Monday, 15 July 2019 09:55

ያስገረመኝን ታሪክ ልንገራችሁ!

Written by  ጌታቸው ተድላ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

      “…የማንም ሐይማኖት ተከታይ አይደለሁም፤ የኔ ሐይማኖት የሁሉንም እኩልነት መጠበቅና ዘረኝነትን ማጥፋት ነው…”
                             
             ባለፈው ወር ለአንድ የግል ጉዳይ ወደ ሰሜኑ ዋልታ አገር ስዊድን ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ማታ ላይ በቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ አንዲት ጥቁር ሴት፣ ከአንድ ከታወቀ የሊበራል ፓርቲ ፖለቲከኛና መሪ ጋር ስትከራከር፣ ለጋዜጠኞች ጥያቄ መልስ ስትሰጥ ተመለከትኩ፡፡ “እዚህ ደረጃ የደረሰች ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ማነች?” ብዬ ስጠይቅ፤ “ከሦስት ሳምንት በኋላ በሚደረገው የሊበራል ፓርቲ መሪ ምርጫ ላይ የምትሳተፍ ሴት ነች” ተባልኩ፡፡ “ምን? ጥቁር አፍሪካዊት የአንድ ፓርቲ መሪ ለመሆን?! ያውም ስዊድን አገር!?” እያልኩ ትንሽ ከራሴ ጋር ተሟገትኩ፡፡        
 ይህች ሴት የትውልድ ሀገሯ ብሩንዲ ነው፡፡ ብሩንዲ በታንዛንያ፣ በኮንጎና በሩዋንዳ የተከበበች ትንሽዬ አገር ናት፡፡ ነፃነቷን እ..ኤ.አ በ1962 ከመጎናጸፏ በፊት ርዋንዳ - ኡሩንዲ ትባል ነበር፡፡ የአገሪቷ ስፋት 27 ሺ 834 ስኩዌር ኪ.ሜ ነው (የኛ ሀገር ስፋት 1.104 ሚሊዮን ስኩዌር ኪ.ሜ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በሀገሪቷ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ይኖሩባታል፡፡ የብሩንዲ መዲና ቡጁምቡራ ቢሆንም በቅርቡ ወደ ጂቴጋ ተዛውሯል፡፡ አገሪቷ በወረቀት፣ በቆዳና በእርሻ ምርት ትታወቃለች፡፡  
ይህች የቡሩንዲ ተወላጅ ኛምኮ አና ሳቡኒ ትባላለች፡፡ የ50 ዓመት እመቤት ናት፡፡ የተወለደችው በቡጁምብራ ከተማ ነው፡፡ አባቷ የክርስትና ሐይማኖት ተከታይ ሲሆኑ የዛየር (በኋላ ኮንጎ) ተወላጅ ናቸው፡፡ ግራ ዘመም ከመሆናቸውም ባሻገር ንቁ የፓትሪስ ሉሙምባ የፖለቲካ ደጋፊ ስለነበሩ፣ ብዙ ጊዜ ታስረዋል፡፡ የሙስሊም ሐይማኖት ተከታይ የሆኑት እናቷ፤ ሳቡኒን በሙስሊም ባሕል መሠረት ነው ያሳደጓት፡፡ ስለዚህም ሳቡኒ፤ ከክርስቲያንና ከሙስሊም አማኝ ወላጆች የተወለደች ናት፡፡ እሷ ግን ስለ ሐይማኖት ግድ የላትም፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በአደባባይ፤ “…እኔ የማንም ሐይማኖት ተከታይ አይደለሁም፤ የኔ ሐይማኖት የሁሉንም እኩልነት መጠበቅና ዘረኝነትን ማጥፋት ነው……” ብላለች፡፡  
አባቷ በግራ ዘመም የፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በአገራቸው ኮንጎ መኖር ባለመቻላቸው፣ ወደ ሩዋንዳ፣ ከዚያም ወደ ታንዛንያ ተሰደዱ:: እዚያም እያሉ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ስለተደረገባቸው፣ የስዊድን መንግሥት ጥገኝነት ሰጥቷቸው ስዊድን ገቡ፡፡ ሳቡኒ አገረ ስዊድንን ስትረግጥ ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡
የስዊድንን ቋንቋ ተምራ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በማጠናቀቅ፣ በታዋቂው የኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ተመረቀች፡፡ ወጣቷ ሳቡኒ ኪስዋሂሊ፣ እንግሊዝኛና ስዊድንኛ አቀላጥፋ ትናገራለች፡፡ ባቋቋመችው የአፍሮ-ስዊዲሽ ማኅበር ውስጥ የፕሮጀክቱ ሃላፊ በመሆን የሰራችው ሳቡኒ፤ የስደተኞችን ችግር ለመፍታት ጥረት አድርጋለች:: በተለያዩ መሥሪያ ቤቶችም ተቀጥራ ሰርታለች:: በ2004 ዓ.ም ባል አግብታ፣ ሁለት መንታ ወንድ ልጆችን ወለደች፡፡
