Print this page
Saturday, 06 July 2019 12:42

መልክቶቻችሁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዓይን ያወጡ ዘራፊዎች መጽሐፌን በዶላር እየቸበቸቡት ነው!


       በአሜሪካ የሚገኙ “መረብ” እና “መሰሌ”  የተባሉ የመፅሐፍ ሽያጭ ጉልበተኞችን ሃይ የሚላቸው ማን ነው? በቅርቡ “ጋሻው፤ ታሪካዊ ልብወለድ” የተሰኘ መፅሐፍ አሳትሜ፣ እዚህ ኢትዮጵያ ለሽያጭ አቅርቤ ነበር፡፡ የመፅሐፉ ዋጋ ለአገር ውስጥ 125.00 ብር ሲሆን  ለውጭ አገራት በ25 ዶላር ነው የቀረበው::  ከተፎዎችና ልማደኞች የመረብ መፅሐፍ ሻጮች፣ በአሜሪካ በonline መጽሐፌን በ10.99 ዶላር ለመሸጥ አስተዋውቀዋል፡፡ እኔ በሌላ አቅጣጫ፣ ይህን ከማወቄ በፊት መፅሐፌን አንዳንድ እርማቶችና ማስተካከያ አድርጌ፣ አሜሪካ ለመሸጥ ባቀርበው፣ ጉልበተኞች ቀደም ብለው ዋጋ ሰብረው ስላቀረቡት፣ ሊሸጥልኝ  አልቻለም፡፡
እነኝህን መሰል ብልጣ ብልጥ ጉልበተኞችን፣ የአሜሪካን ህግ ሃይ የሚላቸው አይመስለኝም፡፡ እንደውም የሚደግፋቸው መሆኑን ነው የተረዳሁት:: ህጉ ከአሜሪካ ውጭ የሚመጡ የማንንም አገር እቃና መፃሕፍት ባገኙት ዋጋ እንዲሸጡ  የሚፈቅድ ነው፡፡ ISBN እንዳላወጣ ደግሞ በእኛ አገር ኢኮኖሚ ውድ ነው፡፡ ደግሞም በአሜሪካን የሚሸጡ አብዛኞቹ የአገራችን መፅሐፍት ይህንን ቁጥር አያወጡም፡፡
አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል እንደሚባለው፤ ከኢንተርኔት መረጃ ስበረብር፤ ከዚህ ቀደም ያሳተምኩትን “ጋቦና ዋራንት፡ የቀይ ሽብር እስር ከሶደሬ እስከ ከርቸሌ” የሚለውንም ሌላ መፅሐፌን በተመሳሳይ መንገድ በዶላር እንደቸረቸሩት ተገነዘብኩ፡፡
ይገርማችኋል፤ የዚህ የመፅሐፍ ዘረፋ ተጠያቂ የምንሆነው አገር ቤት ሆነን መፅሐፍ የምናሳትም ጸሃፍት ነን፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩት እዚያው ስለሚከታተሏቸውና ISBN በቀላሉ ስለሚያወጡ  አይደፍሩም፡፡
እነኝህን መሰል በውጭ አገር ያሉ ጥገኞች፣ አገር ቤት ግንኙነታቸው ከእነማን ጋር እንደሆነ የሚታወቅበት መንገድ አይታወቅም፡፡ በዚህም ባለቤቶቹ ደራሲያንና አሳታሚዎች ሳይጠቀሙ፣ እነሱ የሰው መጽሃፍ  እየቸበቸቡ ዶላር ያፍሳሉ:: እንደው ግን እነዚህን ዓይን የበሉ ህገ ወጦች የሚዳኛቸው ማን ይሆን? እንዲህ እየዘረፉ የሚቀጥሉትስ እስከ መቼ ነው?
ይህንን አጭር ማስታወሻ ሁሉም እንዲያውቀውና እንዲጠነቀቅ በሚል ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ከመላኬ በፊት “መፅሐፌን ዋጋ ሰብራችሁ እንድትሸጡ ማን ፈቀደላችሁ?” ብዬ በኢሜይል ጠይቄያቸው ነበር፡፡ ግን  ክመጤፍም አልቆጠሩኝም::  በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ፣ ከኮፒ ራይት ጥሰት ጋር ተያይዞ የደረሰው አሳዛኝ ውድቀትና ድቀት፣ ወደ ሥነጽሁፉና መጻህፍትም የማይመጣበት ምክንያት አይታየኝም፡፡  
ዛሬ በአሜሪካ ተጀምሯል፡፡ የጥበብ ቤተሰቦች በጊዜ ነቅተው፣ ህገ ወጥ ዘረፋውን ለመከላከል ካልተቻለ፣  መጽሐፍ አሳትሞ ለአንባቢ ማቅረብ ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም፡፡
ደራሲ ዶ/ር


Read 1138 times
Administrator

Latest from Administrator