Saturday, 13 July 2019 11:14

ፋና ብሮድካስቲንግ የራሱን ተቋም የሙስናና የአስተዳደር ችግሮች እያጣራ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ሠራተኞች ለአጣሪ ኮሚቴው ጥቆማ እየሰጡ ነው


              በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ ውስጥ ይፈፀማሉ የተባሉ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከድርጅቱ ሠራተኞች የተለያዩ ጥቆማዎችን እየተቀበለ መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ፡፡
ከማናጅመንት አባላት ሶስት እንዲሁም አንድ ከሠራተኞች በአባልነት የተካተቱበት ኮሚቴው ካለፈው ሣምንት ጀምሮ በተቋሙ ከሚፈፀሙ የሙስና ተግባራትና የአስተዳደር ችግሮች ጋር የተያያዙ በርካታ ጥቆማዎች መቀበሉን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ባለፉት አመታት በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ሲፈፀም እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ በአመራር ላይ ያሉ አንዳንድ የስራ ኃላፊዎችም “ከሄደው ከመጣው” የመንግስት አካል ጋር በመመሳሰል በአድርባይነት በሠራተኞች ላይ በርካታ በደሎች መፈፀማቸውን ይናገራሉ፡፡
በሠራተኞች ላይ ከሚፈፀሙ የአስተዳደር በደሎች መካከል ከዚህ ቀደም የኦነግ አስተሳሰብ አላችሁ በሚል የተባረሩትን ጋዜጠኞች ጨምሮ በሰበብ አስባቡ በብሔር እየለዩ የማባረር ድርጊቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል - ምንጮች፡፡
አንዳንድ አመራሮች ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ቦታቸውን ተገን በማድረግ በቀጥታ በጣቢያው የዘገባ ይዘቶች ላይ ጣልቃ በመግባት የግል ጥቅም የሚያገኙባቸውን ዘገባዎች በትዕዛዝ የማሠራት ድርጊትም በስፋት ሲፈፀም መቆየቱን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ የጣቢያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከባለሀብቶች ጋር የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር  ዘገባዎች በጫናና በትዕዛዝ እንደሚያሰሩ የሚናገሩት ምንጮች፤ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ እነዚህን ጉዳዮች በጥልቀት እንደሚገመግም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በሠራተኛው ስማቸው በክፉ የማይነሳው የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመስል በግል ምክንያት ኃላፊነታቸውን ሊለቁ ይችላሉ መባሉን ተከትሎ ተተኪያቸው “ማን ይሆን”? የሚለው ጉዳይ በሰራተኞች ዘንድ ጭንቀትና ስጋት መፍጠሩን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡  
በተቋሙ ይፈፀማል የሚባለውን የሙስና ድርጊትና የአሠራር በደሎች እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ በአካልም፣ በስልክም በርካታ ጥቆማዎች እየቀረቡለት እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮች፤ አንዳንድ ማጣራት የሚካሄድባቸው አመራሮች የኮሚቴውን ተግባር ለማደናቀፍ ውሣኔ ሰጪዎችን በጥቅም ለመደለልም ጥረት እያደረጉ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
የተጀመረው የአጣሪው ኮሚቴ ሥራ ሲጠናቀቅ ለተቋሙ የማናጅመንት አካል ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ፤ ፋና ቴሌቪዥንን ጨምሮ ኤፍ ኤም 98.1 እንዲሁም በየክልሉ በርካታ የኤፍኤም ጣቢያዎችንና ሬዲዮ ፋናን ያስተዳድራል፡፡


Read 8719 times