Monday, 15 July 2019 10:44

የሜቄዶኒያው መስራች ቢኒያም በለጠ በአሜሪካ እውቅና አገኘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)


         መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ከአመታት በፊት መስርቶ እስካሁን ከ2ሺህ በላይ ለሆኑ ራሳቸውን ችለው መመገብ፣ መፀዳዳትና መንቀሳቀስ የማይችሉ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ከየጐዳናው በማንሳት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው አቶ ቢኒያም በለጠ፤ እያደረገ ላለው ትልቅ ሰብአዊ ድጋፍና ላከናወነው በጐ ተግባር ከአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት ሴኔትና ከዋይት ሃውስ እውቅና ማግኘቱ ተገለፀ፡፡
አቶ ቢኒያም ኮተቤ አካባቢ የሚገኘውን የወላጆቹን መኖሪያ ግቢ ለአረጋዊያንና ለአዕምሮ ህሙማን መርጃነት በማመቻቸት፣ ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሚያገኘው ድጋፍ፣ አረጋዊያንና ህሙማኑ የተሟላ ምግብ፣ ልብስ፣ ህክምናና ቤተሰባዊ ፍቅር እንዲያገኙ በማድረግ ለሚያከናውነው በጐ ፈቃድ ተግባር ነው እውቅና ያገኘው፡፡
ማዕከሉ እያደረገ ያለውን በጐ ተግባር የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ አገልግሎቱን እንዲያሰፋና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር እንዲያሳድግ 30ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በነፃ የሰጠው ሲሆን፤ በዚህ ቦታው ላይ 11 ፎቆች ያሉት ህንፃ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የህንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ የተረጂዎቹን ቁጥር ወደ 10ሺህ ከፍ ለማድረግ መታቀዱም ታውቋል፡፡ የህንፃው ግንባታ 1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ይህን በጐ ተግባር በመደገፍ በውጭ የሚገኙ በጐ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ በዴንቨር ከተማ ባዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ አቶ ቢኒያም እውቅና ማግኘቱም ተገልጿል፡፡

Read 11045 times