Monday, 15 July 2019 09:31

ካፒቴን አምሳለ ጓሉ እንደኛ ነው

Written by  (ተምሳሌት ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ 2007
Rate this item
(1 Vote)

 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አብራሪ


           በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ፣ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀሰብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረው ግን በዚያን ጊዜ ነበር፡። ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣ አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለሁ:: አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድንጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፣ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው ጉብኝታችን፣ እንዴት የበኩር ልጁ የእድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡
የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፣ የመጀመርያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩት ነው ያደግሁት:: አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ ‹‹ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው›› ብለውኝ እያውቁም፡፡ ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬው ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እያንዳንዱ የማህበረሰቡ አባል እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ:: የእለት ተዕለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርቴ በርትቼ እንድገፋ ያበረታቱኝ ነበር:: አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን (አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛ ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የሕዝብ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ፣ ሥነ-ህንጻ  (አርኪቴክቸር) ትምህርት መማር ጀመርኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የልጅነት ህልሜን አልዘነጋሁትም ነበር፡። የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመርያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡። እኔም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡። የሥነ-ህንጻ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የመግቢያ ፈተናውን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡ ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ሥልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርት ገደል እንደመክተት ሆነብኝ:: የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ሥልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ሥልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በህዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም፤ በረዳት አብራሪነት ለ4ሺ475 ሰዓት አውሮፕላኖችን አብርሪያለሁ፡፡ ከዚያም ከተለያዩ ፈተናዎች፣ ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ፣ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ሥልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመርያ በረራዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ በ2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡ የሰለጠንኩትም ሆነ የሰራሁት በበርካታ ዓይነት አውሮፕላኖች ነው:: ከእነሱም መካከል ፎከር 50፣ ዳሽ 8Q – 400፣ ቦይንግ 757 እና 767 ይገኙበታል፡፡   
