Tuesday, 16 July 2019 10:16

የማዕረግ ተመራቂዎች - ከጅማ ዩኒቨርሲቲ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)


         አንጋፋው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ በሁለት ዙሮች በድህረና ቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር (ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም) 3301 ተማሪዎችን፣ በሁለተኛው ዙር (ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም) ደግሞ 2376 በድምሩ 5ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎችን አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 28 የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ሲሆኑ አብዛኞቹ በከፍተኛ ማዕረግ ነው የተመረቁት፡፡ በሁለተኛው ዙር ምረቃ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ አምስት ተማሪዎችን በትምህርት ቆይታቸው፣ በገጠሟቸው ፈተናዎች እና በወደፊት ዕቅዶቻቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡


                  በባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ 3.4 ነጥብ ተመራቂ

          ደራርቱ ደረጀ እባላለሁ፤ የመጣሁት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ መተከል አካባቢ ወንበራ ከሚባል ቦታ ነው፡፡ ለቤተሰቦቼ ሶስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ እየወጣሁ ነው ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት፡። በተለይ ሁለተኛ ደረጃ  እያለሁ ሁሌም አንደኛ እየወጣሁ ነው ዩኒቨርሲቲ የገባሁት:: ዛሬም እንደምታይኝ የባዮ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቴን በብቃት አጠናቅቄ ተሸልሜአለሁ። 3.4 ነው ያመጣሁት፡፡
ጅማ ለመምጣት ሶስት ቀን ነው የተጓዝኩት፡፡ ወደ ቤተሰቤም ለመሄድ ሶስት ቀን ነው የሚፈጀው፡፡ ይህንን ሁሉ ተጉዤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት ዓላማ ስላለኝ ነው፡፡ ዓላማ ያለው ሰው የመንገድ ለርቀትና ሌሎች ፈተናዎች አያግዱትም፡፡ ከጀርባችን ቤተሰብ አለ፤ ትልልቅ ሰዎች አሉ፣ አገራችን አለ፣ ሕዝባችንም አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከኔ የሚጠብቁት ነገር አለ፡፡ እነሱ የሚጠብቁብኝን ነገር እንዲያገኙ ለዓላማዬ መበርታት ነበረብኝ፡፡ አሁን ያሳካሁ ይመስለኛል፡፡
ወደማያውቁት አካባቢ መምጣት፣ ሴትነት፣ በዚያ ላይ ወጣትነት ፈተናዎች መሆናቸው አይካድም፤ ግን እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ዓላማ ያሸንፋቸዋል አሸንፏቸዋልም፡፡ እኔም በግሌ ትልቅ ቦታ ደርሼ ማየት ህልሜ ስለነበር ፈተናዎች ሳያሸንፉኝ ለምርቃት በቅቻለሁ፡፡
ለኔና ለጓደኞቼ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ትምህርት ዕድል ሰጥቶናል፤ ትምህርታችንን እንቀጥላለን፡፡ ያው ከትምህርት ወደ ትምህርት ማለት ነው፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ በዘርፋችን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ጥናትና ምርምር በማድረግ ለማህበረሰቡ በሚጠቅም መልኩ እንሰራለን ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም ፈጣሪዬን፣ ቤተሰቦቼን፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲን፣ መምህራንንና አማካሪዎቼን አመሰግናለሁ።


