Sunday, 07 July 2019 00:00

ሕይወቴ እና የፕሬስ እርምጃ

Written by  አንቺ ዓለም ከበደ
Rate this item
(2 votes)

 ‹‹ጋዜጣ ሳይኖር መንግስት ከሚኖርበት ሀገርና ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ከማይኖርበት ሀገር የቱን ትመርጣለህ ቢሉኝ፤ ምርጫዬ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት የማይኖርበት ሀገርን ነው››
               

        አዲስ የፕሬስ ህግ እየወጣ ነው፡፡ ደግሞም ዘንድሮ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀውን ጉባዔ ያስተናገደችው ሐገራችን ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ስለዚህ ስለ ፕሬስ እንጫወት፡፡ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በአፍሪካ አህጉር ሲከበር ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጋና ጉባኤውን አስተናግዳለች፡፡ ሁለተኛውን የማስተናገድ ዕድል ያገኘችው ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን ጉባዔ ከዘጠኝ መቶ በላይ የሚሆኑ፤ ከተለያዩ ሐገራት የመጡ ተሳታፊዎች ታድመው ነበር፡፡ እናም በአፍሪካ ህብረት ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባዔ፤ ተሳታፊዎቹ በተለያዩ ፕሬስ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ የእኔ ጉዳይ ፕሬስ በግለሰብ ህይወት ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው ሊያመለክቱ የሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮችን በማንሳት ጨዋታ መፍጠር እንጂ ጉባዔው አይደለም፡፡ ግን እግረ መንገዴን የሐገራችንን ፕሬስ ወቅታዊ ቁመና አንስቼ አልፋለሁ፡፡  
ፕሬስ አንድ ሃገር ከራስዋ ጋር የምታወራበትና መልኳንና ገጽዋን የምትመለከትበት መስታወት ነው:: የአንድን ሃገር ጤንነት ፣ ሰላማዊነትና እድገት፣ የፕሬሱን ገጽ በመመርመር መረዳት ይቻላል፡፡ ፕሬስ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ህይወት ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ያለው ተቋም ነው፡፡ ዘወትር ሲጠቀስ የምንሰማው የአሜሪካው ፕሬዜዳንት የቶማስ ጃፈርሰን ቃል የፕሬስን ፋይዳ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው:: ጃፈርሰን፤ ‹‹ጋዜጣ ሳይኖር መንግስት ከሚኖርበት ሀገርና ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ከማይኖርበት ሀገር የቱን ትመርጣለህ ቢሉኝ፤ ምርጫዬ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት የማይኖርበት ሀገርን ነው›› ብለው ነበር:: ይህ የቶማስ ጃፈርሰን ቃል የፕሬስን ፋይዳ አጉልቶ ሊያሳየን ይችላል፡፡
