Saturday, 06 July 2019 15:14

ምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ዋንጫን መፎካከራቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


             በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ 24 ብሄራዊ ቡድኖች ባሳተፈው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ አገራት የበላይነት እያሳዩ ናቸው፡፡ ሁለቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ዞኖች በአህጉሪቱ እግር ኳስ ላይ ከሌሎቹ ዞኖች የላቀ ብልጫ መያዛቸውን በተለያዩ ሁኔታዎች ለማመልከት ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ ተዘጋጅቷል፡፡


              በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና  ከፍተኛ ውጤት
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለ24 ጊዜያት በመሳተፍ ቀዳሚ የሆነችው የሰሜን አፍሪካዋ ግብጽ ስትሆን፣ ከምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ አይቬሪኮስት 23፤ ጋና 21፤ ካሜሮን 19፤ ናይጀሪያ 18 እንዲሁም ዲ.ሪ ኮንጐ 18 የአፍሪካ ዋንጫዎችን ተሳትፈዋል፡፡ ከሰሜን አፍሪካ ቱኒዚያ 19፣ አልጀሪያ 18፣ ሞሮኮ 12 ጊዜ ከሰሜን አፍሪካ ተሳትፈዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካም ዛምቢያ 17 ጊዜ  ስትሳተፍ ከምስራቅ አፍሪካ 10 የአፍሪካ ዋንጫዎችን በመሳተፍ ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች፡፡
ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት በተካሄዱት 31 የአፍሪካ ዋንጫዎች 10 ጊዜ በማሸነፍ የሰሜን አፍሪካ ዞን ቀዳሚው ሲሆን ግብጽ (7 ጊዜ)፣ አልጀሪያ (1 ጊዜ)፣ ሞሮኮ (1 ጊዜ)፣ እንዲሁም ቱኒዚያ (1 ጊዜ) በማሸነፋቸው ነው፡፡ በ9 የአፍሪካ ዋንጫ ድሎች የምዕራብ አፍሪካ ዞን 1 የሚከተል ሲሆን ጋና (4 ጊዜ)፣ ናይጀሪያ (3) እንዲሁም አይቬሪኮስት 2 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡
የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ዞን 2 በ8 ዋንጫዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ካሜሮን (5 ጊዜ) ዲ.ሪ ኮንጐ 2 እንዲሁም ኮንጐ 2 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ዞን 2 ዋንጫዎች በሱዳንና ኢትዮጵያ  እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ዞን 2 ዋንጫዎች በደቡብ አፍሪካና ዛምቢያ ሻምፒዮንነት የመጨረሻውን ደረጃ ተጋርተዋል:: በ1977 እኤአ ላይ ከመካከለኛው አፍሪካ  ዛየር የአፍሪካ ዋንጫን ካሸነፈች በኋላ ከተካሄዱት  22 የአፍሪካ ዋንጫዎች ከምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ውጭ ያሸነፉት  ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው::
የአፍሪካ ዋንጫውን የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ካሸነፈ 56 ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ቡድን  ካሸነፈ ደግሞ 16 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫውን በ2008ና በ2010 እኤአ ግብጽ ያሸነፈች ሲሆን በ2012 እኤአ ደግሞ ሻምፒዮኗ ዛምቢያ ነበረች፡፡ ናይጀሪያ በ2013፣ አይቬሪኮስት በ2015 እንዲሁም ካሜሮን በ2017 እኤአ የአፍሪካ ሻምፒዮኖች ነበሩ፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው ከፍተኛ ግብ ግቢዎች
በአፍሪካ ዋንጫው የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ ላይም የምዕራብ አፍሪካ ተጨዋቾች በብዛት ቢገኙም  ሰሜን አፍሪካ በግብጽ መወከሏ አልቀረም፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 18 ጐሎች በማስመዝገብ የምንጊዜም ከፍተኛ አግቢ የሆነው የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ ሲሆን፣ የአይቬሪኮስቱ ሎረንት ፓኩ በ14፣ የናይጀሪያው ራሺዲ ያኪኒ በ13፣ የግብፁ ሃሰን አልሻዝል በ12 ጐሎቻቸው ተከታታይ ደረጃዎችን ይዘዋል፡፡ የካሜሮኑ ፓትሪክ ምምቦማ፤ የግብፁ ሆሳም ሀሰንና የአይቬሪኮስቱ ዲዲዬር ድሮግባ በ11 ጐሎች የከፍተኛ ግብ አግቢውን 5ኛ ደረጃ ተጋርተዋል፡፡  
የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ጠንካራ ስብስብ
ሴኔጋል 385.30 ሚሊዮን ዩሮ
በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት 24 ብሔራዊ ቡድኖች በተጨዋቾች ስብስባቸው
የዋጋ ተመን ሲወጣላቸው እስከ 10ኛ ደረጃ የያዙት የሰሜንና የምዕራብ አፍሪካ አገራት ናቸው:: የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በ385.30 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ በመተመን አንደኛ ሲሆን አይቬሪኮስት በ284.78፤ አልጀሪያ በ197.9፤ ግብፅ በ194.2፤ ናይጄርያ በ192.10 እንዲሁም ሞሮኮ በ176.3 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን እስከ አምስተኛ ደረጃ አላቸው፡፡ ካሜሮን በ131.1፤ ማሊ በ122.7፤ ጊኒ በ119.5፤ ጋና በ116.45፤ ዲሪ ኮንጎ በ78.15፤ ቱኒዚያ በ71.25፤ ደቡብ አፍሪካ በ33.5፤ ቤኒን በ17.65፤ ማዳጋስካር 14.05 እንዲሁም ኡጋንዳ በ6.15 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን እስከ 16ኛ ደረጃ በመያዝ ለ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ የደረሱ ብሄራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ ከ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ጨዋታ የተሰናበቱት 8 ብሄራዊ ቡድኖች ኬንያ በ1.08 ሚሊዮን ዩሮ፤ ዚምባቡዌ በ952ሺ ዩሮ፤ አንጎላ በ921ሺ ዩሮ፤ ታንዛኒያ  በ643ሺ ዩሮ፤ ጊኒ ቢሳዎ በ625ሺ ዩሮ፤ ብሩንዲ በ412ሺ ዩሮ፤ ናሚቢያ በ207ሺ ዩሮ እንዲሁም ሞውሪታኒያ በ204ሺ ዩሮ የዋጋ ተመን እስከ 24ኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ 150 ሚሊዮን ዩሮ
በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተሳተፉ 24 ብሄራዊ ቡድኖች 552 ተጨዋቾች መካከል በዝውውር ገበያው  ወቅታዊ የዋጋ ተመን ውዱ ተጨዋች የሆነው ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ ሲሆን በ150 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ዞኖችን  በመወከል ከሚሳተፉ አገራት መካከል የምዕራብ አፍሪካና የሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ የሚገኙ  ተጨዋቾች በአውሮፓ እና በዓለም የእግር ኳስ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ በመሆናቸው ብልጫ ይወስዳሉ:: ከእነዚህ የአፍሪካ ዞኖች የሚወጡ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በአማካይ ዋጋቸው ከፍተኛው 150 ሚሊዮን ዩሮ ዝቅተኛው እስከ 15 ሚሊዮን ዩሮ ነው:: የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ዞኖችን በሚወክሉት ብሄራዊ ቡድን የሚሰለፉ ተጨዋቾች  በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመናቸው ከ10 ሚሊዮን ዩሮ በታች ሲሆን ብዛታቸው በጣት የሚቆጠር ነው፡፡
በወቅታዊው የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን የ27 ዓመቱ ግብፃዊው መሐመድ ሳላህ  ለእንግሊዙ ሊቨርፑል እየተጫወተ በ150 ሚሊዮን ዩሮ የመጀመርያውን ደረጃ ሲወስድ፤ የ27 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ሳዲዩ ኦማኔ በእንግሊዙ ሊቨርፑል በ120 ሚሊዮን ዩሮ፤ የ28 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ካሊድ ኩለባሉ በጣሊያኑ ናፖሊ በ75 ሚሊዮን ዩሮ፤ የ24 ዓመቱ አይቮሪኮስታዊ በ65 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የ24 ዓመቱ ካሜሮናዊ በ2 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን እስከ አምስተኛ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡ ሪያድ ማህሬዝ  ከአልጀሪያ 60 ሚሊዮን፤ ቶማስ ከጋና 50 ሚሊዮን፣ ዌልፍሬድ ዛሐ ከአይቪሪኮስት  45 ሚሊዮን፤ ሀኪም ሃዛዬክ  ከሞሮኮ 40 ሚሊዮን፤ ዊልዬድ ጊድ
ከናይጀሪያ ለ15 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው እስከ 10ኛ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡
አፍሪካን በዓለም ዋንጫ በመወከል
በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ አፍሪካን የሚወክሉት በምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ዞኖች የሚገኙ አገራት ናቸው፡፡ ሩስያ ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ግብጽ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ከሰሜን አፍሪካ እንዲሁም ናይጀሪያ እና ሴኔጋል ከምዕራብ አፍሪካ ነበሩ፡፡
