Print this page
Saturday, 13 July 2019 11:11

የአማራ ክልልን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አብን አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

አዴፓ ያለማንም ተፅዕኖ አመራሮችን እንዲሰይም ጠይቋል

                የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የአማራ ክልል መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝና በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ያስታወቀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ አባላቱ በየደረጃው ካለው የመንግሥትና የአዴፓ መዋቅር ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ሕዝቡን የማረጋጋትና ሰላምና ደህንነቱን የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
በአማራ ክልል ባለሥልጣናት ላይ ከተፈፀመው ግድያ ጋር በተያያዘ ከ250 በላይ አባላቱ መታሰራቸውን ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የጠቆመው አብን፤ ሕዝብና አገርን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡
አብን ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ በጥልቀት ገምግሞ ባወጣው ባለ 7 ነጥብ መግለጫው፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥትና ገዥው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በተፈፀመው የባለስልጣናት ግድያ የተነሳ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመሸፈን ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ በፀዳ ሁኔታ መሪዎቹን እንዲሰይም፤ ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ውዥንበሮችንም እንዲያጠራ ጠይቋል፡፡
‹‹የተፈጠረውን ግድያ ተከትሎ በክልል የፀጥታ መዋቅር ላይ ለአማራ ሕዝብ ቀና አመለካከት የሌላቸው ሃይሎች በቃልም በተግባርም የማዳከም ሴራና ስራ ውስጥ በግልጽ     እየታዩ ነው›› ያለው አብን፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የአማራን ሕዝብ ለማንበርከክ የሚፈልጉ ሃይሎች ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ ንቅናቄው አያይዞም፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለአግባብ የተያዙ የፀጥታ አመራሮችና አባላት ከእስር በአስቸኳይ ተለቀው ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱም ጠይቋል፡፡
‹‹የክልሉ ልዩ ልዩ የጸጥታ ዘርፍ አመራሮችና አባላትም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የሕዝባችንን አንድነትና ደህንነት ለማስጠበቅ እንድትሰሩ እንጠይቃለን›› ያለው አብን፤ “በየደረጃው ያሉ የአብን አመራሮችና አባላትም በሚፈለገው ሁሉ ከፀጥታው ሃይሎች ጎን ሆነው ይተባበራሉ” ብሏል፡፡
የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልል በአባላቶቼና አመራሮቼ ላይ እስራትና ማዋከብ እየተፈጸመ ነው ያለው አብን፤ ከዚህ በተጨማሪም በ“አስራት” ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ በአዲስ አበባ ባለ አደራ ም/ቤት አመራሮች፣ በመንግሥት ላይ ትችት ባቀረቡ ግለሰቦች ላይ የተካሄደው የጅምላ እስር እንዲሁም በእስረኞች ላይ እየተፈጸመ  ያለው ኢ-ሰብአዊ አያያዝ እንዲቆም ጠይቋል:: ይሄን ጉዳይም በሰብዓዊ መብት መከበር ላይ የሚሰሩ አገር በቀልና አለማቀፍ ተቋማት እንዲከታተሉትና በመንግሥት ላይ አስፈላጊውን ግፊት እንዲያደርጉ አብን ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ በአዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሠሩ የፓርቲውን አባላት ለመጠየቅ ሐሙስ እለት ባመሩበት ወቅት በዚያው እሣቸውም መታሠራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የታሠሩበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑንና ድርጊቱ አፈና እንደሆነ አብን አስታውቋል:: አቶ ክርስቲያንም ሆኑ አባላቶቹ በአፋጣኝ እንዲለቀቁም ፓርቲው ጠይቋል፡፡


Read 9111 times