ባለፈው ሚያዚያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በመዲናችን አዲስ አበባ በተካሄደው ዓለማቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ጉባኤ መልዕክት ያስተላለፉት የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም፤ ‹‹የሰለጠነና የዘመነ ማህበረሰብ እንዲኖር የሰለጠነ እና የዘመነ ፕሬስ ያስፈልጋል›› ሲሉ ፣መናገራቸው የፕሬስን ፋይዳ የሚያመለክት ነው፡፡  ዶ/ር ዐቢይ፤ ‹‹የመናገር ነፃነት መንግስት፣ ፓርቲ፣ ወይም አንድ ሌላ አካል ለፈለገው የሚሰጠው ላልፈለገው የሚነፍገው እርጥባን አይደለም፡፡ ተፈጥሮ ያጎናፀፈችን መተኪያ የሌለው ታላቁ ስጦታችን፣ ሰው በመሆናችን ብቻ የምናገኘው ፀጋ ቢኖር ያሰብነውን በነጻነት መናገር ነው›› ካሉ በኋላ ‹‹በሀገራችን ዲሞክራሲ እንዲያብብ ብቻ ሳይሆን አሽቶና ጎምርቶ ፍሬውን እንድንበላ ከተፈለገ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከወረቀት ባለፈ በተጨባጭ ሲተገበር ማየት አለብን›› ብለዋል::
የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ ሊከበር የቻለው የፕሬስ ነፃነትን አታከብርም እየተባለች ስትወቀስ የቆየችው ሀገራችን፤በፕሬስ ነፃነት አከባበር ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቷ ነው፡፡ ዛሬ ተዘግተው የነበሩ ጋዜጣና መጽሔቶች እንደገና ወደ ህትመት ገብተዋል፡፡ ከሀገር ውጭ ሆነው የቆዩት ሚዲያዎችም በሀገር ቤት በነጻነት መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ከ260 በላይ ተዘግተው የነበሩ ብሎጎችና ድረገጾች እንደገና ተከፍተዋል፡፡ በእስር ላይ የቆዩ ጋዜጠኞች ከእስር ተለቀዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነትን የሚያውኩ ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ የማድረግ እንቅስቃሴም ተጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ  ‹‹መብት የሌለው ኃላፊነት ባርነት ነው፡፡ ኃላፊነት የሌለው መብትም ልቅነት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ባርነትንም ሆነ ልቅነትን አንፈልጋቸውም›› በማለት መንግስታቸው የፕሬስ ነጻነት መብት በሚገባ እንዲከበር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡›› የማህበራዊ ሚዲያውንም ጉዳይ አልዘነጉትም፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውን የሚገዛ ህግና አሰራር ለመዘርጋት መንግስታቸው ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ለመሆኑ ፕሬስ ምንድነው?
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ እንደ ተመለከተው፤ ‹‹ፕሬስ›› ማለት የህትመት ሥራዎችን የሚያከናውን ማንኛውንም ዓይነት የመገናኛ ብዙሃን ተቋምን እና የመገናኛ ብዙሃን መልዕክት ማስተላለፊያን ሁሉ ይጨምራል፡፡ የህትመት ሥራዎች ሲባል ደግሞ በየጊዜው የሚመጡ ህትመቶችን፣ ለስርጭት ታስበው በማተሚያ ቤት ወይም በሌላ ዓይነት የማባዣ ዘዴ ታትመው የሚወጡ ማናቸውንም ዓይነት ህትመቶችን፣ የኦዲዮ፣ የቪዥዋል ወይም የኦዲዮ- ቪዥዋል