመያዝ፤ ወይም ዘሩ ተቆጥሮለት ለጓደኝነት እንዲመረጥ ቢመኝ መብቱ ቢሆንም፤ የራስ አክብሮት የሌለው፤ በራሱ የማይተማመን፤ አእምሮውን በማደንዘዙ ሰዎችን በአስተሳሰባቸው፤ በተግባራቸውና በባህርያቸው ጥሩና መጥፎ ብሎ የማይመዝን ቀፎ፤ ምግባረ ብልሹነቱን ብኩንነቱንና ቀፎነቱን በዘር ግንድ እንዲካካስለትና እንዲሞላለት የሚፈልግ ተባይ ነው፡፡ እርባና ቢሱ “ተባይ” ተመልሶ “ሰው” ሊሆን የሚችለው ዘረኝነቱን የተወ እንደሆነ ብቻ ስለሆነ ጓደኝነት በዘር (በብሔር ብሔረሰብም) አይደለም ብለን ልንመክረው እንችላለን፡፡ ሳናስገድደው፡፡ የ60ዎቹ አብዮተኞች ምክር ግን ከዚህ ይለያል - “ጓደኞችን ስትይዝ የብሔር ብሔረሰብን መብትና እኩልነት አክብር፤ ሁለት ከኦሮሞ ተወላጅ፤ ሁለት ከአማራ ተወላጅ፤ ሁለት ከትግራይ፤ ሁለት ከሶማሌ - ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ በእኩልነት፤ ኮታ በመመደብ ሁለት ሁለት ተወላጆችን በጓደኝነት ትመርጣለህ - የብሔር ብሔረሰብ መብት ነውና” የሚል ነው ምክራቸው:: በሌላ አነጋገር “ጓደኝነት በዘር እየታየ መሆን አለበት - ሁለት ከዚህ ሁለት ከዚያ፡፡ ዘርን የማታይ ሳትሆን ዘርን የምትቆጥር ሁን” ማለታቸው ነው፡፡ ምክራቸው፤ ዘረኝነት በሌላ ዘረኝነት እንዲተካ ነው፡፡
የአብዮተኞቹ ፖለቲካ ሲታይም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ዘርን፤ ብሔር - ብሔረሰብን እስከናካቴው ከፖለቲካ እንደማውጣት ጭራሽ በጣም አስፈላጊ ነገር አደረጉት፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በተግባር አዋለው፡፡ በህገ መንግስት “ብሔር - ብሔረሰብ ዘር” ልክ ህይወት እንዳላቸው አንዳች ፍጡር ሆነው ቀረቡ፡፡ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች…” ይህን ህገ መንግስት አጽድቀናል ተብሎ ተፃፈ - ብሔር ብሔረሰቦቹ በየትኛው እጃቸው እንደፈረሙ ባይገልጽም፣ መሬት የብሔር - ብሔረሰቦች ነው ተባለ፡፡ እናም የዚህ ብሔር ክልል፤ የዚያ ብሔረሰብ ከተማ፤ የእገሌ ዘር ዞን፤ የአንቶኔ ጐሳ ልዩ ወረዳ፤ እየተባለ ተቋቋመ:: ለሹመት፤ ለትምህርት፤ ለስራ የብሔር ተዋጽኦ ማመጣጠን ያስፈልጋል - ተባለ - ሁለት ከዚህ፤ ሁለት ከዚያ፡፡
የብሔር ብሔረሰብ ዘረኛ ፖለቲካ በሁሉም በኩል ተንሰራፋ፡፡ ሚዲያውም ትምህርት ቤቶችም በዚሁ መንገድ ተሰማርተው ዘመቱ፡፡ ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ ሳያጋጥመው የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ድል አደረገ፡፡ ይኸው ዛሬ በፓርላማ ስብሰባ “ለዚህ ብሔር ሹመት ተሰጠ፤ ከዚያ ብሔረሰብ ግን አነስተኛ ነው” ብሎ መከራከር የተለመደና መደበኛ ሆኗል፡፡ ክርክሩ በብሔር ብሔረሰብ አያቆምም፡፡ ወደ ክልል ወረድ ብትሉ “አንድ ብሔረሰብ” የተባለው ነገር በ50ና በ60 ጐሳ ይከፋፈልና “የኛ ጐሳ አልተሾመም፤ የዚያ ጐሳ ግን አስተዳዳሪ ሆነ” የሚል የጦፈ ጥል ይፈጠራል፡፡ በአውራጃና በወረዳ፤ በቆላና በደጋ፤ በዘርና ጐሳ መናቆር ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በቀበሌና በቀዬ፤ ከጐሳም አልፎ በ7 ትውልድ ይሄ በእውነት እየተፈፀመ የሚኝ አስፈሪና አሳፋሪ ነገር ነው፡፡
