Saturday, 06 July 2019 14:24

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

“በራስህ ላይ ስትነቃ በውስጥህ የተቀበረችው እውነት ቦግ ትላለች”
                              

             ውሸት ባህል የሆነበት አገር ነበር፡፡ አንድ ቀን ‹ንጉሡ ሞተ› ተባለ፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በቤተ መንግስቱ አደባባይ ተገጠገጠ፡፡ ንጉሡ በመገረም ሰገነቱ ላይ ወጥቶ፡-
“ምን ሆናችሁ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡
“የንጉሣችን ገዳይ እንዲሰቀል እንፈልጋለን” አሉ፡፡
“ንጉሣችሁን ታውቁት ነበር?” ጠየቃቸው
“አዎ” በማለት መለሱለት፡፡
“ምን ይመስላል?”
ዝም፡፡
ንጉሡ ትንሽ አሰበና … “የገደለኝ ሰው ነገ ይሰቀላል” አላቸው፡፡ አጨብጭበው ሄዱ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ትልቅ መስቀያ ተዘጋጀ፡፡ ህዝቡም መስቀያውን ከቦ እየተጋፋ ሲንጫጫ ዋለ፡፡ አመሻሽ ላይ መስቀያው ፈርሶ ገመዱ ተፈታ፡፡
ሰዎቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አንዳንዱ “የተሰቀለው ሰውየ አስማተኛ ስለሆነ በደንብ አልታየኝም” ሲል፤ ሌላው “በጣም ረዥም ነው … ጥቁር፡፡ … ወይ ደግሞ አጭርና ቀይ ነው” እያሉ እንደመሰላቸው ተከራከሩ፤ “ማሪያም ያችትና” እያሉ ሰማይ ላይ አንጋጠው እንደዋሉት ያገሬ ሰዎች:: የሞተም፣ የገደለም፣ የተሰቀለም አልነበረም፡፡ ማርያምም አልታየችም፡፡ ውሸት ባህላቸው ስለነበረ እንጂ፡፡
ቀደም ባለ ጊዜ የአንድ ገበሬ ጎጆና የእህል ክምር ተቃጠለ ተባለ፡፡ የአካባቢው ሰው አውጫጭኝ በመቀመጥ ተመካከረና አጥፊውን ለመንግስት አሳልፎ ሰጠ፡፡ አራትና አምስት የሚሆኑ ሰዎች ህግ ፊት ቀርበው፣ ቃለ መሀላ ፈፀሙ፡፡ ድርጊቱ ሲፈፀም በዓይናቸው መመልከታቸውን መሰከሩ፡፡ ነገሩ ግን ሌላ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በሃሰት እየተወነጀሉ ይታሰራሉ፡፡ ውሸት ያካባቢው ባህል ነው፡፡ ነገሩን በዘዴ ለማረጋገጥ የተደረገ ጥናት ነገር ነው፤ የግዛቱ አስተዳዳሪ በራሳቸው ሰዎች በኩል ሆን ብለው የፈፀሙት፡፡ እንደተወራውም ሆነ፡፡ ውሸት ያካባቢው ባህል መሆኑን አረጋገጡ፡፡
ወዳጄ፡- ህዝብ ይዋሻል፣ መንግስት ይዋሻል፣ ሚዲያ ይዋሻል፣ ቤተ ዕምነቶች ይዋሻሉ፣ ዩኒርሲቲ ኮሌጆች ይዋሻሉ፡፡ … እና ማን ቀረ? … ጥያቄው:: መቼ ነው በራሳችን ላይ የምንነቃው? መቼ ነው ለራሳችን የምንታመነው … የሚል ነው፡፡
***
ነገ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ‹የንባብ ቀን› ተብሎ እንዲሰየም በፓርላማ ለማስወሰን እየጣረ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታውቋል:: በእጅጉ የሚበረታታ ሃሳብ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ገንቢ ምክሮች ባለማዳበራችን ይመስለኛል፣ ውሸት ያገራችን ባህል እየሆነ የመጣው፡፡ እርስ በርስ የማንግባባና መንገኞችም እየሆንን ነው:: አእምሮአችን እየዶለዶመ ከእውነት ርቀናል፡፡ በፍጥነት ካልነቃን ነገ “ንጉሡ እራቁታቸውን ናቸው” ብሎ እውነት የሚነግረን ህፃን እንኳን አናገኝም፡፡
ችግራችን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባንን ጉዳይ አለማወቃችን ነው፡፡ ብዙ ነገር ጎድሎብናል:: ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ የማናውቀውን ስናሯሩጥ፣ የምናውቀው አምልጦናል፡፡ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ ዕውቀት ሲተረጎም የሚፈልጉትን ማወቅ ነው፡፡ “መንቃት” (Conscious, awareness) የምንለው እሱን ይመስለኛል፡፡
ወዳጄ፡- “ጨርሶ ከመቅረት ዘግይቶ መምጣት” ይሻላል፡፡ … የፓርላማው ሰዓትም ይደውላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