ሥራዎችን፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ዝግቶችን፣ ከማብራሪያ ጋር ወይምን ያለማብራሪያ የተፃፉ ወይም የታተሙ የሙዚቃ ሥራዎችን፣ ተውኔቶችን፣ ፊልሞችን፣ ስዕሎችን፣ ካርቱኖችን፣ መጻህፍትንሰ፣ በራሪ ጽሁፎችን፣ ፖስተሮችን እና የንግድ ማስታወቂያዎችን፤ እንዲሁም የዜና አገልግሎቶችና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ማንኛውንም ዓይነት የማስተላለፊያ ቴክኒክ በመጠቀም፣ በቃላት፣ በምስል ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገድ ለፕሬስ የሚልኳቸውን መረጃዎች፣ መግለጫዎች እና ሌሎች ጽሑፎችን ያካትታል፡፡ ይህ ድንጋጌ ኢንተርኔትን እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደሚያጠቃልል እሙን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክ  አጭር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጋዜጣ መታተም የጀመረው በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት በ1893 ዓ.ም ሲሆን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ጋዜጦችም የፍራንሲስካን ሚሲዮን ቄስ በነበሩት በአባ ማሪ በርናርድ በአማርኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ ይታተም የነበረው ‹‹ለሰሜን ደ ኢትዮጲ›› የተባለ ሳምንታዊ ጋዜጣ እና በግሪካዊው ነጋዴ እንድሪያስ ካቫዲ ይታተም የነበረው ‹‹አዕምሮ›› የተሰኘ ሌላ ሳምንታዊ ጋዜጣ ነበር፡፡ ከዛ ወዲህ የመጡት ጋዜጦች ዛሬም እየታተሙ ያለው እና ሁላችንም የምናውቃቸው መንግስታዊ ፕሬሶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ መታተም የጀመረው በሽግግሩ ዘመን ነው፡፡ በሽግግሩ ዘመን የወጣው ቻርተር ሳንሱር መቅረቱን እና የፕሬስ ነፃነት መረጋገጡን የሚያመለክት ድንጋጌ ነበረው፡፡ ሆኖም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በህግ የተረጋገጠው በ1985 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ነው፡፡ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ፕሬስ በጥራትም ባይሆን በቁጥር ከፍተኛ እመርታ አሳይቷል፡፡ ዳግም ማሽቆልቆል የጀመረው ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ዓመታት ነው፡፡  ከአዋጁ በኋላም የአንባቢን ቀልብና ስሜት መግዛትና አድናቆት ማትረፍ የቻሉ የግል ጋዜጦች መታተም ጀምረዋል፡፡
ሆኖም ከኔ ህይወት ጋር ጥብቅ ትስስር ያላቸው ሬዲዮ ቴሌቪዥንና ቴፕን የመሳሰሉ የፕሬስ ውጤቶች እንጂ ጋዜጦች አልነበሩም፡፡ በእርግጥ የልጅነት ዘመኔን ባሳለፍኩበት ሰንጋተራ አካባቢ አንድ የማውቃት ጋዜጣ መሸጫ ኪዮስክ ነበረች:: ያቺ ጋዜጣ መሸጫ ዛሬ በቦታው የለችም፡፡ ሰንጋተራም የለችም፡፡ የዕለታዊውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለመግዛት ረፋዱ ላይ በዚያች ኪዎስክ የሚሰለፉ ሰዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ዘወትር