ፖለቲካው ሁሉ ዘር፤ ብሔር - ብሔረሰብ ሆኗል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በዘር ተቧድኖ “የራሴን ክልል ልመስርት፤ ዞን ይቋቋምልኝ፤ ልዩ ወረዳ ይሰጠኝ፤ ይሄ መሬት የኛ ነው፡፡ ያ ከተማ ለኛ ይገባል” ማለት እንደ ፋሽን ተይዟል፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በፈለገውና በተመቸው የአገሪቱ ክፍል የመኖር መብትን በሚያሳጣ አስተሳሰብ  “መሬት የብሔር - ብሔረሰቦች ነው” ተብሏል፡፡ ታዲያ እዚህም እዚያም የዘር፤ የጐሳ ግጭቶች ሲከሰቱና የሰዎች ህይወት ቢቀጠፍ ቢረግፍ፤ አካል ቢቆረጥ ቢጐድል፤ ንብረት ቢቃጠል ቢወድም ይገርማል? ግጭቶቹ ደግሞ እየተከሰቱ ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው በሚያስፈራ መጠን በብዛት እየተቀፈቀፉ፤ እየፈሉ ናቸው፡፡ በዘር ተቧድነው “ልዩ ዞን እንዳልመሰርት፤ ልዩ ወረዳ እንዳላቋቁም ተከለከልኩኝ፤ ከተማዬን ተነጠኩኝ” የሚሉት መዥገሮች እርስ በርስ በሚያቀጣጥሉት ጠብ እየተጨፋጨፉ ሌላውን ጤናማ ዜጋ ወደ ጥላቻ ሲጐትቱት፤ በጅምላ ለሞትና ለአካለ ጎደሎነት፤ ንብረቱን አሳጥተው ለችግርና ለስደት ቢዳርጉትስ ይገርማል? ባለፉት ሦስት አመታት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
 እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በፈለገው የአገሪቱ ክፍል የመኖር አንድ አይነት መብት እንዳለው የማይቀበሉ አእምሮ ቢስ መዥገሮች፤ “በኔ ብሔር ክልል፤ በኔ ብሔረሰብ ዞን፤ በኔ ዘር ከተማ የምትኖረው በኔ ዘር ቸርነት ነው” ከማለትም አልፈው “ካሰኘኝ፤ ከፈለግኩ አስወጣሃለሁ” እስከማለት ሲደርሱስ? ጭራሽ ከተማ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ማለት፤ እያንዳንዱ ዜጋ በተፈጥሮ የተቀዳጀውን አንድ አይነት ሰብአዊ መብት ተከብሮለት በነፃነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተብለው የተዋቀሩ መንግስታዊ ተቋማት መሆናቸው ቀርቶ “የዚህ ብሔር የዚያ ብሔረሰብ፤ የእገሌ ዘር” ተብለው ስለተሸነሸኑ፤ “ከኔ ዘር ክልል ወረዳና ከተማ ውጣ” የሚል የዘር ማጽዳት ለማካሄድ የሞከሩና እልቂትን ያስከተሉ ባለ ረዣዥም ጥፍር መዥገሮችም እየታዩ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ “የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካ” ያስከተለው አደጋ ነው፡፡
የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ይሄው አደጋ በጊዜ ካልተገታ መዘዙ ምን ያህል ዘግናኝ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ አይከብድም፡፡ ማሰብ የሚከብደው ካለም ከቅርብና ከሩቅ ምሳሌዎች አሉለት፡፡ ዩጐዝላቪያ አለለት፤ ከፈለገም ሩዋንዳ አለለት፡፡ በዘረኛ አስተሳሰብ ሳቢያ በተፈጠረ የአውሬ ባህሪ በሦስት ወራት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሰው አልቋል - በቀን አስር ሺህ ሰው ማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እልቂት የሚፈፀመው አእምሮአቸውን አደንዝዘው፤ የራስ አክብሮት አጥተው ራሳቸውን በሚንቁ፤ የናቁትን ቆሻሻ ሰብዕና በዘረኝነት ለመሸፋፈን በሚቋምጡ ጥቂት፤ በጣም ጥቂት ተባዮችና መዥገሮች አማካኝነት ነው፤ ምክንያቱም የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካ ተቀባይነት አግኝቶላቸዋል፡፡
ይህ ዘግናኝ አደጋን ለማስወገድና በሰላም የብልጽግና ህይወት ለመኖር በመጀመሪያ የብሔር - ብሔረሰብ ፖለቲካን ከስር መሰረቱ ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ሰው ሊያስብበት ይገባል - ኢህአዴግም፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም፣ ምሁራንም፤ ጋዜጠኞችም በአጠቃላይ ሁሉም ዜጋ፡፡
(አዲስ አድማስ ግንቦት 24 ቀን 1994 ዓ.ም)


Read 1536 times