___________________________


                 ‹‹በብዙ ፈተና ውስጥ አልፌ ለዚህ ማዕረግ በቅቻለሁ››


           ሁሴን እንዳለ ሀይሌ እባላለሁ፡። ትውልድና እድገቴ ሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ፣ ነው፡፡ አበራ ዶኮ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እንደምታይኝ አካል ጉዳተኛ ነኝ፡፡ ይህ ችግር ያጋጠመኝ የ6 ወር ሕጻን እያለሁ ነው?; ወንድሜ በዝናብ ተሸክሞኝ ሲሮጥ ጭቃ አንሸራትቶ ሁለታችንም ድንጋይ ላይ ወደቅን። እናቴ እንደነገረችኝ፤ ወንድሜ ፈርቶ ወዲያውኑ መውደቃችንን አልተናገረም፡፡ እንደውም ጭቃ በጭቃ ስሆን ጥሎኝ ነው የጠፋው፡፡ በኋላ ጎረቤቶች እናቴ እንዳትደነግጥ አጣጥበው ነው የሰጧት፡፡ እየቆየሁ ስሄድ መዳህም አልቻልኩም፡፡ ቤተሰቦቼ ግራ ሲገባቸው ወጌሻ ጋር የወሰዱኝ፡፡ ‹‹ይሄ ክፉ መንፈስ ነው፤ ምንም ሌላ ነገር የለውም›› ተባለ ሆኖም መቆም አቃተኝ፡፡ መውደቄ የታወቀው ችግሩ መመለስ የማይቻልበት ደረጃ ከደረሰ በኋላ ነው:: በወቅቱ ቢደረስበት ኖሮ በዱላ ቆሜ የመሄድ እድል ይኖረኝ ነበር፡፡ ነፍስ ካወቅኩ በኋላ ለሌላ ምርመራ ሃኪም ጋ ስሄድ፣ በልጅነቴ ከፍተኛ ስብራት ወገቤ ላይ እንደደረሰብኝና አሁን ምንም ማድረግ እንደማይቻል ነግረውኛል፡። እርግጥ ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ ‹‹ኔዘርላንድ ወስደን እናሳክምህ›› ያሉኝ ነጮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ ማንም የሚያማክረኝ ስላልነበረ ፈርቼ ተውኩት፡፡ የመገለል ጉዳይ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ለአባቴ የመጨረሻ ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ከእናቴ እኔን ብቻ ነበር የወለደው፡፡ አባቴ  ሲሞት አካል ጉዳተኛ ነው የሚደግፈው የለም›› ብሎ አብዛኛውን ንብረቱን ለኔ ነበር አውርሶ የሞተው፡፡ ‹‹እንዴት በቅርብ የተወለደ ልጅ ይወርሳል›› ብለው የአባቴ ልጆች፣ ወንድሞቼ በኔ ላይ ክፉ አስበው ሲጣሉኝ፣ ከሚገድሉኝ ብዬ ጠፍቼ ሌላ ቦታ ሄድኩኝ፡፡ ምንም ንብረት ሳልይዝ ማለት ነው፡፡ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ባዕድ ነው ያስተማረኝ፡፡
እዚያው ሲዳማ ውስጥ ቀባዶ ት/ቤት 12ኛ ክፍልን ከጨረስኩ በኋላ ሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመንግሥት ድጋፍ ተምሬ በዲፕሎማ ተመረቅሁ:: ለአራት ዓመታትም ተፈሪ ኬላ ጤና ጣቢያ ላይ አገልግያለሁ፡፡
በማታው የትምህርት ክፍል 6 ዓመት ተምሬ በፋርማሲ ነው የተመረቅኩት፡። እንደሰማሽው ውጤቴ 3.83 በከፍተኛ ማዕረግ ነው የተመረቅኩት:: ስማር ከምሰራበት ደሞዝ እየተከፈለኝ ነው:: በማታው የትምህርት መርሃ ግብር ስትማሪ ክፍያ አለው፡፡ የአዕምሮ ብርታቴን የተመለከተው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግን ከአካል ጉዳተኛ ማህበር ያመጣሁትን ደብዳቤ ተቀብሎ፣ ከክፍያ ነጻ አድርጎ አስተምሮኛል:: እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ እኔም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲውን አኩርቻለሁ፡፡
የአጠናን ሁኔታን በተመለከተ ከተማሪዎች ጋር ነው የምናጠናው፤ የማውቀውን አካፍላቸዋለሁ፡፡ የማላውቀውን ከእነሱ አገኛለሁ፡፡ ተማሪዎች ለእኔ ልዩ አክብሮትና እንክብካቤ ነበራቸው ይገርምሻል፣ ራሱ እየተላቀስን ነው የተለያየነው፡፡ በቆይታዬ ምቹ ሁኔታን ለፈጠሩልኝ፣ ልዩ አክብሮትና ፍቅር ለሰጡኝ፣ አብረውኝ ለተማሩ ጓደኞቼ ልዩ ክብርና ምስጋና አለኝ፡፡
 እኔ የምሰራበት ጤና ጣቢያ ገጠር ውስጥ ነው:: አሁን ከፍተኛ ውጤት ስላለኝ ከተማ ልግባ ሳልል፣ በተመደብኩበት ቦታ አቅሜ በፈቀደው መጠን በማገልገል፣ የሕዝቡንና የአገሬን ውለታ እከፍላለሁ::
ትዳር አልያዝኩም፡፡ እጮኛም የለኝም፡፡ አሁን ትምህርቴን በጥሩ ሁኔታ ስለጨረስኩ እጮኛ ፈልጌ አገባለሁ፤ ቤተሰብም እመሰርታለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡


___________________________                    ‹‹ሕግ እንዳጠና ፀልዬ ነበር፤ ፀሎቴ ተሳክቷል››


         ቤዛዊት ይርጋ እባላለሁ፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት አምስት ዓመታት የሕግ ትምህርቴን ተከታትዬ፣ ዛሬ በከፍተኛ ማዕረግ ስለተመረቅኩኝ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ጦር ሃይሎች እንዲሁም አስኮ አዲስ ሰፈር ነው፡፡ ወንድሞችና አንድ እህት አሉኝ፡፡ ለቤተሰቤ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከኬጂ እስከ አንደኛ ደረጃ ጥሩ የትምህርት ጊዜ ነበረኝ፡፡ ቤተሰቦቼም ያስጠኑኝ ነበር፡፡ ሀይስኩል ስገባ ቤተሰቡም ራሷን ችላለች በሚል ተወት አደረጉኝ፡፡ በተለይ አስረኛ ክፍል ላይ ትምህርቱን ተወት የማድረግ፣ ‹‹ፍንዳታነት›› መጣነው፡። በኋላ ግን ባነንኩኝ ‹‹ምን እየሆንኩ ነው›› በሚል ወደ ትምህርቴ ማተኮር ጀመርኩኝ፡። ከዚያ በኋላ በጥሩ ውጤት ነው ዩኒቨርሲቲ የገባሁት፡፡
ከልጅነቴ ጀምሮ የሕግ ትምህርት መማር እፈልግ ነበር፡፡ አባቴ ሕግ ሲማር የሚያመጣቸውን መጻሕፍትና ሌሎች ማቴሪያሎች በማንበብ ነው ፍላጎቱ ያደረብኝ፡። አገራችን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር የእኛ ሙያ ከፍተኛ ፈተና እንደሚገጥመው ባውቅም ፈተናውን ተቋቁሜ፣ አቅሜን ሁሉ ተጠቅሜ፣ በሙያዬ አገለግላለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በጣም የምወደው የምፈልገው ሙያ ነው፡፡ ትልቅ ስሆን ሕግ እንድማር ፀልዬ ሁሉ ነበር፡፡ ፀሎቴ ከተሳካ በሙያዬ ለማገልገል ፈተና አይበግረኝም፡፡
በዩኒቨርሲቲው ቆይታዬ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ:: የመጀመሪያው ከቤት ብዙ ወጥቼ የማላውቅ ልጅ ነበርኩና ቤተሰቦቼ እዚህ ዩኒቨርሲተ አድርሰውኝ ሲመለሱ ብቻዬን በመቅረቴ በጣም ከፍቶኝ ፈርቼ ነበር፡፡ ብቻዬን ስቆም እኔ ማን ነኝ የሚለው ነበር ትልቅ ፈተና የሆነብኝ፡፡ ከሌላው ተማሪ ጋር እንዴት ተላምጄ እቀጥላለሁ የሚለውም ትልቅ ጥያቄ ነበር፡፡  ሌላው ሴት ሆነሽ ወጣት ስትሆኚ የሚመጡ ፈተናዎችም ይኖራሉ፡፡ ይህን ሁሉ ነገር እንዴት አስተናግዳለሁ የሚለው ሁሉ አስጨንቆኝ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ በአግባቡ ተወጥቻቸዋለሁ፡፡ ለዚህ የረዳኝ ይዤው የመጣሁት ማንነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ በእኔ ላይ እምነት፣ ፈተናዎችን ሁሉ አሸንፌ በማዕረግ ለመመረቅ አብቅቶኛል፡፡____________________________                     ‹‹ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጣም አስደንግጦኝ የነበረው ጉርሻ ነው››