“መጀመሪያ የአዕምሮ ስንቅህን ፈልግ፤ ሌላው በሂደት ይዳብራል፤ ባይሆንም አያጎልም” በማለት ይህንኑ ሃቅ ያረጋገጠልን ፍራንሲስ ቤከን ነው፡፡
ወዳጄ፡- እያንዳንዱ ሰው እራሱን የቻለ ዩኒቨርስ ነው” ሲባል በያንዳንዱ አዕምሮ ውስጥ የመላው ተፈጥሮ ቅሪት አለ ወይም እያንዳንዱ አእምሮ የመላው ተፈጥሮ ህዋስ ነው እንደማለት ነው፡፡ “The portion is the part of the whole and the whole is the part of the portion” ይላሉ ሊቃውንት፡፡ በቀጥታም ሆነ በረቀቀ መንገድ፤ ወዲያ ማዶ ከሚኖር፣ ጨርሶ የማታውቀው ሰው አካል ነህ፤ እንደ ማለት ነው፡፡ የአንተ ደም በሱ፣ የሱ ደግሞ ባንተ ውስጥ አለ፡፡ ልዩነቱ ቆዳችንና አዕምሮ ንቃታችን ላይ ነው፡፡ ቆዳችን ቢገፈፍ አንዳችን ካንዳችን መለየት አንችልም፡፡
ወዳጄ፡- ህይወት ረቂቅ ናት፡፡ መላው ዓለም በዓይን እንኳ ከማትታይ ሲንግል ሴል ሊፈለቀቅ እንደሚችል የሳይንስ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ የDNA እና Clonning ምህንድስናም እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፡፡
በሁለንተናዊ ዓለም ላይ በሚንተከተከው ተፈጥሯዊ ዑደት ውስጥ አንዲት ህዋስ ስትጎዳ ሌላው የማይጎዳበት፣ የአንዲት ህዋስ ጥቅም የሌላው ጥቅም የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ይነገራል፡፡ ዕፅዋት ያለ ምክንያት ሲጨፈጨፉ፤ አራዊትና እንስሳት ሲጎሳቆሉ ‹ለነቁ› ሰዎች ህመም ነው፡፡ በተቃራኒው ዛፎች ሲተከሉ፣ አራዊት፣ ወፎችና ሌሎች ነፍሳት መጠለያ ሲያገኙ፣ የሁሉም ተፈጥሮ ጥቅም ይሆናል፡፡
ወዳጄ፡- ተፈጥሮን ማከም ከማመንና አለማመን፣ ፖለቲከኛ ከመሆንና አለመሆን በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በጊዜ መንቃት ጥቅሙ ለዚህም ጭምር ነው፡፡ ንባብ፣ ንባብ፣ ሲባል ከመንጋ ስለሚነጥል፣ ከአመፅ ስለሚያርቅ ወይም የዕውቀት መንገድ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ በራስ ላይ ዘምተህ እንደ ማንኛውም የተፈጥሮ አካል፣ ሰው የመሆን ግዴታህን እንድታስቀድም ነው፡፡ በራስህ ላይ ስትነቃ በውስጥህ የተቀበረችው እውነት ‹ቦግ› ትላለች፡፡ ያኔ በአካባቢህ ያሉትን ሁሉ ታሳይሃለች፡፡ ፍሬዴሪክ ኒች እንደሚለው “ሃብታም አታደርግህም፡፡ ነፃነትህን ግን ታገኛለህ”
“Truth will not make us rich, but it will make us free”
ወዳጄ፡- የመንቃትና የነፃነት ነገር ከተነሳ ከትናንት ወዲያ ሐሙስ ዕለት የተባበረችው አሜሪካ የነፃነት ቀኗን አክብራለች፡፡ … Liberty day!!, July 4,1776. በአስራ ሁለት ግዛቶች አንድነተ ላይ ተመስርታ ዛሬ የደረሰችበት ደርሳለች፡፡ ሌላው፣ ሌላውን ነገር ብንተው እንኳ አሜሪካ ሃብታም፣ በማንኛውም መንገድ ራሷን መከላከል የምትችል፣ በህዋ ውስጥ መንደር የገነባች፣ ከተለያዩ ሃገራት ለተሰደዱ ህዝቦች መጠለያ መሆን የቻለች ስልጡን ሃገር ናት፡፡ አሜሪካ ታላቅ የሆነችው በራሷ ላይ በመንቃቷና የአንድነትን ጥቅም በማስቀደሟ ነው፡፡
በአንድነት ትንንሾቹ ግዛቶች ትልቅ ሃገር ሆነዋል፤ በመናቆር ደግሞ ትላልቆቹ ፈራርሰዋል (By union the smallest states trives, by discord the greatest are destroyed  ) የሚልህ ታላቁ ዳንኤል ዌብስተር ነው፡፡ … ገጣሚው፡-
ክረምትና በታ - ተጋብተው አንድ ላይ
ቆንጆ ልጅ ወለዱ - ቆንጆ ጠይም ፀሐይ
አባቷን ማትመስል - እናቷን ማትመስል
ሲስቁ መሳቅ ነው - ሲያዝኑ ልቧ ቁስል
መልዓክ መሰለችኝ - ‘ማታዳላ እንደ ሰው
አገሬም እንደሷ - ብትሆንልኝ ምነው፡፡
… በማለት ፅፎ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ፤ ወዳጄ የፓርላማው ሰዓት መች ይሆን የሚደውለው?
ሠላም!!

Read 783 times