Saturday, 09 June 2012 08:27

አበባ - ልብ - ዳይመንድ ጦር - ካርታ

Written by  ዮሐንስ ሀብተማርያም
Rate this item
(1 Vote)

አይን ከሚያንከባልሉባት …በቅዠታቸው ከሚሴስኗት…በብሌን ጥፍራቸው እያንዳንዷ ስሜቷ ሳትቀር ለመቧጠጥ ከሚመኙ ወንዶች መካከል አንዱ ነበርኩ…ያይኖቻችንን ብዛት ጠንቅቃ ታውቅ ነበር፡፡ ስራችን ያልኮፈሳት መስላ…የጥንቃቄ ካባ እንደደረበች ሁሉ…መምረጥ ስለነበረባት መረጠች፡፡ አይኔ ያምራል፡፡ ትክክለኛ ግጣሟ መሆኔን ከመጠርጠር በላይ ወደ ማወቁም ደረጃ በመቃረቤ ታጥቤ - ታጥኜ ጠበኳት፡፡ መረጠችኝ፡፡ አበባ ይዤላት የመጣሁትን አበባ በአድናቆት ስታየው ቆየች …በርጥብ ከንፈሯ ሳመች…ወደ አፍንጫዋ አስጠግታ መዓዛውን ማገች…በሳንባዋ ሙሉ አየር ዋጠች…ሁለመናዋ በእርካታ አበጠ…“አበባ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

“ምንድን ነው?”

“አበባ የተክሎች የወሲብ አካል ነው፡፡ ስናደንቀውና ስንወደው መኖራችን ለራሳችን አካል ካለን ፍቅር የተነሳ ነው…” እየዋጠኝ ባለው የመገረም ረግረግ ውስጥ ቀስ በቀስ እየሰጠምኩ…ላለመዋጥ ከቁመቴ በላይ ሆኖ ያደገውን ጨፌ በመዳፌ ሙሉ እየዘገንኩ…እያሟለጨኝ…ስዘግነው ---ሲያሟልጨኝ…ቀስ በቀስ ስጠልቅ…በትግል ውስጥ ሆኜ ሳደምጣት “…እኔና አንተም እድሜያችንም አበባ እንደሆንን ታውቃለህ?”

“ማለት - የወሲብ አካል ነን እያልሽ ነው?” - ሀፍረቴም ሳቄም እኩል እያብለጨለጩ፡፡

የተከራየናት አልቤርጐ ንፁህ ብትሆንም እንደወፍ ጐጆ ያለች ነች፡፡ ዘና ብሎ ለመቀመጥ ትርፍ ቦታ የሌላት…ተጠባብቆ…ተደራርቦ ለመተኛት የምታስገድድ፡፡

“ቀላል ነው - ከኔ ጋር ግብረ ስጋ ትፈልጋለህ - እኔም እንዳንተው፡፡”

ሳቅ ባረገዘ ዝምታዋ ምኔ ውስጥ እንደምታይ እንጃላት…በራስጌ በኩል የነበረችው ሴት በግርጌው ወገን ወዳለሁት እኔ በዳዴ መጣች…

አበቦች ሆንን…ንቦች ቀሰሙን…እንፋሎታችንን - ላቦታችንን - ወዛችንን - ሲቃችንን ወስደው ጣዝማ ማር ሰሩ - ጥፍጥናው - ቃናው - አጀብ የሚያሰኝ ጣዝማ…

በዚህ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ አበባ ስንሆን ኖርን…

አበባ መዝዤ ጣልኩ…

አየት አደረገኝ…አጣጣሌ እንዳስፈለገው ሁሉ ከንፈሩን ሲያሸሽ ውብ ጥርሶቹ ፍንትው አሉ፡፡

ንባባቸው…

“…ካርታ ጨዋታ ነው…ጨዋታም ሂደት ነው….” የሚሉ ቃላትን ደርድሮ፡፡

ልብ

በመደነቅ እያየኋት ነው - በሚያምረው አይኔ፡፡ እሷ ደግሞ እኔን ታያለች - እኔን ብቻ፡፡ በሷ ውስጥ ዓለምን እያየሁ ነው…በሷ ውስጥ ሴትነትን እያየሁ ነው…በሷ ውስጥ ሰው መሆንን እያየሁ ነው - ሰው ፆታ ነው - ሰው ጌታ ነው - ሰው አበባ ነው - ሰው ሎሌ ነው - ሰው ልብ ነው…በሷ ውስጥ …እያየሁ ነው …ስታየኝ …ስታየኝ…ቆይታ ያልገባኝ ኪን የገመደውን ፈገግታዋን ለገሰችኝ፡፡

በሷ ውስጥ የሚታይ ሰው መሆንነት ምን ይመስል ይሆን?

