Monday, 08 July 2019 00:00

የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ ላይ የቀረበ ሒሳዊ አስተያየት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

(ክፍል-፭ ‹‹በተዋህዶ ከበረ››)

                    የፖለቲካል ኢኮኖሚ አንደምታዎቹና የግለሰብ ዕጣ ፈንታ


         በክፍል-4 ፅሁፌ ላይ ሁለት ዋና ዋና ሐሳቦችን ማንሳታችን ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያው፣ እጓለ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ››ን ሐሳብ ባቀረበበት ወቅት ሀገራችን ስትከተል የነበረው የዘመናዊነት ሐሳብ አስቀድሞ የ50 ዓመታት ጉዞ እንደተጓዘና በዚህ ጉዞውም ትውፊታዊው እሴትና ባህላዊ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተመልክተናል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ የእጓለ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ሐሳብ ህሊናንና መንፈስን፣ አመክንዮንና እምነትን፣ ፍልስፍናንና ሃይማኖትን የማስታረቅ ፕሮጀክት እንደሆነና ይሄም ሐሳብ የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስትያን አባቶች ሲወያዩበት እንደነበርና ሐሳቡንም እጓለ ከ1600 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ለውይይት እንዳነሳው ተመልክተናል፡፡ በዛሬው የማጠቃለያ ሐሳብ ደግሞ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፖለቲካዊ ወይስ ፍልስፍናዊ መፍትሔ? የሐሳቡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንደምታዎቹስ ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች እንዳስሳለን፡፡
‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› - ፖለቲካዊ ወይስ
ፍልስፍናዊ መፍትሄ?
እጓለ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ ለዘመናት የጥቅምን ነገር ችላ ብሏል›› ያለው ነገር ትክክለኛ ግምገማ ቢሆንም፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ ብሎ ያመጣው ‹‹ከአውሮፓ የመዋስ›› ሐሳብ ግን ከፖለቲካ አንፃር ካልሆነ በስተቀር፣ ከፍልስፍና አንፃር ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለው ሐሳብ መልስ ሆኖ የሚመጣው ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ ቴክኖሎጂ መፍጠር አልቻለም፤ ታዲያ ምን ይሻላል?›› ለሚለው ጥያቄ እንጂ፣ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ እንዴት ቴክኖሎጂን መፍጠር ተሳነው?” ለሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ ፖለቲካዊ ሲሆን፣ ተከታዩ ደግሞ ፍልስፍናዊ ነው፡፡
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የባህል ችግር ሲኖር፣ ችግሩ የሚቀረፍበትን አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ የፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን፣ የችግሩን ስረ መሰረት ፈልፍሎ ማግኘት ግን የፍልስፍና ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አንፃር፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለው የእጓለ ሐሳብ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንጂ ፍልስፍናዊ ሥረ መሰረት ያለው አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ የተጠቃሚነት እሴት ይጎድለዋል›› የሚለው የእጓለ መደምደሚያ፣ ፖለቲከኞችን በቀጥታ የሚወስዳቸው ‹‹ታዲያ ምን ይሻላል?›› ወደ ሚል አፋጣኝ የመፍትሄ ሐሳብ ሲሆን፣ ፈላስፋዎችን የሚወስዳቸው ግን ‹‹የችግሩ ሥረ መሰረት ምንድን ነው? ሥልጣኔያችን እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እዚህ ችግር ላይ ሊወድቅ ቻለ?›› ወደ ሚል ትልቅ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የሥነ ማህበረሰብና የፍልስፍና ሐሰሳ ነው፡፡
ፈላስፋዎች ለአንድ የባህል ችግር መፍትሄ የሚያቀርቡት፣ በመጀመሪያ የችግሩን ሥረ መሰረት ካገኙት በኋላ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ እጓለ ‹‹ያሬዳዊው ሥልጣኔ›› አሁን ላይ ያለበትን ጉድለት ያሳየን ቢሆንም፣ የችግሩን ሥረ መሰረት ግን ወደ ኋላ ወደ ሥልጣኔው መሰረት ሄዶ ሳያስስ ነው ያለፈው፡፡
ምናልባት፣ እጓለ ይሄንን ያላደረገበት ምክንያት ‹‹ምሁራዊ ወገንተኝነት›› ተጭኖት ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም፣ እጓለ በመፅሐፉ ውስጥ ወቅታዊ ሁኔታዎችን (ለምሳሌ፣ አውሮፓ አሁን ላይ ለታላቅ ሥልጣኔ የበቃበትን ምክንያት በተመለከተ መነሻውን) ወደ ኋላ እየሄደ ከሥረ መሰረታቸው ጀምሮ በጊዜ ሂደት ውስጥ ያሳዩትን ለውጥና ዕድገት የዘገበ ቢሆንም፣ ይሄንን አቀራረብ ግን ‹‹ህፀፅ (ጉድለት) አለበት›› ላለው ለያሬዳዊው ሥልጣኔ ሲጠቀመው አይታይም፡፡
‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የፖለቲካል ኢኮኖሚ አንደምታዎቹና የግለሰብ ዕጣ ፋንታ
እጓለ በአንድ በኩል ከአውሮፓ ትምህርትና ቴክኖሎጂ ጋር እንድንተዋወቅ ይፈልጋል፤ በሌላ በኩል ግን፣ ያሬዳዊው የህይወት ክፍል (ባህሉ፣ ሥነ ምግባሩ፣ ሃይማኖቱ፣ ፖለቲካው…) በሙሉ በፊት በነበረው ትውፊታዊ አኗኗርና አስተሳሰብ እንዲቀጥል ይፈልጋል።