ከሚታየው ከዚህ ሰልፍ ለመዳን የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ወረፋ ይገዛሉ ወይም ከጋዜጣው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ገንዘብ ይከፍሉ ነበር፡፡ በተለይ ከሳምንቱ በየትኛው ዕለት የሚታተመው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሆነ ባላስታውሰውም የትርፍ መሸጫ ዋጋው የሚንርበት ሰልፉም የሚረዝምበት ዕለት መኖሩ ትዝ ይለኛል:: በነዚህ ቀናት እኔም ከሌሎች የሰፈር ልጆች ጋር በመሰለፍ ወረፋ በ5 ወይም በ10 ሳንቲም መሸጤን አረሳውም፡፡  
ሆኖም በሽግግር መንግስቱ ዘመን በርካታ የግል ጋዜጦች መታተም በመጀመራቸው እና ጋዜጦችም እንደ ሎተሪ በአዟሪዎች በየቦታው በመሸጣቸው ያቺ የጋዜጣ መሸጫ ኪዎስክ ከነረጅም ሰልፏ ብዙም ሳትቆይ ጠፍታለች፡፡ እያደር የግል ጋዜጦች ገበያቸው ደራ፡፡ ያወጡት የነበረው ዜናና መጣጥፍ በየኬክ ቤቱ የወሬ ማድመቂያ ሆነ፡፡ በተለይም የጋዜጦቹ የአስትሮሎጂ አምዶች የበርካታ የጋዜጣ አንባቢዎችን ቀልብ የሚይዙ ሆነው በመገኘታቸው፣ አብዛኞቹ የግል ጋዜጦች የአስትሮሎጂ አምዶችን በጋዜጦቻቸው ያካትቱ ነበር፡፡
በበኩሌ በወቅቱ የግል ጋዜጦችን አንባቢ አልነበርኩም፡፡ ስለዚህ  የሰብዕና መሰረት ተደርጎ በሚወሰደው የእድሜ ዘመኔ ከፕሬስ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ከጋዜጣ ጋር የተሳሰረ አልነበረም፤ ከሬዲዮ ከቴሌቪዥን እና ከሙዚቃ ጋር እንጂ፡፡ በመሆኑም ጋዜጣ በግል ህይወቴ ላይ አሳደረብኝ የምለው ተጽዕኖ የለም፡፡
የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጉዳይ ሳስታውስ የልጅነት ዘመኔን ያሳለፍኩባት ሰንጋተራም ተጎትታ ትመጣለች:: አሳዛኙ ነገር፤ ግን ያቺ የትዝታ ማህደሬ የሆነችው ሰንጋተራ ዛሬ የለችም፡፡ ሰንጋተራ መሐል በነበረው እና ዛሬ የትዝታዬ ማህደር አድርጌ በምቆጥረው ከጥቂት ዓመታት በፊት መኖሪያችን በነበረው ግቢ አራት ቤተሰብ ይኖር ነበር ፡፡
በወቅቱ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ እንደ ዛሬው በቀላሉ የሚታይ ንብረት አልነበረም፡፡ በኛ ግቢ ቴሌቪዥን የነበራቸው ከግቢው በር አጠገብ በነበረው ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጎረቤቶቻችን ናቸው፡፡ እኛ ቤት ደግሞ ከአባቴ እጅ የማትጠፋ ትንሽ ሬዲዮ ነበረች፡፡ ታዲያ የኛ ሬዲዮ፣ የጎረቤቶቻችን ቴፕና ቴሌቪዥን በእኔ ህይወት ያሳደሩት ትዝታ ትልቅ መሆኑን የተገነዘብኩት አሁን ነው፡፡
የእኛ ሬዲዮ አራት ትናንሽ ባትሪ ድንጋይ ትወስዳለች፡፡ መጠኗም ከአባቴ እጅ ትንሽ ከፍ ብትል ነው፡፡ የቪ.ኦ.ኤ እና የዶቼቬሊን ስርጭት በልዩ ትኩረት እንደሚከታተል አስታውሳለሁ፡፡ የቪ.ኦ.ኤ እና የዶቼቬሊ ሰዓት ሲደርስ፤ ሬዲዮኗን በእጁ ይዞ ወደ ጆሮው ያስጠጋታል፡፡ አባቴ በማይኖርበት ጊዜ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ዝግጅቶችን ለመከታተል፤ ወደጎረቤት እንሄዳለን፡፡ ነገር ግን በዚህ ዕድል ለመጠቀም የምንችለው፤ በትጋት እና በታታሪነት ለጎረቤቶቻችን በመታዘዝ ብቻ ነው፡፡
