Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Print this page
Monday, 15 July 2019 09:33

ዶ/ር ዐቢይ “ሕዝበኛ” መሪ ናቸውን?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)


               ሐሳብ ማስገሪያ
ሕዝበኝነት (Poplulism) ለሰፊው ሕዝብ ፋይዳ ያለው ፣ሥርነቀል ለውጥ በማምጣት፣ ዘላቂ ዴሞክራሲዊ ሥርዓትን በመገንባት ፈንታ፣ ለሕዝብ ስሜት ቅርብ የሆኑ ሰሞነኛ አጀንዳዎችን በማቀንቀን ለፖለቲካ ትርፍ መታተር ነው፡፡ በዚህ የፖለቲካ ስልት ሥልጡን የሆኑ መሪዎች፤ የሰፊውን ሕዝብ ስሜት በሚያጎሹ ተቀናቃኞች ላይ የማጥቃት ዘመቻ በመክፈት፤ የሚገዙትን ማህበረሰብ ቅቡልነት ለማግኘት ላይ ታች ይላሉ፡፡ ይኼ የፖለቲካ ዘይቤ፣ በባሕሪው ከፋፋይና ብዝኃነትን የማይቀበል ነው፡፡
በዚህ መሰሉ የፖለቲካ ጨዋታ ከተካኑ መሪዎች መካከል የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ፣የቱርኩ ኤርዶጋንና የሩሲያው ፑቲን ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ መሪዎች ግለሰባዊ ምስላቸውን /personal cult/ ለመገንባት የሄዱበት ርቀት ከግምት በላይ ነው፡፡ አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ተቋማዊ ዋስትና ያለውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገዝገዝ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ስቴቨን ሌቪትስካይና ዳኒኤል ዚብላት “How democracy dies” በሚለው ድርሳናቸው፣ሕዝበኛ ፖለቲከኞች ምን ያህል ለዴሞክራሲ ጣውንት እንደሆኑ ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል፡-
“Blatant dictatorship - in the form of fascism, communism, or military rule - has disappeared across much of the world. Military coups and other violent seizures of power are rare. Most countries hold regular elections. Democracies still die, but by different means.”
ግርድፍ ትርጉሙ፤ በአለማችን በአሁን ሰዓት እንደ ፋሺሲዝም፣ኮሚኒዝም ወይም ወታደራዊ አገዛዝ አይነት አይን ያወጣ አምባገነንነት የለም፡፡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትና በአመጻ ሥልጣን በአቋራጭ የሚያዝበት መንገድ በሩ ተዘግቷል፡፡ አብዛኞቹ አገራት ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ያካሂዳሉ፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲ እየሞተ ይገኛል፤ግን በተለየ መንገድ፡፡   
እንደ ተንታኞቹ አባባል፤የዘመናችን የዴሞክራሲ ሥጋት የሚከተለው ዘይቤ፣ ከወትሮው ረቂቅ የሆነ ሥልትን ነው፡፡
ዐቢይ አሕመድ “ሕዝበኛ” ናቸውን?
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በሕዝበኝነት የሚተቹ ሂስ አቅራቢዎች፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ተቀባይነታቸው የላቀ እንዲሆን፤የታይታ ሥራዎች ላይ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፡፡ የፓርቲውን የሥልጣን መዋቅር በመጠቀም፣ ትልልቅ ሰልፎች በከተሞች እንዲካሄዱ ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኗቸውን በማሳረፍ፣ ገጽታቸውን ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል::” ይላሉ፡፡  
በሌላ በኩል፤ ጠ/ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ዓይነት የሴራ ፖለቲካ ጋር ፈጽሞ እንደማይተዋወቁ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እያጣቀሱ የሚሞግቱ ተንታኞችም አሉ፡፡ ታዋቂው የ”ጋርዲያን” ጋዜጠኛ ቶም ጋርድነር፤ ዶ/ር ዐቢይ ህዝበኛ ናቸው የሚለውን ክስ አይቀበልም፡፡ ከወራት በፊት፣ በታዋቂው የፎርየን  ፖሊስ ድረ-ገጽ ላይ ባቀረበው ሐተታ፤ ዶ/ር ዐቢይ ለሊብራል ዴሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመጥቀስ፣ ከሕዝበኛ የፖለቲከ ዘይቤ ጋር ኩታገጠም እንዳልሆኑ አስረጂዎቹን አቅርቧል፡፡
“Abiy doesn’t talk like a populist. His addresses aren’t fiery blasts of political invective; they are more like sermons, befitting his background as a devout pentecostal. His policies don’t pander to voters by offering quick fixes to complex problems. Populists, whether on the left or the right, typically offer fanciful and simple solutions such as build a wall, land expropriation, and drowining the rich in taxes.”
