Saturday, 06 July 2019 13:55

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጉዳይ በድርድር እንዲፈታ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

“አጀቶ” ሐምሌ 11 ክልል መሆኑን እንደሚያውጅ አስታውቋል መንግስት ከህግ ውጭ የሚደረግን እንቅስቃሴ እንደማይታገስ አስጠንቅቋል


           የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን የፌደራል መንግስት በድርድር እንዲፈታው የግጭቶች ቅድመ ምርመራ ላይ ትኩረት አድርጐ የሚሠራው “ክራይስስ ግሩፕ” ጠየቀ፡፡
“ጉዳዩ በእጅጉ አስጊ ነው” ያለው አለማቀፋ የግጭቶች ጥናት ቡድን፤ የፌደራል መንግስት ከጥያቄ አቅራቢ የማህበረሰቡ አባላት ጋር በድርድር ህዝበ ውሣኔ የሚካሄድበትን አግባብ ሊያበጅ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ህዝበ ውሣኔ ሊካሄድ የሚችልበትን ቀን መንግስት ከህዝቡ ተወካዮች ጋር ሆኖ ከወዲሁ መወሰን እንዳለበት የጠቆመው ክራይሲስ ግሩፕ፤ ጉዳዩ በጥንቃቄ ካልተያዘ ደቡብ ክልል በአጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡
የሲዳማ የክልልነትን ጥያቄ የማያነሱ ወገኖችም በተለይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው ሃዋሣ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች እልባት እስኪያገኙ፣ በተናጠል የክልልነት አዋጅ ከማስነገር እንዲቆጠቡ ተቋሙ መክሯል፡፡
በቂ ህገመንግስታዊ ዝግጅት ሳይደረግ የሲዳማ ክልል መሆን ከታወጀ ክልሉን ወደ አለመረጋጋትና ቀውስ እንደሚያመራው ሰፊ ማሳያዎችን በማቅረብ በሪፖርቱ የተነተነው ተቋሙ ለዚህ መፍትሔው ከወዲሁ መንግስትና ጥያቄውን የሚያነሱ ወገኖች ቁጭ ብለው መደራደር ነው ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል 10 ብሔረሰቦች ክልል መሆን ፍላጐት እንዳላቸው በጥናት መረዳቱን የገለፀው ክራይሲስ ግሩፕ፤ ለሁሉም መነሳሳት የፈጠረው የሲዳማ ጥያቄ ነው ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዳውሮ፣ ጋሞ፣ ጐፋ፣ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ከፍቾ፣ ከምባታ፣ ወላይታ እና ሌሎች ብሔረሰቦች ክልል የመሆን ፍላጐት አላቸው ብሏል - ተቋሙ በሪፖርቱ፡፡
የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ የሚያቀነቅነው ኢጄቶ የተሰኘው አደረጃጀት ከትናንት በስቲያ ሃዋሣ ላይ ባደረገው ስብሰባ፤ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ክልል መሆኑን ለማወጅ መዘጋጀቱንና የቀድሞ አቋሙን አለመለወጡን አስታውቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ “ክልል ልሁን ብሎ ጥያቄ ማቅረብ ህገመንግስታዊ መብት ነው፤ ምላሹም ህገመንግስታዊ መሆን ስላለበት ጥያቄ አቅራቢዎች ህገመንግስታዊ ምላሽ እስኪሰጥ በትዕግስት መጠበቅ አለባቸው” ብለዋል:: አያይዘውም፤ መንግስታቸው ከህግ ውጭ የሚደረግን እንቅስቃሴ ሁሉ እንደማይታገስም አስጠንቅቀዋል፡፡


Read 10387 times