የልጆች ክፍለ ጊዜ፣ ህብረ - ትርኢት እና ታላቅ ፊልም የመሳሰሉ ዝጅቶች በሚታዩባቸው ዕለታት የጎረቤቶቻችንን ትዕዛዝ ያለ አንዳች ማጉረምረም ለማከናወን ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡ በእንዲህ ያሉ ቀናት ሲታዘዙ መነጫነጭ የለም፡፡ እንዲያውም ለጎረቤቶቻችን ለመላክ እና ለመታዘዝ ከቤታቸው በር ፊት ለፊት ስናንዣብብ እንውላለን፡፡
እንደማስታውሰው በሠፈራችን በእኛ ግቢ ከሚገኘው አንድ ቤተሰብ ሌላ በመንደሩ ቴሌቪዥን ያለው ሰው አልነበረም፡፡ በዚህ የተነሳ ቴሌቭዥኑ የእኛ ባይሆንም፤ የቴሌቭዥን ዝግጅቶችን ለማየት በሚፈልጉ የሠፈራችን ልጆች ባለስልጣን የመሆን ዕድል ነበረን፡፡ እነዚያ የሠፈራችን ልጆች ቴሌቭዥን ለማየት ልክ እንደኛ ለግቢያችን ባለቴሌቪዥኖች መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ከኛ የሚለያቸው አሳዛኙ ነገር፤ እነሱ ቀኑን ሙሉ ያለማንገራገር ታዘው እና ተልከው፤ በመጨረሻ ሰዐት ይቋምጡለት የነበረውን የቴሌቪዥን ዝግጅት ላያዩ ይችላሉ:: ወይ ቤተሰቦቻቸው በምሽት ከቤት እንዳይወጡ ከልክለዋቸው፤ አለያም ባለቴሌቪዥኖቹ ‹‹ልጆች መሽቷል ወደ ቤታችሁ ሂዱ›› ብለው ስለሚያባርሯቸው፤ ድካማቸው ከንቱ ሊሆን ይችላል፡፡
የአባቴ ሬዲዮ የባትሪ ድንጋዩ ኃይል ካልደከመ ምንም የሚያመልጠን የሬዲዮ ፕሮግራም አልነበረም፡፡ ከሬዲዮ ፕሮግራሞች በተለይ አሁን ድረስ ከውስጤ የማይጠፉ ትዝታዎችን ጥለውብኝ ያለፉት እና በጣም የምወዳቸው ፕሮግራሞች ነበሩ:: አንዱ የቅዳሜ ጠዋቱ የልጆች ክፍለ ጊዜ  ነበር፡፡
ደማቅ የልጅነት ትዝታዬ ሆኖ የቀረው የአለም ፀሐይ ወዳጆ ‹‹ፀሐዬ ደመቀች›› የሚለው መዝሙር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ከልጅነት እስከ ወጣትነት፤ ከፆታ እስከ ሀገር ፍቅር በሚዘረጋ የትዝታ መዝገቤ ላይ ሁሉ መህተሟን ያሳረፈች ድንቅ ደራሲ ነች፡፡
ከ‹‹ጸሀዬ ደመቀች›› ሌላ በሬዲዮ ተደጋግሞ የሚቀርብ፤ ቋንቋውንም ሆነ ትርጉሙን ባላውቀውም አብሬ የምዘምረው አንድ መዝሙር ነበር -- ‹‹ሾሾሾ ዶዲ›› የሚል፡፡ ከህጻናት መዝሙሮች በተጨማሪ በሬዲዮ ይቀርቡ ለነበሩ ዝግጅቶች ማጀቢያ እየሆኑ፤ መሀል መሀል ይደመጡ የነበሩ ዘፈኖች ለልጅነት እና ለወጣትነት ዕድሜዬ ደማቅ ጥለቶች ሆነው በህሊናዬ ታትመው ቀርተዋል፡፡
እንደኔ የልጅነት ዘመኑን ከሬዲዮ ጋር አስተሳስሮ የሚመለከት ማናቸውም የኔ ዘመነኛ የሆነ ታዳጊ ወጣት፤ ከከልጆች ዓለም ዝግጅት በተጨማሪ ዘወትር እሁድ ማታ የሚቀርበውን የ‹‹ከመጻህፍት ዓለም›› ትረካ፣ የቅዳሜ ከሰአት የወጣቶች ፕሮግራም፣ በእሁድ ጠዋት ይቀርቡ የነበሩት የነዳንዲዮ ሰርቬሎ፣ የአነዘነበ ወላ ሀይሌ ዘበቅሎቤት የመሳሰሉትን ፀሀፊዎች እና የነፊርማዬ አለሙን ግጥም የነይሉ ፀጋዬን ድራማ የነአብርሀም ወልዴ ጭውውትን ማስታወሱ አይቀርም፡፡