በስዊድን የወጣቶች ሊበራል ፓርቲ ውስጥ ገብታ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የቦርዱ አባል በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግላለች - ከ1996-1998፡፡ ከዚያም የፎልኬት ፓርቲ (የሕዝብ ፖለቲካ ቡድን) አባል ሆና፣ በምርጫ ተወዳድራ በማሸነፍ፣ ፓርላማ ገባች፡፡ የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም፣ በ2002 ዓ.ም የኢንተግሬሽንና ጄንደር ኢኳሊቲ (Minister for Integration and Gender Equality) ሚኒስትር አድርጎ ሾማት፡፡ በዚህም በስዊድን ታሪክ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሚኒስትር ሆነች፡፡ ሳቡኒ እስከ 2013 ድረስ ለ11 ዓመታት በሚኒስትርነት አገልግላ ከመንግሥት ሥራ በፈቃድዋ ለቀቀች፤ከውጭ ሆኜ ፓርቲዬን የበለጠ ላጠናክረው በሚል፡፡  
በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር በምታደርግበት ወቅት ሕዝቡ እያጨበጨበ ድጋፉን ይሰጣታል:: ጥቁር ብትሆንም ቅሉ፣ ዘረኛ ነች እያሉ የሚቃወሟትም አሉ፡፡ እኔ በአንድ መድረክ ከተናገረችው ውስጥ ስሜቴን የነካው፤ “ብዙ ስደተኞች መብታቸውን በስህተት ይረዱታል፤ የሐይማኖት ነፃነት ማለት፣ ምንም ነገር በሐይማኖት ሳቢያ መፈጸም ይመስላቸዋል..እዚህ ስዊድን ቤት ሠርታችሁ፣
ልጆች ወልዳችሁ፣ የልጅ ልጆች አይታችሁ ህይወታችሁን ስትመሩ፣ ከሕብረተሰቡና ባህሉ ጋር መዋሃድና መስማማት ግዴታችሁ ነው” ያለችው ነው፡፡
ስዊድን እያለሁ ላገኛትና የበለጠ እሷን ለማወቅ ፈልጌ ወደ ቢሮዋ ደወልኩኝ፡፡ ነገር ግን  በፓርቲው ምርጫ ተወጥራ ስለነበር ከምርጫው በኋላ ሊያገናኙኝ እንደሚችሉ የቢሮዋ ሰዎች ነገሩኝ፡፡ እኔ ግን የመመለሻዬን ቲኬት ለማራዘም ስላልፈለግሁ፣ ሳላገኛት ተመለስኩ፡፡ ወደ አገሬ ለመመለስ አንድ ቀን ሲቀረኝ፣ ወይዘሮ ሳቡኒ፣ የሊብራል ፓርቲ መሪነቱን አሸንፋ መመረጧን በሁሉም ጋዜጦችና በቲቪ ለማየት በቃሁ፡፡ እናም በእጅጉ ተገረምኩ፡፡
“ይሄ ምን ያስገርማል? ደስ ይላል እንጂ” ትሉ ይሆናል፡፡ እኔን ያስገረመኝ ሁኔታውን ከአገሬ ጋር  እያወዳደርኩት ነው፡፡ እስቲ አስቡት! ይህች ሴት እኛ አገር ብትሆን፣ አሁን ያለችበት ደረጃ ትደርስ ነበር? “የኛ አገር ሰው አይደለሽም፤ አገርሽ ሌላ ነው፤ እዛው ብሩንዲሽ ተመለሺ!” ተብላ አትፈናቀልም? ሳቡኒ ቆዳዋ ጥቁር ነው፡፡ ዐይኗ፣ ፀጉሯ፣ ከንፈሯ፣ ባጭሩ ሁለመናዋ በፍፁም ከነጮቹ ጋር አይመሳሰልም:: የነጮቹ መልክም ሆነ ባህሪ የላትም፡፡ እዚያም አልተወለደችም፡፡ በስደትና በጥገኝነት በ12 ዓመቷ የመጣች ሰው ናት፡፡ ነገር ግን እዚያ አድጋ፣ እዚያ ተምራ፣ የሕብረተሰቡን ኑሮና ባህል ተለማምዳ፣ ሳትሳቀቅ ኮርታ፣ “አገሬ ስዊድን ነች” ብላ የምትኖር እመቤት ነች፡፡ በነገራችን ላይ ስዊድን ሰዎች ሁሉ በዴሞክራሲና በእኩልነት አንድ ላይ የሚኖሩባት ነጻ  አገር ነች፡፡
እዚህ ኢትዮጵያ ቢሆንስ? እንኳን የውጭ ሰው የአገሩ ተወላጅ ከትውልድ ቀዬው ውጭ በነጻነት መኖር እንደማይችል እያየን ነው፡፡ “አንተ’ኮ ብሔርህ አማራ ነው፣ አንቺ’ኮ ኦሮሞ ነሽ፣ አንተ’ኮ ብሔርህ ጉራጌ ነው፣……. አንተ መጤ ነህ፣ ወደ ክልልህ ሒድ!” እየተባለ ስንቱ ተፈናቅሏል? ስንቱስ ተበትኗል? ለዚህ ነው በስዊድን የምትኖረው ጥቁር አፍሪካዊቷ ሳቡኒ፣ የሊበራል ፓርቲ መሪ ሆና መመረጧ ያስገረመኝ:: እኛ አገር እኮ አንድ ሰው ከክልሉ ውጭ በምርጫ መወዳደር አይችልም፡፡ አሁንማ መኖርም ጭምር ፈተና ሆኗል፡፡  
ለማንኛውም ሠላም በአገራችን ይስፈን፤ የጥንቱ፣ የጧቱ በጋራ የመኖር ባህላችን፣ ፍቅራችንና ትብብራችን ይመለስ፡፡ ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ ለዘላለም ትኑር!

Read 1384 times