“በቅድሚያ ከዐቢይ አሕመድ አንደበት የሚፈልቀው መልእክት ከሕዝበኛ መሪ/Populist/ ጋር ሊያጎዳኛቸው የሚችል አይደለም፡፡ ንግግራቸው ለሴራ ትንተና የማይመች፤ ከመንፈሳዊ ስብከት ጋር የሚመሳሰል ቁምነገር ይበዛዋል:: ዐቢይ፤ የመራጮቻቸውን ይሁንታ ለማግኘት፣ ለውስብስብ ችግሮች ቅጽበታዊ መፍትሄዎችን ለመስጠት አይከጅሉም፡፡ እንደ ዶናልድ ትራምፕ፣ ግንብ የመገንባት ፕሮጀክት፤ ወይም እንደ ቀድሞው የዚምባቡዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ፣ መሬት ከነጭ ገበሬዎች ነጥቆ ለጥቁር አርሶ አደሮች የማከፋፈል ፖሊሲ ዓይነት፣ ሰሞነኛ ውሳኔን በማሳለፍ ለፖለቲካ ትርፍ ላይ ታች አይሉም፡፡”
በእርግጥ ጋርድነር ያቀረበው አመክንዮ በከፊል ሚዛን የሚደፋ ቢመስልም፤ በሌላ አቅጣጫ ጉዳዩን ይበልጥ ከመረመርነው፣ድምዳሜያችን ከጋዜጠኛው ሃሳብ ጋር ላይጣጣም  ይችላል፡፡
መሬት ላይ ያለው ከፊል እውነታ
ቶም ጋርድነር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሴራ ይልቅ ለቀናኢ ዓላማ የሚቀርበውን የፖለቲካ ዲስኩሮቻቸውን እንደ ዋቢ በመውሰድ፣ከሕዝበኝነት ጎራ እንደማይመደቡ አጽዕኖት ሰጥቶ እንዳብራራ ቀደም ባሉት አንቀጾች ላይ ተመልከተናል፡፡ ይሄ ግን ቀናት በገፉ ቁጥር መልኩን እየቀየረ እንደመጣ  መታዘብ ችለናል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፣ በሥልጣናቸው አፍላ ወቅት ከአንደበታቸው የሚፈልቀው ለሴራ ትንተና የማይመች፤ ሁሉን አካታች የሆነ የመደመር ጥሪን ያዘለ ነበር፡፡ ወራት፣ ወራትን እየወለደ ሲሄድ ግን ዲስኩሮቻቸው ቀስ በቀስ የሕዝበኝነት መንፈስ እየተጫነው ለመምጣቱ አንዳንድ ዳናዎችን ማስተዋል ጀምረናል፡፡ የንግግሮቻቸው አንደምታ ከወትሮው ለየት ያለ እንደሆነ እየተመለከትን ነው:: ይሄ ምናልባትም ጫፍና ጫፍ የረገጡ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ በአዲሱ አስተዳደር ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመመከት የተቀየሰ ፖለቲካዊ ስሌት ሊሆን ይችላል፡፡ በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር ላጣቅስ፡-
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ27 ዓመታት በአምባገነናዊ አገዛዝ እንዲዳክር ምክንያት የሆነውን ሕገ መንግሥት፤ “በደምና አጥንት” የተተከለ ሰነድ እንደሆነ ኮስተር ብለው መናገራቸው የሚታወስ ነው:: እንዲህ አይነት ዲስኩር ምናልባትም ያስደስታል ከተባለ፣ ከየትኛውም ኃይል በላይ የሚያስደስተው የሕገ መንግሥቱ ዋስ ጠበቃ እንደሆነ የሚናገረውን ሕወሓትንና መሰል ቡድኖችን ነው፡፡ የንግግራቸውን ፍሬ ሐሳብ መነሻ በማድረግ፤ “ዶ/ር ዐቢይ ካኮረፉ ኃይሎች ጋር አዲስ የግንኙነት ማእቀፍ ለመፍጠር አቅደዋል” የሚል ሌላ የሴራ ትንታኔን በር ሊከፍት ችሏል፡፡
ቶም ጋርድነር እንደሚለው፤ ሕዝበኛ መሪዎች፣ በአብዛኛው ውስብስብ ችግሮችን በሸንጋይና የአጭር ጊዜ መፍትሄ ነው ለማለፍ የሚሞክሩት፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ፖለቲካዊ አካሄድ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደማይከተሉ ይሞግታል፡፡ ከቶም ሐሳብ ጋር የማይጣጣም የመሰለኝን አንድ ኹነት ላቅርብ፡፡
ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጣልቃ ገብነት፣ በክልሎች መካከል የተፈጠረውን ወሰን ተከትሎ የተከሰቱትን ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎች ለመፍታት በሚል እሳቤ፤ የማንነትና ወሰን ኮሚሽን በአዋጅ እንዲቋቋም መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኽ ምናልባት ችግሩ ያለባቸውን የክልል ሕዝቦች ለጊዜው ለማለዘብ ይጠቅም ይሆናል እንጂ፣ በፖለቲካ ውሳኔ የተተከለውን ሥርዓት በእንዲህ መልኩ ለመፍታት ማሰብ ተምኔታዊ ነው፡፡ ስለዚህ የኮሚሽኑ መቋቋም ሥር-ነቀል ለውጥ ወይም ዘላቂ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ፤ ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ሊሆን ይችላል:: ይኽንን ዓይነት ስልት ታሳቢ ተደርጎ የሚወሰድ ፖለቲካዊ እርምጃ ደግሞ ከሕዝበኝነት ባህል ጋር የሚዛመድ ነው፡፡
