Print this page
Saturday, 06 July 2019 14:06

ለሰላማችን ሲባል - ፌስቡክ ለጥቂት ጊዜ ይዘጋልን!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)


          ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሪፖርት በጽሞና አዳመጥኩት:: የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትንም መልስና ማብራሪያ በአንክሮ ተከታተልኩት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትራችን የአሁኑ አቀራረብ እኔን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎችን ያስደሰተ እንደነበር ባለኝ ግንኙነት ካገኘኋቸው ግብረ መልሶች ለመረዳት ችያለሁ፡፡
በአንድ በኩል፤ የሀገሪቱ ችግር ውስብስብና ጭንቅላት የሚያዞር ነው፡፡ ለዘመናት የተደረተን የችግር ድሪቶ በአጭር ጊዜ ፈትቶ እፎይታን በመፍጠር መቶ ሚሊዮን ህዝብ ማስደሰት በተዓምር ካልሆነ በስተቀር በተግባር የማይቻል ነገር ነው:: ሀገሪቱ ድሃ፣ ብዙሃኑ ህዝቧ ማውራት እንጂ መስራት የማይወድ፣ በአቋራጭ መክበርን እንጂ በሂደት ማደግን የማይፈልግ ጠባቂ መሆኑ ደግሞ የታታሪና ቅን መንግስትን ጥረት የሚፈታተን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፤ ኢህአዴግ ያቀፋቸው የ“ብሔር” ፓርቲዎች እና አጋር ድርጅቶች፣ ላለፉት 26 ዓመታት ባደረጉት ጉዞ፣ ሀገሪቱን ከረሃብ አዙሪት አውጥተው ወደተሻለ እድገት ሊመሩ ቀርቶ ራሳቸው አርቅቀው “በህዝብ ይሁንታ እንዲጸድቅ አደረግን” ያሉትን ህገ መንግስት ሊያከብሩት ባለመቻላቸው፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተደፍቀዋል:: እኩል ተጠቃሚነት እውን ሊሆን አልቻለም:: በዚህም ምክንያት ዶ/ር ዐቢይና መንግስታቸው በርካታ ውዝፍ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ውዝፍ ሥራዎቹ ሳይሰሩ መወዘፋቸው ብቻ ሳይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለመስራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍና ያንን መሸከም የሚችል ተቋም አለመኖሩ፤ ቢኖርም ሊያሰራ የሚችል አደረጃጀት የሌለው መሆኑ ዋነኛ ችግር መሆኑም ይታየኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፤ ባለፉት 26 ዓመታት የነበረው የኢህአዴግ አስተዳደር በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን የአንድነትና የወንድማማችነት ስሜት እንዲሸረሸርና በምትኩ አለመተማመን፣ ጥርጣሬ፣ ጭንቀት፣ ፍርሃት፣ ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ውጥረት… እንዲነግስ ማድረጉ የተረጋጋና ጠንካራ የሥራ መንፈስ ያለው ማህበረሰብ እንዳይኖር አድርጎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የተዛባ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት መዘርጋቱና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር መደረጉ ደግሞ በዜጎች መካከል ተገቢ ያልሆነ ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል::
እንዲህ ያለ ያጋደለ ሚዛንን የማስተካከል ሥራ ነው ዶ/ር ዐቢይን ዓይኑን አፍጥጦ የሚጠብቃቸው:: እንዲህ ያለ የተዛባ ሁኔታ ደግሞ ቅንነትና ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ጉልበት ይጠይቃል፡፡ ሀብትና ገንዘብ ግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ ሰላምና መረጋጋትን ይፈልጋል፡፡ ሰላምን፣ መረጋጋትን፣ የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን ደግሞ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት በአግባቡ አልተወጣም፡፡