በ2014 እኤአ ብራዚል ባስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ካሜሮን ፣ጋና፣ አይቬሪኮስት፣ ናይጀሪያ ከምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም አልጀሪያ ከሰሜን አፍሪካ ነበሩ::  በ2010 እ.ኤ.አ ላይ 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ደቡብ አፍሪካ በአዘጋጅነቷ ስትሳተፍ  አልጀሪያ ከሰሜን አፍሪካ፣ ጋና፣ ካሜሮን፤ አይቮሪኮስትና ናይጀሪያ ከምዕራብ አፍሪካ ነበሩ:: በ2006 እ.ኤ.አ ጀርመን ባዘጋጀችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካዊውን ዞን በመወከል አንጐላ ስትካፈል ቱኒዚያ ከሰሜን አፍሪካ ጋና፣ አይቬሪኮስትና ቶጐ ከምዕራብ አፍሪካ ተሳትፈዋል:: በ1988 እና በ2002 እ.ኤ.አ በተካሄዱት የዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ከመሳተፏ ባሻገር ከዚያ በፊት በተካሄዱት የዓለም ዋንጫዎች የሰሜንና የምዕራብ አፍሪካ አገራት በዓለም ዋንጫው አህጉራቸውን ወክለዋል፡፡
የግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ 143.87 ሚሊዮን ፓውንድ
ሐብታሞቹ የአፍሪካ ክለቦችና የሊግ ውድድሮች በሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ የሚገኙት ናቸው፡፡
በሰሜን አፍሪካ ያሉ ክለቦች በዓመት ከ8-15 ሚሊዮን ዶላር በጀት የሚያንቀሳቅሱ ሲሆን በተለይ በግብጽ፤ በአልጄርያ፤ በቱኒዚያ እና በሞሮኮ የሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች በጣም መጠናከራቸው የብሄራዊ ቡድኖቹን የፉክክር ደረጃ አሳድጎታል:: በምዕራብ አፍሪካ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኖች በርካታ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ማሰባሰባቸው የአፍሪካ ዋንጫውን የበላይነት አስገኝቶላቸዋል:: የምዕራብ አፍሪካ አገራት በደካማ የፌዴሬሽን አስተዳደር ቢፈተኑም የሚያካሂዷቸው የክለብ ውድድሮች  በስፖንሰርሺፕ፣ በተለያዩ የንግድ ስራዎች በማሟሟቅ ልዩ ገበያ በመፍጠራቸው ምሳሌ ይሆናሉ፡፡
18 ክለቦች የሚወዳደሩበት የግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ የተጨዋቾች ስብስቡ በ143.87 ሚሊዮን ፓውንድ የዋጋ ተመን ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ይጠቀሳል:: የሞሮኮው ቦቶላ ፕሮ ሊግ በ134.28 ሚሊዮን ፓውንድ፤  የደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪሚዬር በ130.91 ሚሊዮን ፓውንድ፤ የአልጄሪያው ሊግ ፕሮፌሽናሌ1 በ82.31 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም የቱኒዚያው ሊግ1 ፕሮ በ81.32 ሚሊዮን ፓውንድ እስከ 5 ያለውን ደረጃ ይወስናሉ::
ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ በ202
ሚሊዮን ዶላር ገቢ
በተጨዋችነት ዘመናቸው ከፍተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የአፍሪካ ሃብታም ተጨዋቾች ደግሞ በአመዛኙ ከምዕራብ አፍሪካ የፈለቁት  ናቸው:: የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ 202 ሚሊዮን ዶላር፤ የአይቮሪኮስቱ ያያ ቱሬ 170 ሚሊዮን ዶላር፤ የአይቮሪኮስቱ ዲዲዩር ድሮግባ 155 ሚሊዮን ዶላር፤  የናይጄርያው ጄጄ ኦኮቻ 150 ሚሊዮን ዶላር፤ የናይጄርያው ኑዋንኩ ካኑ 100 ሚሊዮን ዶላር፤ የጋናው ማይክል ኤስዬን 70 ሚሊዮን ዶላር፣ የቶጎው ኢማኑዌል አደባዬር 57 ሚሊዮን ዶላር፤ የናይጄርያው ጆን ኦቢ ሚኬል 50 ሚሊዮን ዶላር፤ የአይቬሪኮስቱ ኮሎ ቱሬ 43 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የጋናው ሱሊ ሙንታሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ከ1 እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
ከ361 በላይ ናይጄርያዊ
ፕሮፌሽናሎች በዓለም ዙርያ
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ከሚሰለፉ 552 ተጨዋቾች መካከል 315 በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ 201 ከአፍሪካ ፤ 32 ከቻይና እንዲሁም 4 ከአሜሪካ ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው ለመሰለፍ የተገኙ ናቸው፡፡ በዓለም እግር ኳስ ላይ ናይጀሪያ 361 ፕሮፌሽናሎች በማሰማራት ከአፍሪካ የመጀመርያዋ አገር ስትሆን ጋና 286፣ ሴኔጋል 203፤ አይቬሪኮስት 202፣ ካሜሮን 178 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ለዓለም እግር ኳስ በማቅረብ  ይጠቀሳሉ፡፡


Read 12263 times