እኔ በኢትዮጵያ የመጀመርያዋ ሴት አብራሪ አይደለሁም፡፡ የመጀመርያዋ አብራሪ (1925) ሙሉ እመቤት እምሩ ሲሆኑ እሳቸውን ተከትለውም በ1950ዎቹ ዓመታት አሰገደች አባተ ሁለተኛዋ ሴት አብራሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከዚያም ሌሎች ሦስት ሴቶች አብራሪ ከሆኑ በኋላ ነው እኔ ስድስተኛዋ አብራሪ የሆንኩት፡፡ ነገር ግን ለካፒቴንነት ማዕረግ የሚያበቃውን ሙሉ ሥልጠናና መመዘኛ ወስዶ በማጠናቀቅ፣ የመጀመርያዋ ሴት ካፒቴን መሆን ሳይሆን አሰልቺውንና እልህ አስጨራሹን የሥልጠናና የግምገማ ሂደት በስኬት ተወጥቼ፣ የሙያዬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ መቻሌ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ስኬታማ ለመሆን ያገዘኝ፣ በራሴ ላይ ያለኝ እምነትና ተስፋ አለመቁረጤ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በጣት የሚቆጠሩ ሴት አብራሪዎች ለመኖራቸው በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል:: በመጀመርያ ደረጃ፣ አብዛኛው ሰው አብራሪነትን እንደ ወንድ ሥራ አድርጎ መቁጠሩ፣ ሌላው ደግሞ ለአብራሪነት የሚጠየቀው የቁመት መስፈርት 1.7 ሜትር ሲሆን ብዙዎቹ እህቶቻችን ደግሞ ያን ያህል ረዥም አለመሆናቸው ይመስለኛል፡፡ ፆታዬ ምንም ዓይነት አሉታዊ አስተያየቶች ቢደርሱብኝም በጄ ብየ ስለማልቀበልና እንደ ቁም ነገር ስለማልቆጥራቸው አስጨንቀውኝ አያውቁም፡፡ ሕብረተሰብ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር አይለወጥም፤ ነገር ግን የራስን አመለካከትና የአስተሳሰብ ዘይቤ መለወጥ ይቻላል፡፡ እናም በጥንካሬና በትጋት በመበርታት ህልምን ከግብ ማድረስ ይቻላል፡፡ ፈተና በገጠመኝ ጊዜ ከፆታዬ ጋር አላገናኘውም፡፡ ይልቁንም በሙያና በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙና መታለፍ ያለባቸው ፈተናዎች እንደሆኑ አድርጌ ነው የማስባቸው፡፡
ትልቁ ፈተናዬ የነበረው ልጆቼን ማሳደግ ነው፡፡ ሙያው በአጠቃላይ መፈናፈኛ የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው ከቤተሰቦቼ እንድለይ ያስገድደኛል:: አንዳንዴ ከቤት ውጭ አንድ ሳምንት የማሳልፍበት ጊዜ አለ፡፡ ነገር ግን ጥሎ አይጥልም እንዲሉ ጠንካራ ድጋፍ የሚያደርግልኝ ባለቤት ሰጥቶኛል፡፡ በአየር መንገዱ ደንብ መሠረት፣ ሴት ነፍሰጡር ስትሆን በረራ እንድታቆም ትገደዳለች፡። እኔም በእርግዝናዬ ወቅት የጀማሪ አብራሪዎች መምህር በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ ታዲያ ከረዥም እረፍት በኋላ ወደ በረራ ሥራ ስመለስ ብቃቴን ማደስና አውሮፕላን በሚመስለው የመለማመጃ ጣቢያ (ሲሙሌተር) ላይ እንደገና መሰልጠን ይጠበቅብኛል፡፡
አሁን የልጅነት ህልሜን ማሳካት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደፊት በሞያዬ ቦይንግ 777 እና 787 የመሳሰሉትን ትላልቅ አውሮፕላኖች በካፒቴንነት ለማብረር እሻለሁ፤ በቤተሰባዊ ህይወቴ ደግሞ፣ ልጆቼ አድገውና ስኬታማ ሆነው ለማየት እመኛለሁ:: በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሕይወት ታሪኬን፣ ተሞክሮዬንና ስኬቴን በማጋራት፣ ለማህበረሰቡ የድርሻዬን አስተዋፅኦ ለማበርከት እሞክራለሁ:: እንደ አንድ ውጤታማ፣ ብቁና ለሌሎች አቅም የምትሆን ሴት፣ አዲሱን ትውልድ በተለይ ደግሞ ልጃገረዶችን ለማበረታታት፣ እንዲሁም ጥሩ አርአያ ለመሆን እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መንፈስ አነቃቂ ተናጋሪ ለመሆንም እሻለሁ፡፡ እነዚህን መከወን ለእኔ ትልቅ የመንፈስ እርካታ ያጎናጽፈኛል፡፡
ህልሜ በአገሬ ህዝቦች መካከል ህብር ተፈጥሮ ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በልዩ የበለጸገ ታሪኳ፣ ባህሏና ቅርሷ እንድትታወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወንዶቹም ሴቶቹም ያለሙትን ለማሳካት እኩል መብትና እድል አግኝተው ማየትም እሻለሁ፡፡ ሴቶች የተሻለ እድል፣ የተሻለ ሕይወትና የተሻለ ገቢ አግኝተው እንዲሁም ከጥገኝነት ተላቀው እንደማይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በዛሬ ዘመን  በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያድጉ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች የምለግሳቸው ምክር እንዲህ የሚል ነው፡፡ ፍላጎታችሁን በቅጡ ለይታችሁ በማወቅ ተግታችሁ ሥሩ፤ በልጅነት እድሜያችሁ ትምህርትን የሙጠኝ ብላችሁ እስከመጨረሻው በትኩረት ግፉበት፤ የምትወዱት ሥራ ላይ  አተኩራችሁ፣ ሁለመናችሁን በመስጠትና በቁርጠኝነት ተግታችሁ ሥሩ፤ በምንም ነገር ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ፤ እናንተም ወንዶች የገነኑበት ሙያ ውስጥ ገብታችሁ ልትገኑበት እንደምትችሉ አትጠራጠሩ፡፡ አውሮፕላን አብራሪነትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትርነትም ቢሆን፤ የማይቻል ነገር የለምና፡፡
ምንጭ (ተምሳሌት ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ 2007

Read 1221 times