እንደኔ እንደኔ በዚህ ወቅት ለሰላማችን መደፍረስ ቤንዚን ሆኖ እያቀጣጠለው ያለው ማህበራዊ ሚዲያ በተለይም “ፌስቡክ” መሆኑን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያው በተለይም ፌስቡክ በመዘጋቱ ያገኘነው እፎይታ ከእስር ቤት የመፈታትን ያህል ደስታ የፈጠረ እንደ ነበር በርካቶች ተናግረዋል፡፡ የእኔን ገጠመኝ ልንገራችሁ፡፡
በእኔ ቤት ውስጥ ማታ ማታ ሁሉም ሰው የተናጠል ቁዘማ ውስጥ ሆኖ ነው የሚያሳልፈው፡፡ እኔ፣ ባለቤቴ፣ ልጆቼና እህቶቼ ስልክና ኮምፒዩተር ላይ ተቸክለን፣ በየራሳችን ዓለም መቅዘፍን ልምድ ካደረግነው ሰነባብተናል፤ ኧረ እንዲያውም ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ተቀምጠን፣ ዓይናችን ፈጦ አንተያይም፡፡ ሁላችንም ለየራሳችን እናወራለን፡፡ አንዳንዴ ፈገግ ሌላ ጊዜ ሳቅ እንላለን፡፡ ብቻውን ጮክ ብሎ የሚስቅም አለ:: ግን አንሰማውም ወይም በምን ጉዳይ እንደሚስቅ አናውቅም አሊያም አንጠይቀውምም፡፡
በእኔ ቤት ውስጥ ቤተሰቤ በጋራ እራት መብላት ካቆመ ቆይቷል፡፡ ተሰባስበን እራት ከበላን እንደ ብርቅ ነው የምናወራው፡፡ ሰሞኑን ሶሻል ሜዲያ በመዘጋቱ ቤተሰቤ በተከታታይ በጋራ እራት ይበላ ጀመር፡፡ ከልጆቼና ባለቤቴ ጋር መጨዋወት፣ በጋራ ፊልም ማየት፣ ተረት ማውራት፣ መጽሐፍት ማንበብ፣… ጀምረናል፡፡
በአጠቃላይ፤ ሰሞኑን ፌስቡክ በመዘጋቱ የተገኘውን እፎይታ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ፌስቡክ በመዘጋቱ በአንድ ቤት እየኖሩ “ተለያይተው የነበሩ” ቤተሰቦች ተገናኝተዋል፡፡ አዲስ ህይወት የጀመርን ያህል ተሰምቶናል፡፡ ብዙዎቻችሁ እንዲህ ያለ ስሜት እንደተፈጠረባችሁ አስባለሁ፡፡ በበኩሌ የፌስቡክ ባሪያ መሆናችንን ጥሩ አድርጌ የተገነዘብኩት ገና አሁን ነው፡፡
የዛሬዋን አጭር ፌስቡክ ተኮር መልእክቴን ከመቋጨቴ በፊት አንድ ከብዙዎች ጋር የማያስማማኝን ሃሳብ በማጠቃለያነት ላቅርብ:: በእኛ ማህበረሰብ አሉባልታ ዋነኛ እሴታችን ነው:: የአሉባልታችን መፍለቂያ ምንጩ ቡና ነው:: በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ (ጧት እና ቀን) የቡና ስርዓት አለን፡፡ ጎረቤቶቻችንን እንጠራለን፡፡ የቡና ቁርሱ ይቀርባል፡፡ ቡናው ተፈልቶ ይቀዳል፡፡ እሱን እየጠጣን ወሬያችንን እንጠርቃለን፡፡ ሀሜቱንም አሉባልታውምን ጨማምረን መረጃ እንለዋወጣለን፡፡
ዛሬ ዛሬ (በዘመነ ፌስቡክ) ለቡና መጠራራት የለ፣ የቡና ቁርስ የለ፣ ቡና የለ… ሁሉም ነገር በፌስቡክ ሆኗል፡፡ ለቅሶ የምንደርሰውም፣ የምናስተዛዝነውም፣ የወለደች የምንጠይቀውም፣… ደስታና ኀዘናችንን የምንገልጸውም በፌስቡክ ሆኗል፡፡ አሉባልታውንና ሀሜቱን የምናራግበው፣ ቁም ነገሩንም የምንዘግበው በዚያው በፌስቡክ አድርገነዋል፡፡
ፌስቡክን ለበጎ ነገር መጠቀም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ያልሰለጠነ ማህበረሰብ፣ ወደቀ ሲሉት ተሰበረ ብሎ የሚያወራ ማህበረሰብ እንደ ፌስቡክ ያለ ቴክኖሎጂን በኃላፊነት መንፈስ ይጠቀማል ማለት ዘበት ነው፡፡ እናም ዶ/ር ዐቢይ ከልባቸው ሀገራቸውን የሚወዱ ከሆነ፣ ካንጀታቸው ህዝባቸውን የሚያፈቅሩ ከሆነ፣ ህዝባቸው ሰላምና እፎይታ አግኝቶ ወደ ሥራ እንዲሰማራ የሚፈልጉ ከሆነ፣ ፌስቡክን ለተወሰነ ጊዜ ያዘጉልን፡፡ እኛም ልዩነቱን እንየው፡፡ በአንድ ጣሪያ ስር እየኖረ የተበተነ ቤተሰባችን ይሰብሰብ፡፡ ሁለት መስመር ኮሜንት በመጻፍ ወይም በማንበብ ሊቀ ሊቃውንት የሆነ ያህል የሚሰማው ሰው ሁሉ ወደ መጽሐፍ ማንበብ ይሸጋገር፡፡ የእውቀት ገበታ መጽሐፍ እንጂ ፌስቡክ አለመሆኑንም ያስተውለው፡፡
ለመረጃ ልውውጥ ከሆነ ሌሎች የበይነ-መረብ (የኢንተርኔት) አገልግሎቶች (ለምሣሌ ኢሜይል) ክፍት እንዲሆኑ ቢደረግ በቂ ነው፡፡ ለሚሰሩት ሥራና ለሚያሰራጩት መረጃ ኃላፊነትን መውሰድ የሚችሉ ድረ-ገፆች ተቋቁመው፣ ባለሙያዎችን ቀጥረው ቢሰሩ ደግሞ ጥርት ኩልል ያለ መረጃ በማግኘት ሁላችንም ተጠቃሚ እንደምንሆን አምናለሁ፡፡ እናም እንደዚያ ዓይነት ተቋማት እንዲፈጠሩ ወይም ያሉት እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2380 times