Saturday, 06 July 2019 14:46

ቃለ ምልልስ ፈተናዎች የበዙበት የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 • ጽንፈኝነትን ማሸነፍ የምንችለው ዲሞክራሲያዊ መብትን በመከርከም አይደለም
       • መንግስት በምርጫው ጉዳይ ላይ ከተፎካካሪዎች ጋር መወያየት ይኖርበታል
       • የሚለማ መሬት አለን የሚለው ነገር፣ በጥናት መፈተሽ ይኖርበታል


           የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያልገጠሙት ፈተናዎችና አደጋዎች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከየአካባቢው ተፈናቅለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ዘር ተኮር በሆኑ ግጭቶች ሳቢያ ተማሪዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በታጠቁ ሃይሎች ጥቃቶችና ግድያዎች በህዝቦች ላይ ተፈጽመዋል፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በባህርዳርና በአዲስ አበባ በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ አስደንጋጭ ግድያ ተፈጽሟል፡፡ እኒህ ሁሉ ችግሮች፣ ከአንድ ዓመት በላይ ዕድሜ ላላስቆጠረው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ በእጅጉ የበዛ ነው፡፡ እስካሁንም በፈተና ብዛት ከሥራ ውጭ አለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስገርም ነው፡፡ ከዚህስ በኋላ? የዶ/ር ዐቢይ መንግስት የአመራር ዘዬውን ይለውጥ ይሆን? የእርሻ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅና የስራ ፈጠራ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አማረ ምግባሩን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲህ  አነጋግሯቸዋል፡፡


           የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አመራርን እንዴት ይገመግሙታል?
አንዳንዶች “ይሄ መንግስት ወዴት እንደሚወስደን አናውቅም፤ ፍኖተ ካርታ የለውም፤ፍኖተ ካርታ አልሰጠንም” ይላሉ፡፡ እኔ በዚህ ሃሳብ ፈጽሞ አልስማማም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው፤ ከዚህ በኋላ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በፍቅርና በመደመር፤ በሀገሪቱ ሠላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ቁርጠኛ የሆነበትን አቋም ደጋግመው ለህዝብ አሳውቀዋል፡፡ ለዚህም ጽንፈኛ ፖለቲካ የሚያራምዱትን ጨምሮ የትጥቅ ትግል ሊያካሂዱ የነበሩትን ድርጅቶች ሁሉ ወደ ሀገር ውስጥ ጠርቶ፣ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ የሚያስችል የቃልኪዳን ስምምነት አስቀምጧል፡፡ የምርጫ ቦርድን ለማሻሻል ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ሌሎች የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ግንባታ ማከናወን ደግሞ በራሱ የሚፈልገው ጊዜ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ይህ መንግስት የወደፊቱን መዳረሻ በሚያመላክት መልኩ ተጨባጭ የሆኑ መሠረታዊ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ ትልቁ ስጋት የነበረው የምትገኝበት ጂኦግራፊያዊ ቀጣና ሁኔታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሆነ ችግር ውስጥ ብትወድቅ፣ በአካባቢው ያሉ ሃይሎች በውስጥ ጉዳይ ገብተው ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ለዚህ አስቀድሞ አርቆ በማሰብ ከአካባቢው ሃገሮች ጋር የወዳጅነት፣ የሰላም፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮሽ ሊፈጥሩ የሚችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ነገር ቀላል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከአካባቢው ሀገራት ጋር የተጀመረው ቅርርቦሽና ወዳጅነት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች እያሉን መንግስት ምን እንደሚፈልግ? ወዴት እንደሚወስደን አናውቅም ማለት ምን ማለት ነው? ይልቁንስ እነዚህን ትልልቅ ነገሮች ህዝብ በተገቢው መንገድ አልተረዳው ከሆነ፣ እሱን የማስገንዘብና ለሀገሪቱ ምን ፋይዳ እንዳለው የመግለጽ ኃላፊነቱ የኛ ነው፤የሚያዲያው የምሁሩና የፖለቲከኛው፡፡
በአማራ ክልል አመራሮችና በመከላከያ ባለስልጣናት ላይ የተፈፀመው ግድያ፤ የለውጡ ሂደት ችግር እንዳለበት አመላካች  ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን አስተያየት አለዎት?
