Saturday, 06 July 2019 14:12

“የጥበብ ዋልታዎች” ነገ በሀገር ፍቅር አዳራሽ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 በአንጋፋው ጋዜጠኛ ይጥና ደምሴ የተዘጋጀውና በዕንቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቻችን ግለታሪክና የስራ ተሞክሮ ላይ የሚያጠነጥነው “የጥበብ ዋልታዎች” የተሰኘው መፅሐፍ ነገ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በሀገር ፍቅር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
መጽሐፉ፤ የሀገራችን ታላላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህይወትና የስራ ተሞክሮ ለተተኪ የጥበብ ባለሙያዎች መማሪያ እንዲሆን ታልሞ መዘጋጀቱን ጋዜጠኛ ይጥና ደምሴ ጠቁሟል፡፡
በነገው ዕለት መጽሐፉ ሲመረቅ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለታዳሚው የሚቀርቡ ሲሆን ታሪካቸው በመፅሐፉ የተካተቱም ሆኑ ያልተካተቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የህይወት ተሞክሯቸውን  እንደሚያጋሩ ታውቋል፡፡ መድረኩ በአንጋፋው ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ እንደሚመራም ተጠቁሟል፡፡  መፅሐፉ በ254 ገጾች ተቀንብቦ፣ በ101 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ የቀረበ ሲሆን ደራሲው ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ይዘት ያለው “የዘመን አሻራ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

Read 7535 times