ሌላው ከፊል እውነታ
የዶ/ር ዐቢይን የፖለቲካ ሰብእና በሁለት እርከን ከፋፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ወራት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ከገባበት የፖለቲካ ቆፈን እንዲወጣ ስሜት ቀስቃሽ ዲስኩሮችን ያበዙ እንደነበር ይታወቃል:: ከዚህ ጎን ለጎን ያለፈው ሥርዓት የተዋቸውን ሽንቁሮች ለመድፈን የሄዱበት ርቀት ከተገመተው በላይ እንደሆነ የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን ነጻ በመልቀቅ፣ ቀያጅ ሕጎችን በማሻሻልና ከሀገር ውጪ የነበሩትን የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላም እንዲታገሉ ምህዳሩን በመክፈት አስደማሚ የለውጥ እርምጃን ወስደዋል:: ምናልባትም እነዚህ እርምጃዎች፣ ከሕዝበኛ መሪ ይልቅ ከእውነተኛ የሀገር ተቆርቋሪ መሪ የሚመነጩ የፖለቲካ ውሳኔዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ሌላው ጠ/ሚኒስትሩን በሕዝበኝነት እንዳንጠረጥራቸው ከሚያደርጉን እውነታዎች መካከል፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወሳኝ ጡብ በሆኑት የተቋማት ግንባታ ላይ ያሳዩት  ቁርጠኝነት ነው፡፡ ለአብነት ያህል፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን፣ በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ያልነበረውን የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ለማጠናከር፣ ብርቱዋን ፖለቲከኛ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳን ወደ አመራር ማምጣታቸው ከየአቅጣጫው አድናቆት አትርፎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  የፖለቲካ ልዩነት ያላቸውን ግለሰቦች እንደ ማጥቂያ ያገለግል የነበረውን የሕግ ሥርዓት ለማሻሻል፣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸው፣ ጠ/ሚኒስትሩ ለለውጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከሰሞኑ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር  ሆነው የተሾሙት  የመብት ተሟጋቹ ዶ/ር ዳንኤል በቀለም ሌላው ማሳያ ናቸው፡፡  
ባጠቃላይ ዐቢይ አሕመድ ከሕዝበኝነት የፖለቲካ ባህል ጋር እንደማይተዋወቁ እማኝ የሚሆኑን ተጨባጭ ማሳያዎችን መጥቀስ ብንችልም፤አፋችንን ሞልተን እንዳንደመድም ከሚያቅቡን ነባራዊ እውነታዎች ጋር መላተማችን ግን አይቀርም፡፡
ሕዳግ
ሀገራችን ልክ ከዚህ ቀደም በታሪክ ፊት እንደተከሰቱት መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ፤ ወሳኝ ኩርባ /critical juncture/ ላይ ነው ያለችው፡፡ በዚህ ትኩረት የሚሻ የታሪክ አጋጣሚ ላይ የመሪያችን የፖለቲካ ሰብእና እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከሕዝበኝነት /የታይታ ግብር/ የራቀ፣ሀገራችንን ከገባችበት ቅርቃር መንቅሎ የሚያወጣ፤ ብርቱ ተክለሰውነትን የተላበሰ የሀገር መሪን የምንሻበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ስለዚህም ከጠ/ሚኒስትራችን የምንጠብቀው አበርክቶት እጅግ የገዘፈ ነው፡፡

Read 1452 times Last modified on Monday, 15 July 2019 10:05