እዚህ ላይ አንድ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ፤ እጅግ አፋኝ፣ ሁሉንም ነገር በሃይል የማድረግ ባህሪ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት፤ አሁን ላይ ለቀቅ ነጻነት ያለ ገደብ መስጠት ሲጀምር፣ ለዲሞክራሲ መለማመጃ የሚሆን ክፍተት ሲፈጥር፤ ሌላም ያልተጠበቁ ያልታሰቡና ምንም ቢሆን ያልተዘጋጀንባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ መገመት ይገባል:: አሁን የተከሰተው ችግር የሚያሳየው የለውጡ ሂደት ትክክለኛ አለመሆኑን አይደለም፤ እንዲያውም የሂደቱን ትክክለኛነት ነው የሚያመለክተው፡፡ ይሄንን ሂደት ለማሰናከልና በሆነ መንገድ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚደረግ ጥረት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡
እንዲህ ያለው ነገር መከሰቱ አስደንጋጭም ቢሆን በታሪክ አዲስ ነገርም አይደለም፡፡ እንኳንስ እኛን ለመሰለ ሀገር ይቅርና የግብፁን አንዋር ሳዳትን የገደሉት የራሳቸው ጠባቂዎች ናቸው፣ አንድራ ጋንዲን፣ ራውል ጋንዲን የገደሉት የራሳቸው ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ሰፋ ያለ አመክንዮአዊ እይታ ሊኖረን ይገባል፡፡ በእውነቱ አሁን የተፈጠረው ችግር የሚያሳየው የለውጡን ጤናማ አካሄድ አለመያዝ ሳይሆን፤ ሂደቱ በፈተናና በትግል የተሞላ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ተፈትኖ ማለፍ ደግሞ የግድ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ አጋጣሚ ተፈትሸው መንጠር ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ዲሞክራሲ የሁሉ ነገር ፍቱን መድሃኒት ሆኖ አይደለም፤ ሁሌም ዲሞክራሲ ይኑር የምንለው፡፡ ከሱ የተሻለ ነገር ስለሌለ ነው፡፡ ወይ አምባገነንነትን ወይ ዲሞክራሲን መምረጥ አለብን:: ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ደግሞ በየትም አለም ጽንፈኞችን ማገድ ወይም መከልከል አይችልም፡፡ በአሜሪካን ሀገር ኒዮ ፋሽስቶች የፈፀሙትን በታሪክ ማየት እንችላለን፡፡ በአውሮፓም ውስጥ በነፃ ሃሳብን የመግለጽና የመደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ተጠቅመው የወጡ ጽንፈኛ ሃይሎች አሉ፡፡
በእኛም አገር በየቦታው ፅንፈኝነት እየገነገነ መጥቶ ለችግር እያጋለጠን ነው፡፡ ምንድን ነው መፍትሄው?