እነዚህ የሬዲዮ ዝግጅቶች ዛሬም በህሊናዬ ብቅ የሚሉ የትዝታዎቼ ጌጦች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ስለቴሌቪዥን ሳስብ፤ በሣጥን ውስጥ በሚቀመጠው ባለነጭ እና ጥቁር ቀለም የጎረቤታችን ቴሌቪዥን ብቅ እያሉ የሚታዩኝ፤ በተረት የሚያጫውቱን እና ‹‹አንተ ከመሐል ያለኸው ….. ›› እያሉ ሲናገሩ በእውነት የሚያዩን ያስመስሉ የነበሩት አባባ ተስፋዬ ናቸው፡፡ እንዲሁም በሣምንት ሁለት ቀናት በሚተላለፈው የህብረ - ትርዒት ዝግጅት የሚቀርቡት እና ብዙ ጊዜ ከማዘጋጃ ቤት ህንጻ አናት ቆመው የሚቀረፁት በርካታ ዘፋኞች በዓይነ ህሊናዬ ሽው ይላሉ፡፡  በብሔረ ጽጌ መናፈሻም የተቀረፁ በርካታ የሙዚቃ ክሊፖች ነበሩ፡፡ የሙዚቃ ክሊፕ ሲነሳ በቶሎ ወደ ህሊናችን የሚመጡት፤ በስቱዲዮ የሚቀርቡ ዘፋኞችን በማጀብ የሚቀርቡት ዳንሰኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ተወዛወዦች በተለመደ አኳኋን ተደርድረው እና በአንድ ዓይነት ልብስ ሲጫወቱ በሁለመናቸው የዘመን አሻራን ያንፀባርቃሉ፡፡  
በቴሌቭዥን ይቀርቡ ከነበሩ የዘፈን ክሊፖች ሁሉ ለየት ተደርገው ሊታዩ የሚችሉ የተወሰኑ ድንቅ ሥራዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ በቅድሚያ ሊጠቀሱ የሚገባቸው የጥላሁን ‹‹ፈልጌ አስፈልጌ›› እና የመልካሙ ተበጀ ‹‹የደህና ሁኚ ፍቅሬ›› ክሊፖች ናቸው፡፡ በተለይ የጥላሁን ዘፈን ሰንጋተራን የሚጠቅስ በመሆኑ ልዩ ስሜት ይፈጥርብኝ ነበር:: ጥላሁን ቢኤም ደብሊዩ እየነዳ፤ ደግሞ ከመኪና ወርዶ በእግሩ እየኳተነ፤ ፍቅሩን ሲያፈላልግ፤ አሳምሬ በማውቀው የሠንጋ ተራ እና የብሔራዊ ቴአትር ጎዳናቸው በጥድፊያ ሲራመድ ሳየው አብዝቶ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እንዲሁም መልካሙ ተበጀም ‹‹ደህና ሁኚ ፍቅሬ›› ለሚለው ዘፈኑ ማጀቢያ አድርጎ የሰራው ክሊፕ የተለየ ስሜት የሚፈጥር ውብ ሥራ ነው፡፡ መልካሙ ከሠገነቱ ቆሞ በአውሮፕላን የምትሄድ ፍቅረኛውን ሲሸኝ፤ እርሷም አውሮፕላን ውስጥ ገብታ እጇን እያወዛወዘች ስትሰናበተው የምንመለከተው ትዕይንት ፍፁም ስሜትን የሚገዛ፤ በዘመኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለውድድር ቢሰለፉ ከምርጥ ክሊፖች ሊመደቡ እንደሚችሉ እገምታለሁ::
ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ የዘፈን ካሴቶች ወይም ሲዲዎች ድራማዎች፣ ፊልሞች ወዘተ ሁሉ የፕሬስ ውጤቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከአለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ጋር አያይዤ የማነሳቸው፡፡ ታዲያ በግቢያችን ካለው ቴሌቪዥን ቀጥሎ መጀመሪያ ቴፕ የገዙት ከኛ ቤት አጠገብ ያሉት ጎረቤታችን ናቸው፡፡ ቴፑ በኤሌክትሪክ የሚሰራ እና ካሴት የሚያጫውት ስለ ነበር ቀኑን ሙሉ ይከፈታል፡፡ ስለዚህ ከአባቴ ሬዲዮ እና ከጎረቤታችን ቴሌቪዥን በበለጠ ብዙ ጊዜ በቴፕ የሚጫወቱ ሙዚቃዎችን መስማት ጀመርን:: ጎረቤታችን ይሄን ቴፕ ሲከፍቱ፤ ድምፁ ለሙሉ ግቢው ሊሰማ በሚችልበት መጠን ከፍ አድርገው ነው፡፡ ቴፑም ያለ ዕረፍት ይጫወታል፡፡
ዛሬ እንደማስታውሰው ዘወትር ማለዳ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳችን በፊት የጠዋቱን ዜና እና ከዜናው ቀጥሎ ለሚቀርበው የኢኮኖሚያችን ዝግጅት ማጀቢያ ሆኖ ይቀርብ የነበረው ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ›› የሚለው ዘፈን የማይቀር የጆሮ ቁርስ ነበር፡፡ እንደዛ ተመናትፈን ሬዲዮና ቴሌቪዥን አይተን በወቅቱ የሚሰሙትን ዜናዎች