“ልብን መስጠት ይከብዳል…እንደዋዛ ልብ የሚሰጥ ሰው ያለ አይመስለኝም ነበር…አንተ ግን ሰጠኸኝ…አልሰጠኸኝም እንዴ? ተሳሳትኩ እንዴ?”

እንደ ሙልሙል ከሚገመጥ ፌዟ ጋር የምታወራው ወሬ…ልብ ስለመቀበሏ…እኔ አይነሸጋው…አይነ መልካሙ ስለሰጠኋት ልቤ…

“በምን አወቅሽ…ማለቴ እንደሰጠሁሽ?”

“ቀላል እኮ ነው…ፍቅር የራሱ ቋንቋ አለው…ይናገራል…”

ልብ መዝዤ ወረወርኩለት…

አየት አደረገችኝ…በአጣጣሌ የተፈተፈተ - የተበጣጠሰ - በቅባት የረሰረሰ ፈገግታውን ሲያሳየኝ…የውብ ጥርሶቹ ንባብ…

...ጨዋታ ሂደት ነው…ሂደትም ሕይወት ነው…የሚሉ ፊደላትን ደርድረው…ሳቅ አርግዞ የወረዛ አይኑ እላዬ ላይ እየተንከባለለ፡፡

ዳይመንድ

እንዲህ …እንዲህ…አድናቆት ከፍታ ላይ በተሰቀለ - በሙሉ መንፈሷ ስትመለከተኝ በምድር ላይ ካለ ነገር ሁሉ በላይ ግራ ታጋባኛለች፡፡

“በየትም አቅጣጫ አማልላለሁ…ከከበረ ነገር ሁሉ በላይ ነኝ - አልማዝህ ነኝ አይደል…አይደለሁም አንዴ?”

“ነሽ”

“እንቁህ አይደለሁም እንዴ?”

“ነሽ”

“ሴራሊዮንን ታውቃታለህ?“

“አውቃታለሁ”

“ጆግራፊ አይደለም የምጠይቅህ…ልጆቿን ምን በላባት?”

“ጦርነት”

“አይደለም - አልማዝ ነው የበላባት”

“አልማዝ እኮ የጦርነቱ መዘዝ ነው?”

“መዘዝ እንጂ ውጤት አይገድልም…ጥንስስ እንጂ ጠላ አያሰክርም”

ዳይመንድ መዝዤ ፊቱ ላይ አሽቀነጠርኩለት…

አልተበሳጨም …ውብ ጥርሶቹ ለኔ ተሰጡ…ፀሐይን መስያቸው…ንባባቸው….ካርታም ሕይወትም ባሉበት አይቆሙም…የሆነ ቦታ ላይ ጀምረው የሆነ መጨረሻ ላይ ያከትማሉ…የሚል ነበር፡፡

ጦር

ምን እንዲህ እንዳደረጋት እኔ ምን አውቄ…ሁሌም ግራ የምታጋባኝ ሴት…ሁሉም ነገር የሚቀላት ሴት - ቀላል እኮ ነው - ስለምትል…

ብስጭትም የቀለላት ሰው…እኔን ከምንም ያልጣፈችኝ ሰው…

“ምንም ነገር ማሰብ አልፈለግም …በተለይ - በተለይ - ስላሳለፍናቸው ጊዜያት ምንም አታንሳብኝ!”