እርግጥ ነገሩ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ ነገር ግን ጽንፈኝነትን ልናሸንፍ የምንችለው ችግሮችን በመፍታት ነው፡፡ የተገኘውን ዲሞክራሲያዊ መብት በመከርከም ሳይሆን የበለጠ በማስፋፋት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ መብትን ወደ ኋላ መመለስ ችግሩን  አይቀንሰውም፤ እንዲያውም መልኩን ለውጦ እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡ የህግ የበላይነትም ስንል በደንብ ማሰብ አለብን፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ዜጐችም ሆንን በውጭ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ ልምዳችንና ባህላችን ምንድን ነው? የሚለውን በጥልቀት መፈተሽም ይገባናል፡፡ የህግ የበላይነት ስንል ፖሊስ ከሆነ ወይም ወታደር ከሆነ አሊያም እስር ቤት ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡ ይሄ የህግ የበላይነት ሊባል አይገባውም፡፡ ዜጐች መብትና ግዴታቸውን አውቀው፣ ለሚያደርጉት ነገር በተስማማንበት ህግ የሚጠየቁበትን ሁኔታ መፍጠር እንጂ ፖሊስና ዱላ ፈርተው ሃሳባቸውን በነፃ ከመግለጽ የሚገቱበት መሆን የለበትም፡፡ ተጠያቂነት መኖር አለበት ስንል ወደ ኋላ ተመልሰን ሰዎች ሃሳባቸውን ለመግለጽ የሚፈሩበትንና የሚሸማቀቁበትን ሁኔታ የምንፈጥር ከሆነ፣ እንደገና ችግራችን ውስጥ ውስጡን ተብላልቶ፣ የሚፈነዳበትን ጊዜ ለመጠባበቅ ይገደዳል፡፡
ውስጥ ውስጡን የሚሄድ፣ የተደበቀ በግልጽ የማይወጣ ነገር ደግሞ ቋቱ ተወጥሮ ሲሞላና ሲፈነዳ፣ ሁኔታው አስፈሪ ነው የሚሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ለፓርላማው የሰጡትን ማብራሪያ ሳዳምጥ ነበር፡፡ በመሠረቱ እሳቸው በተናገሩት በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ሽግግር ሲባል ደግሞ የሚያልቅ፣ መቋጫ ያለው ነገር አይደለም፡፡ የሚመጣም ፈተና አለ፡፡ በመንግስት በኩል እስካሁን የማየው፣ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ቀና መንፈስ ነው፡፡ ነገር ግን መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፣ በጊዜው መወሰድ አለባቸው፡፡ ለምሣሌ የጽንፈኝነቱን ጉዳይ ማንሳት እንችላለን፡፡ በመሠረቱ ለጽንፈኝነት ትልቁ መሠረት፣ ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ የኢህአዴግን አመጣጥ ስናይ፤ በብሔርተኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፤ በውስጡ ያሉትም በብሔርተኝነት የተመረቁ ናቸው፡፡ ከውስጡ የሚወጡትም በብሔርተኛነት ተመርቀው የወጡ ናቸው፡፡ ችግሩ ከውጪ የመጣ አይደለም፤ ከራሱ ከውስጡ ነው፡፡ አሁን ለምሣሌ በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ቀደም ሲል ራሱን እንደ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ እንደ አማራ ለመግለጽ ሲቸገር የኖረው ህዝብ ነው አሁን ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ በሆነ ደረጃ የገነገነው:: የዚህን ችግር ምንጭ፤ በጥሞና በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው ማየት የሚገባው፡፡ በዚህ መሃል ግን ከሰሞኑ በአማራ ክልል የሆነው ነገር በሙሉ የተወገዘና ፈጽሞ ሊሆን የማይገባው ድርጊት ነው፡፡
