Saturday, 06 July 2019 14:00

ትጥቅ የማስፈታው ህገወጦችን ነው- የአማራ ክልል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(12 votes)

 - በሰሞኑ ግድያ የተጠረጠሩ መያዛቸው ቀጥሏል
       - “አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ተመክረው ይለቀቃሉ”
                
            በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሰኔ 15ቱ የአመራሮች ግድያና መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የማጣራት ሂደቱ እንደቀጠለ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደገለፁት፤ በክልሉ ከተከሰተው ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከሚውሉት ሰዎች መካከል በምክር የሚለቀቁ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለዚህም የመምከሪያ ሥፍራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ከሰሞኑ ክስተት ጋር በተያያዘ ሳያውቁ በስህተት በጉዳዩ የገቡትን የህብረተሰብ ክፍሎች የመምከርና የማስተማር ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በድንገትና በግብታዊነት ባለማወቅ የገቡ ወገኖች ከስህተታቸው እንዲማሩና እንዲመለሱ እየተደረገም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በክልሉ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ እየተካሄደ ነው ስለመባሉ የጠየቅናቸው አቶ መላኩ፤ ይህ መሰረተቢስ ወሬ ነው፤ በክልሉ ምንም አይነት ትጥቅ የማስፈታት ሥራ እየተከናወነ አይደለም ብለዋል፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ የግሉን የጦር መሳሪያ በህጋዊ መንገድ አስመዝግቦና ፈቃድ አውጥቶ እንዲጠቀም ከማድረግ ውጪ ትጥቅ እንዲፈታ የተደረገበት ሁኔታ የለም ሲሉም ተናግረዋል:: አያይዘውም፤ መንግስት ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውርን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው፤ በህጋዊ መንገድ የታጠቁትም ቢሆኑ በወንጀል ተግባር ላይ ሲሰማሩ ከተገኙ እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡
በክልሉ ከ2011 አጋማሽ ጀምሮ የግል የጦር መሳሪያ ያላቸው ሰዎች የጦር መሳሪያዎቻቸውን በህጋዊ መንገድ አስመዝግበውና ፈቃድ አውጥተው መያዝ እንደሚችሉ የወጣውን መመሪያ ተከትሎ፣ በርካታ ሰዎች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ አሁንም በህገወጥ መንገድ ከአጐራባች አገራት ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎች መኖራቸው ተመልክቷል፡፡
እነዚህን ህገወጥ መሳሪያዎች ለመያዝና ዝውውሩን ለማስቀረት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተረጋጋ ሰላምና ፀጥታ መኖሩን የጠቆሙት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው፤ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ፀጥታና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡



Read 9142 times