እጓለ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለውን የመፍትሄ ሐሳብ ያመጣው በያሬዳዊው ሥልጣኔ ውስጥ ለዘመናት አልፈታ ያለ አንድ መሰረታዊ ችግር እንዳለ ስለተረዳ ነው - ይሄውም የህሊና መንገድ መበደሉና የዚህ ውጤትም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ ነው፡፡ ይሄም የሚያመላክተን ‹‹በተዋህዶ ከበረ›› ፍልስፍናዊ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካል ኢኮኖሚ አንደምታዎችም እንዳሉት ነው::
ሆኖም ግን፣ እጓለ እነዚህን አንደምታዎች አስቀድሞ ያያቸው አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ከአንደምታዎቹ መካከል ጉልህ ሆኖ የሚወጣው ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፕሮጀክት ውስጥ የአውሮፓ ህሊናና የያሬዳዊው እምነት አልጣጣምላቸው ያላቸው ዜጎች ቢኖሩ ምንድን ነው የሚሆነው? የሚለው አንዱ ነው፡፡
እጓለ ለዚህ ጥያቄ ያዘጋጀው መልስ ምናባዊ ነው - ‹‹በመጀመሪያ የራሳቸውን ሀገር በቀል ዕውቀት በደንብ አላምጠው መዋጥ የቻሉ ሰዎች፣ ምዕራባዊው ትምህርት ምንም ሊያናውጣቸው አይችልም›› የሚል ግምት፡፡ ሆኖም ግን፣ እጓለ እንደ ገመተው ባይሆንስ? ህሊናና መንፈስ፣ አመክንዮና እምነት፣ ፍልስፍናና ሃይማኖት የሚጋጭባቸው ዜጎች ቢመጡስ? በአውሮፓውያኑ ትምህርት የተነሳ ትውፊታዊው እሴት ላይ የሚያምፁ ወጣቶች ቁጥራቸው እየጨመረ ቢሄድ፣ የ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፕሮጀክት ምላሹ ምን ይሆናል? እነዚህ ጥያቄዎች ናቸው የ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፕሮጀክት፤ የግለሰብ ነፃነት፣ የመንግስት ባህሪና የኢኮኖሚ አቅጣጫውን በተመለከተ በውስጥ (implicit) ያለውን አቋም ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን፡፡
‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ዋነኛ ጭንቀቱ፣ የያሬዳዊው ሥልጣኔ ማህበራዊ እሴቱ (Collective Morality) ሳይፋለስ ከአውሮፓ ህሊና የሚጣመርበትን መላ መፈለግ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ እጓለ እንዳሰበው ባይሆንና በምዕራባዊው ትምህርት የተነሳ የያሬዳዊው ሥልጣኔ ማህበራዊ እሴቶች ላይ የሚያምፁ ዜጎች ቁጥራቸው እየበዛ የሚሄድ ከሆነ፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ያን ጊዜ መንግስት ክንዱን በማፈርጠም የትውፊታዊው እሴት ጠባቂ ሆኖ እንዲነሳ ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ አይቀርም። በመሆኑም፣ ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለው የእጓለ ሐሳብ በስተመጨረሻ ግለሰብን በማቀንጨር ለአምባገነን መንግስት አሳልፎ ይሰጠናል። እናም፣ ፕሌቶናዊ ሐሳብ የሚጫነው ይህ የእጓለ ፕሮጀክት፣ ግለሰብን ለትውፊታዊው እሴት መስዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። እናም፣ በእጓለ የ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፕሮጀክት ውስጥ የግለሰብ ዕጣ ፈንታ አሳዛኝ ነው።
‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› በማህበረሰባዊ እሴት ጠባቂነትና በምዕራባዊው የህሊና አንክሮ መካከል የያዘው መንታ ልብ፣ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አቋሙ ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ‹‹በምስራቅ አፍሪካ ዳርቻ ሰማይ ላይ፡- የእጓለ ገብረ ዮሐንስ የፍልስፍና መንገድ›› በሚለው ፅሁፉ ውስጥ አቶ ዮናስ ታደሰ፣ ይሄንን ተፅዕኖ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፣
እጓለ ማርክሲዝምን በአንድ ሐረግ ‹‹ሕልም ነው›› በሚል ከምርጫ ውጭ ያደርገዋል። በመሆኑም፣ የ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ዋነኛ ችግሩ የሚያራምደው የሥነምግባር ሐሳብ (Morality) ላይ ነው። ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የማርክሲዝምን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ባይቀበልም የማርክሲዝምን የጋርዮሽ ሞራሊቲን (collectivist morality) ግን የተከተለ በመሆኑ፤ የግለሰብ ነፃነትና ሞራሊቲ በጣም የተገደበበት ካፒታሊስታዊ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት መምረጡ አይቀርም፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ፣ የግለሰብ ነፃነት ቢጠፋም ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች፣ ፈጣን ባቡሮች፣ ሰፋፊ እና ጥልፍልፍ መንገዶች ይኖረናል ማለት ነው። በአጭሩ አሁን እጓለ በሕይወት ቢኖር ኖሮ የሚነግረን ነገር ‹‹ቻይና እንሁን የሚል ነበር። በዚህም የተነሳ (አሁን ባለንበት የሊበራል ዲሞክራሲ ዓለም ውስጥ) የ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› ፕሮጀክት ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ ነው››
በአቶ ዮናስ አመለካከት የእጓለ ትልቁ አበርክቶት ‹‹በተዋሕዶ ከበረ›› የሚለው ፕሮጀክት ሳይሆን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ታሪከ - ፍልስፍናን (Philosophy of History) ማስተዋወቁ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 5262 times