በሀገሪቱ ላይ ለተፈጠረው የእርስ በእርስ ጥርጣሬና ክፍፍል የዳረገን የፌደራሉ አወቃቀር ነው የሚሉ ሃሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ከፌደራል ስርአቱ ጋር የተያያዘ ነው የሚባለውን በተመለከተ፣ ችግሩን በጥናት ለይቶ መወያየትን ይጠይቃል፡፡ እኔ ከዚህ በፊት በፃፍኩት አንድ መጣጥፍ ላይ፤ እነዚህ ክልሎች ከአቅማቸውና መቆጣጠር ከሚችሉት በላይ ትልቅ ስልጣን ነው የተሰጣቸው፤በዚያ ላይም በተሰጣቸው ሥልጣን ልክ ፀጥታን ማስከበር ወይም ልማትን ማዳረስ አልቻሉም ብያለሁ፡፡ እንደኔ በህግ የተሠጣቸው ስልጣን፤ የፌደራል መንግስቱንም የሚገዳደር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው፤ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማለት፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ብለዋል፡፡ ይሄ የእሣቸው ትርጓሜ ነው፡፡ ወደ ህገ መንግስቱ ሄደን ህገ መንግስቱ ይተርጐም ቢባል፣ ምናልባት የእሣቸው ትርጉምና ህገ መንግስቱን የሚተረጉሙ ሰዎች ትርጉሙ ሊለያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም “እናንተ የዚህ ክልል ባለቤት አይደላችሁም፤ የዚህ ክልል ሰዎች አይደላችሁም” የሚለውን አባባል በየጊዜው ነው የምንሰማው፡፡ አንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት፤ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ተንቀሳቅሶና በምርጫ ተወዳድሮ፣ ክልሎችን የማስተዳደር መብትና ስልጣን አለው ወይ? እንኳንስ ለማስተዳደር ቀርቶ ራሱን ለህዝብ  ለማስተዋወቅም  ችግር እየገጠመው ነው፡፡   
እንደኔ ኢ-ማዕከላዊነትን ለማስፈን የግድ የፌደራል አወቃቀሩ በብሔር መሆን የለበትም:: ህዝብ በፈለገው አግባብ ክልል ቢያደራጅ እመርጣለሁ፡፡ ለምሣሌ በብሔር የተደራጁት ክልሎች ሠፋፊ ቦታ አካለው ይዘው ልማትና ፀጥታን ማስፈን ካልቻሉ፣ ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል፣ ለምን ወደ ሁለትና ሶስት ክልልነት ከፍ አይሉም? አሁን ባለው ሁኔታ፤ በብሔር የተከለሉት ክልሎች በአፄውና በደርግ ጊዜ የነበረው ጥብቅ የማዕከላዊነት ስልጣን ነው በእጃቸው ላይ ያለው፡፡ ይሄ አሁን ያለውን የማዕከላዊነት ሁኔታ እንድንፈትሽ ያስገድደናል፡፡ ህገ መንግስቱም ከዚህ አንፃር መፈተሽ አለበት፡፡ ይሄ ተረጋግቶ የሚከወን ጉዳይ ነው፡፡
በየጊዜው የሚገጥሙ የለውጡን ተደራራቢ ተግዳሮቶች እንዴት መወጣት ይገባል ይላሉ?
አንደኛ፤ በፍጥነት ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ፤ ወደ ምርጫው የምንገባ ከመሆናችን አንጻር፣ አሁን ባለው ሁኔታ፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ሠላማዊና አስተማማኝ ማድረግ እንችላለን ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ያሳስባሉ:: ስለዚህ መንግስት፤ ተፎካካሪ ከሚባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተቀምጦ ይሄን ጉዳይ በስፋት መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ፓርቲዎች ከምርጫው በፊትና በኋላ ያለባቸውን ኃላፊነት በጋራ ተቀምጠው ቢወስኑና በቃል ኪዳን ቢተሳሰሩ መልካም ነው:: ምናልባት አሸናፊ ሁሉንም የሚጠቀልልበት ሳይሆን፣ ተሸናፊ የሆኑትም የሚሳተፉበት አይነት መንግስት የመመስረት ስምምነትም ሊሆን ይችላል::  ይሄን ጉዳይ እየተወያዩ ወደ ጋራ ስምምነት ቢደርሱ ጥሩ ነው፡፡
የጥምር መንግስት አማራጭ ላይም ቢወያዩ መልካም ይሆናል፡፡ ለብዙ አይነት አጋጣሚ መዘጋጀት መቻል አለባቸው፡፡ በተቻለ መጠን የኢኮኖሚ ጉዳይንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኔ ለ33 አመት ያህል፣ በእርሻና በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ከስራ ፈጠራና ከድህነት ቅነሳ ጋር በተያያዙ የምርምር ስራዎች ላይ ነው የቆየሁት፡፡ ከዚህ አንፃር አንዱ የሚያሳስበኝ፤ የግብርና መስኩ ወጣቱን ሊስብ የሚችለው እንዴት ነው? መንግስት ስራ ፈጣሪ ከሚሆን ይልቅ የግል ባለሀብቱ ስራ ፈጣሪ መሆን የሚችልበት መንገድ ምንድን ነው? የሚሉና የመሳሰሉት ነገሮች በቶሎ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
መንግስት የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የሚችልበት መንገድ ይታይዎታል?