የመንግስት መግለጫዎች እና ዘፈኖች በደንብ እናውቃቸው ነበር፡፡ እንዲያውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀውን ኢንፎርሜሽን ሁሉ በእኩል የእውቀት ደረጃ የምናውቅ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው፤ ይህ እውነት የሚሆነው ሬዲዮ በደረሰበት ቦታ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ዛሬ ለቁጥር የሚያደናግሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና የኤፍ ኤም ስርጭቶች እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እና በርካታ ጋዜጦች እና መፅሔቶች ባሉበት ሁኔታ፤ ብዙ ሰዎች ለነገሮች እኩል መረጃ እንደ ሌላቸው ስረዳ ግራ ይጋባኛል፡፡ እናም የሚዲያው እንዲህ መብዛት ጥቅሙ እምን ላይ ነው? ያሰኘኛል፡፡ ሰምቼው የማላውቀው ዜማ፤ አይቼው የማላውቀው ዘፋኝ ይገጥመኛል፡፡ ከሣምንት በኋላ ‹‹እንዲህ ተብሏል እንዴ?›› ብዬ የማጣራው ዜና መኖሩን ሳይ - እውነትም መብዛቱ ጥቅሙ ምንድን ነው ያሰኘኛል፡፡
በርግጥ በሌሎች አገራት ከሚታየው የፕሬስ ተቋማት ቁጥር ጋር በማነፃፀር  የሐገራችን ፕሬሶች ከዚህም በላይ በቁጥር እየተበራከቱ ሊሄዱ ይገባል፤ የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ የመገናኛ ብዙሀን መበራከት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሚችሉበትን እና ሀሳቦች መድረክ በማጣት የሚቀሩበትን ሁኔታ ያስቀር ይሆናል፡፡ የሀሳብ ብዝሀነት ሊፈጠር የሚችለው በፕሬሶች መበራከት ነው፡፡ እንደሚባለውም  የመገናኛ ብዙሀን ቁጥር መብዛት የይዘት ብዝሀነትን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡  ሆኖም ቁጥር ብቻ ዋስትና አይሆንም፡፡ በቁጥር የበረከቱት የሀገራችን ሚዲያዎች የይዘት እና አቀራረብ መደጋገም የሚታይባቸው ከሆኑ ቁጥርን ትርጉም የለሽ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ቁም ነገሩ በ100 ወይም በሺህ የሚቆጠሩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መኖራቸው አይደለም፡፡  ቁም ነገሩ የሚዲያ ምህዳሩን በጥንቃቄ በማጥናት የጎደለውን ለመሙላት እና ታማኝ አድማጭ እና ተመልካች ለማፍራት የሚያስችል አሰራር የሚከተሉ ሚዲያዎች መኖራቸው ነው፡፡ ሚዲያዎቻችን የይዘት ብዝሀነት የማይታይባቸው በተመሳሳይ አጀንዳ እና አቀራረብ የሚገለጡ ከሆነ ቁጥር ፋይዳ አይኖረውም:: እንደ ፋብሪካ ምርት ተመሳሳይ ከሆኑ 100 የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይልቅ  በጠንካራ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚመራ፣ ተቋማዊ ነፃነት ያለው እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን ተከትሎ የሚሰራ አንድ ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን የተሻለ የይዘት ብዝሀነትን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡
ታዲያ የሚዲያዎች ቁጥር እንዲህ እየተበራከተ ቢመጣም በኔ ህይወት እንደተመለከታችሁት የዚህ ዘመን ታዳጊዎች እና ወጣቶች በኔ ዘመን እንደነበሩት ልጆች ህይወታቸው ከሚዲያ ጋር የተሳሰረ ሆኖ አይታየኝም፡፡ ይህን ፁሁፍ ከማጠናቀቄ በፊት ላነሳው የምፈልገው አንድ ጉዳይ አለ፡
አሁን የምናየው የሀገራችን የሚዲያ ምህዳር አዲስ መልክ እየያዘ ነው፡፡ ይህ አዲስ መልክ በቁጥር፣ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፡፡  በሀገራችን ካለው የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚዲያ ምህዳሩ አዲስ መልክ መያዝ ጀምሯል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ሰው ቁጥር ተበራክቷል፡፡ ዛሬ በርካታ ዜጎች እንደቀድሞው ፖለቲካዊና ማህበራዊ አስተያየታቸውን የሚሰሩት ሜንስትሪም ወይም ኮንቬንሽናል እየተባሉ ከሚጠሩት  የመገናኛ ብዙሀን  በሚያገኙት መረጃ ላይ ተመስርቶ አይደለም፡፡ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተጽዕኖ በኛም ሆነ በበለፀጉት ሀገራት ጎልቶ የሚታይ አሳሳቢ አጀንዳ ሆኖ ወጥቷል::
አንዳንድ ምሁራን ‹‹ሲቲዝን ጆርናሊዝም›› የሚሉት ክስተት ተስፋፍቷል፡፡ በመሆኑም መረጃዎች ለህዝብ የሚቀርቡት በተለመደው የሥነ ምግባር ዳር ድንበር ባለው የጋዜጠኝነት አሰራር ሂደት አልፈው አይደለም፡፡  ሞባይል ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆነና የጋዜጠኝነት ሙያ ምን እንደሆነ የማያውቅ ማንኛውም ሰው በመረጃ ስርጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆኗል፡፡
የሐገራችን የሚዲያ ምህዳር እንዲህ ዓይነት አዲስ መልክ መያዝ ጀምሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚዲያ ተቋማት ከክልል፣  ከፖለቲካ ቡድኖች እና ከአክቲቪዝም ጋር እየተሳሰሩ ትልቅ ቀውስ የሚያስከትል አሰራር እና ባህሪ ይዘው ይታያል:: ከሁሉ በላይ አሳሳቢ ሆኖ የሚታየኝ የክልል መንግስታት ሚዲያዎች የቀውሱ አንድ አካል ሆነው መመልከቴ ነው፡፡
እናም አስተውለን ካልተራመድን ዘላቂ ሰላም እና ዲሞክራሲያዊ ሀገር የመፍጠር ህልማችን ሊሰናከል ይችላል፡፡ አሁን በእጅጉ ገንግኖ ስር ሰዶ እና ጎልቶ የሚታየው የዘረኝነት እና የጽንፈኝነት መንፈስ የሚዲያ ምህዳሩን እንዳውሎንፋስ እያመሰው የው፡፡ የሀገራችን የመገናኛ ብዙሀን አሰራር እና አደረጃጀት ከ2 አስርት አመታት በፊት በዩጎዝላቪያ የታየውን ሁኔታ የሚያስታውስ ነው:: ዩጎዝላቪያ ብሄርን መሰረት በማድረግ የተከለሉ  ስድስት ክልሎች የተከፋፈለች ነበረች፡፡ በየክልሉ የሚገኙት የዩጎዝላቪያ ሚዲያዎች እንዲህ እንደኛ ሀገር በብሄሮች መካከል ጥርጣሬ የሚያሰፍን እና ስሜታዊነትን የሚያነግሱ ዘገባዎችን ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህም ውሎ አድሮ ሀገሪቱን ለደም አፋሳሽ ጦርነት እና ለብተና ዳርጓታል፡፡  የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ስናከብር እንዲህ ዓይንት ፈታኝ ሁኔታዎችን በጥሞና መመርመር እና አካሄዳችንን በጊዜ ማስተካከል እንዳለብን በማሰብ ሊሆን ይገባል::


Read 823 times