“ለምን እንደሱ ትያለሽ? ለኔ ስናደርገው የኖርነው ሁሉ ትዝታ ነው፡፡”

ገለፈጠች - የተከፈተ አፏ ከቧልት ማህፀን ውስጥ የፈለፈላቸውን የለግጥ ፍሬዎቹን እንደ ኮሽም እያሆመጠጠኝ…ይቺ የፌዝ ሴቴ መሬት የሆነች ሰው…በኔ ላይ ተረፈ ምርቷን ልታራግፍብኝ እየጣረች ነው፡፡

“ትዝታ ብሎ ተረት አይገባኝም…ነገር ሁሉ አሁን ነው፡፡ የምልህ ግን ይገባሀል? አሁን ካንተ ፍቅር የለኝም…ካንተ ብቻ ሳይሆን ከማንም የለኝም…ነፃ ሰው መሆን እፈልጋለሁ…”

ረጅም ሳቋን ለቀቀች - ለነፃነቷ! ሌላውን እግር ከወርች ጠፍረው ነፃ መሆን አለ እንዴ? ሌላውን የብርሃን ፍንጣቂ ወደ ሌላው ድቅድቅ ወይኒ ጥሎ የነፃነት መዝሙር ማቀንቀን ምን ይሉት ፈሊጥ ነው…

“…ቀላል እኮ ነው…እኔ እሄዳለሁ *- ሌላ ሴት ትቀበላለህ - እኔም ነፃ መሆኔ ሲያከትም ሌላ ወንድ ገላ ላይ እጣበቃለሁ - አለቀ፡፡”

“አላለቀም - እንዲህ በቀላሉ የሚያልቅ ነገር ውስጥ አልከተትሽኝም፡፡”

መላ አካሌ ተቆጣ፡፡ እረግቶ የኖረ እሳተ ጐሞራዬ ካደፈጠበት መላወስ ጀመረ፡፡

“አታክብደው - ግድ የለህም ቀላል ነው፡፡ በከበደ ዓለም ውስጥ እንደመኖር የምጠላው ነገር የለም፡፡ ነፃ መሆን ነው የምፈልገው…”

ትግዕስቴን እያሙዋጠጠች ነው…ሰይጣኔን ጠራችው…የኔ ከተፎ - ከተጠራበት መጥቶ እንደግራኝ ድንጋይ ተከመረብኝ…

“ከሰው ጋር መኖር ትግል አይደለም..ከሆነ ደግሞ ትርፉ ስቃይ ነው…አንተም ነፃ እኔም ነፃ መሆን አለብን…”

“ነፃ ሙሆን ለምን አማረሽ?”

“አየህ አንድ አይነት አበባ መሆን አልፈልግም…አንድ ልብ ብቻ መቀበል አልፈልግም…አንድ አልማዝ ብቻ መሆን እጠላለሁ…አንተም እንደዛ ሆነህ እስክትሞት አብረኸኝ ለመኖር መፍቀድ የለብህም…”

ከተፎው ሰይጣኔ - ጥሪዬን ሰምቶ መጥቷል - ደሜን አንተክትኳል…አበባ - ልብ - ሴራሊዮን - ዳይመንድ - ጥንስስ - እኔ - ሰይጣኔ - የተቆለለብኝ ሰይጣኔ…

ስታሾፍ “አታሹፊ” አልኳት፡፡

“ማሾፍ እኮ የኑሮ ቅመም ነው” አለችኝ፡፡

“ሹፈት አይጠቅምሽም፡፡”

“መጥቀም አለመጥቀሙን ለኔ ተውልኝ፡፡”

እንደለማኝ እንጀራ ነካክተው ሲተውኝ ያመኛል …ከጀመሩኝ እንደሚያስጐመጅ አጥንት ፈረካክሰው መቅኔዬንም ሳይቀር መመጥመጥ አለባቸው - ያለበለዚያ እቆጣለሁ፡፡

“የተለያየ ቀለም ያለው አበባ መሆን አይጥምህም …የተለያየ ስብዕና ያለው ልብ ውስጥ መኖር እንደ አማልክት አያደርግህም…

የተለያየ መንፀባረቅ ያለው አልማዝ መሆን…” እያወራች እመር ብዬ ተነሳሁ…የክህደቷን ልዕልት በሰላ ስለት አማሰልኳት፡፡

የጣልኩትን ጦር እያየ ተበሳጨ…ውብ ጥርሶቹ ጠፉብኝ…እጁ ላይ የነበሩትን ካርዶች ወረወረብኝ፡፡

“አፈቅራት ነበር ስትል አታፍርም!? በዘመንህ - ራስህን እንጂ ማንንም አፍቅረህ አታውቅም” አለኝ የእስር ቤት ጓደኛዬ፡፡

በግራ መዳፉ ፊቱን እየፈተገ መጽሐፈ ሲያነብ ውሎ ያድራል፡፡

 

 

Read 4951 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 09:25