Print this page
Monday, 01 July 2019 00:00

የዶክተሮች ቀን ማክሰኞ በኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይከበራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በዓለም ለ38ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው የዶክተሮች ቀን ማክሰኞ ጠዋት በጳውሎስ ሆስፒታል ከሰዓት በኋላ ከ11፡30 ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ የኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች በራስ ሆቴል እንደሚከበር የኢትዮጵ ህክምና ማህበር አስታወቀ፡፡
በጠዋቱ መርሃ ግብር ህክምና ማህበሩ ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ታካሚዎች፣ የታካሚ ቤተሰቦችና የታካሚ ህፃናት ወላጆች ሃኪሞቹ ለቤተሰቦቻቸው ላደረጉት ህክምናና ቤተሰባዊ እንክባኬ ዶክተሮችን የሚያመሰግኑበትና ተካሚዎች ገጠመኞቻቸውን ለታዳሚዎች እያወጉ የሚጨዋወቱበት ፕሮግራም የተሰናዳ ሲሆን፣ በከሰዓቱ የራስ ሆቴል መርሃ ግብር የስነ ፅሁፍ የወግና የዘፈን ተሰጥኦ ያላቸው ዶክተሮች ለታዳሚዎች ስራቸውን እንደሚያቀርቡ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ሚዲና ኮሚዩኒኬሽን ኦፌሰር አቶ አባተ ሀይሉ ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያንና ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝን ጨምሮ በርካታ ዶክተሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚታደሙ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገንና ሌሎች ሁለት አርቲስቶች ግጥም እንደሚያቀርቡም ታውቋል፡፡ መድረኩም በማህበሩ የወጣት ሀኪሞች ፕሬዚዳንት ዶ/ር ልዕልና ሽመልስ ይመራል ተብሏል፡፡
በ1954 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ከ4ሺ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በየዓመቱ በዓለም የዶ/ሮች ቀን ሲከበር በኢትዮጵያ ግን ቀኑ አለመኖሩን የገለፁት ኦፊሰሩ ማህበሩ ቀኑ በኢትዮጵያ እውቅና ተሰጥቶት እንዲከበር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብቶ ምላሽ እየጠበቀ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በማህበሩና በአባላቱ ተነሳሽነት የዶ/ሮች ቀን መከበር መጀመሩን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 3954 times