ሁለት ነገሮችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል፤ ሀገራችን ለሁላችን ትበቃለች፤ ሰፊ መሬት ውሃ፣ ተስማሚ አየር፣ ፀሃይ አለን እንላለን፡፡ ይሄ ትርክት ይበልጡን ሃሳባዊና ማራኪ ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡ ስለ ብሔራዊ ኩራታችን፣ ስለ ነፃነታችን ከምንተርከው ጋር ተመሳስሎ የሚቀርብ ትርክት ነው፡፡ ነገር ግን በኔ ግምት፣ እውነታው እንደዚያ አይደለም፡፡ ለምሣሌ ከአንድ ሄክታር የሚገኝ ምርት፣ በየጊዜው እያሽቆለቆለ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የእርሻ መሬትና የአርብቶ አደሩ የግጦሽ መሬት እንዲሁም የደን ሃብት ተብለው የተከለሉትን መሬቶች ከፈተሽን አሁን ላይ እየተደፈሩ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር በመጨመር ላይ በመሆኑ አዳዲስ ቦታ እየታረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ሠፊ የሚለማ መሬት አለን የሚለው ነገር፣ እንደገና በጥናት መታየት ይኖርበታል፡፡ ምርጥ ዘርና ዘመናዊ የግብርና ግብአቶችን ማቅረብ እንዲሁም  የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ማከናወን ካልቻልን፣ብዙም ውጤታማ አንሆንም፡፡ መንግስት፤ የእርሻ ምርምር ተቋምን  ማበረታታት አለበት፡፡
የእርሻ ምርምርና የተፈጥሮ እንክብካቤ ላይ የሚሠሩ ሃይሎችና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ የሚሠሩ ሃይሎች የተቀናጁ አይመስለኝም፡፡ ብዙ የሚታረስ መሬት አለን ግን ወጣቱ ወደ ግብርናው ሊገባ አልቻለም የሚባለው ነገር በደንብ መመርመር አለበት፡፡ ወጣቱ እንደ አባቶቹ ሞፈርና ቀንበር ይዞ መሬት ያርሣል ብሎ መጠበቅም አይቻልም፡፡ ወጣቱ በተቻለ መጠን ወደ አገልግሎት ዘርፉ ሊገባ የሚችልበትን መንገድ ነው ማፈላለግ ያለብን፡፡ ዘመናዊ የግብርና ግብአቶችን በማካተት ምናልባት ወጣቱን ወደ ግብርና መሳብ ይቻላል፡፡ እኔ “እንዴት ወጣቱን ወደ ግብርና ማስገባት ይቻላል?” በሚል ለአለማቀፍ የምርምር ተቋማት የሠራሁት አንድ የስትራቴጂ ጥናት አለ፡፡ በኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ውስጥ ያሉ ሰዎችም ያንን ጥናት ያውቁታል:: በተቻለ መጠን ጥናቶችን ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ጥናቶችን ተጠቅሞ ወደ ስትራቴጂ ቀረፃ ቢገባ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡     
ለዓለማቀፍ ተቋማት ያቀረቡት ስትራቴጂክ ጥናት ይዘቱ ምንድን ነው?
እኔ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት አድርጌ አልሠራሁም:: ብዙ ሀገሮችን የተመለከተ ነው፡፡ እነ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን ጋናን የመሳሰሉትን አገራት ያካትታል፡፡ ግን ያንን ስትራቴጂ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡

Read 6918 times