        ሴዛር ሮማኖ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከደቡብ ሱዳን ነው፡፡ የዛሬ ተመራቂ ተማሪ ነኝ፡፡ በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ፡፡ ሌሎች 27 ጓደኞቼ አማርኛ አይናገሩም፡፡ እኔ እንደሰማሽው አዳራሽ ውስጥ ንግግር ያደረግኩት በአማርኛ ነው:: ብዙ ሰውም ተገርሞ ነበር፡፡ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ፣ አማርኛ በጣም ከባድ እንደሆነ አስብ ነበር፡፡ እስከ ሶስተኛ አመት ምንም አማርኛ አላውቅም ነበር፡። አራተኛ አመት ስገባ አንድ ጓደኛዬ፤ ‹‹አንተ ሲዛር፤ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቆይተሃል፤ ለምንድነው አማርኛ የማትናገረው?›› አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ‹‹አይ አማርኛ ከባድ ነው አልኩት፡፡ ‹‹ለመሆኑ ሞክረሃል?›› አለኝ:: አልሞከርኩም አልኩት ‹‹ታዲያ ሳትሞክር ከባድ ነው ትላለህ እንዴ?›› ብሎ በጣም ተቆጣኝ፡፡ ከዚያ አማርኛ መማር ጀመርኩኝ፡፡
አንደኛ በዩቲዩብ ያሉ የአማርኛ ትምህርቶችን በማውረድ ለጀማሪ የሚሆኑትን መማር ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ ከኢትዮጵያዊያን ጓደኞቼ በንቃት በማውራት፣ አሁን እንደምታይኝ፤ በአማርኛ ቃለ ምልልስ እያደረግን ነው፡፡ መናገር ብቻ ሳይሆን ማንበብም መጻፍም እችላለሁ፡፡ አብዛኛውን ከዩቲዩብ ተምሬ ያው፤ የክፍል ጓደኞቼም እየረዱኝ ማለት ነው፡፡
ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ሱዳን ተገንጥላ ራሷን ከቻለች 8 ዓመት ሆኗታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡። በዚያን ጊዜ እኔ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበርኩኝ:: አሁን 25 ዓመቴ ነው፡፡ የትምህርት እድሉን የሰጠን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት አማካኝነት ከ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጣን የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ለደቡብ ሱዳን ትምህርት ሚኒስቴር ማመልከቻ አስገባን፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተን ጅማ ዩኒቨርሲቲ ገባን፡፡
ያለፉት አምስት አመታት ቆይታችን አሪፍ ነበር፤  ገና እንደመጣን ግን ከባድ ነበር፡፡ በተለይም ምግብ ላይ ከባድ ነበር፡፡ ቋንቋም፣ የኢትዮጵያን ባህልም አናውቅም ነበር፡፡ እንጀራ አቅቶን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንጀራ ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን እንጀራ የለም፡፡ ማሽላ በቆሎ ሩዝ ነው ምግባችን በአረብኛ ‹‹አሲዳ›› የሚባል ገንፎ የሚመስል ገንፎ ያልሆነ ምግብ ነው ባህላዊ ምግባችን፡፡ አሁን ግን እንጀራ በጣም ለምደናል፡፡ በጣም ነው የሚጣፍጠው:: ሽሮ ወጥ፣ ዶሮ ወጥ፣ ጎመን በስጋ… ሌሎችንም ባህላዊ ምግቦች ለምደን በደንብ ነው የምንበላው፡፡ በተረፈ በጣም አሪፍ ውጤት ነው ያመጣሁት:: በ3.68 ነው የተመረቅኩት፡፡ የደቡብ ሱዳን ጎበዝ ተማሪዎችም በማዕረግ ሲመረቁ አይተሻል፡፡ እኔ በእነሱ እኮራለሁ፡፡
ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በጣም ያስደነቀኝ ነገር ጉርሻ የሚባለው ነገር ነው፡፡ እኛ አገር ጉርሻ የለም፡፡ ለሕጻንና በህመም ምክንያት ራሱ መመገብ ለማይችል ሰው ያውም በማንኪያ ነው የሚጎርሰው፡፡ አንድ ቀን የተማሪ መመገቢያ አዳራሽ ስንገባ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ወንድ ጓደኛሞች ነበሩ፤ አንዱ ትልቅ ጉርሻ ወስዶ ሌላኛው አፍ ውስጥ ሲጨምር አይቼ በጣም ደነገጥኩኝ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? እንዴት ወንድን ወንድ ያጎርሳል? ብዬ ስጠይቅ በጣም ሳቁብኝና ይሄ የተለመደ የኢትዮጵያ ባህል እንደሆነ፣ አረጋጉኝ፡፡ አሁን ታዲያ ብቻ እኔ ራሴ ጉርሻ እወዳለሁ፡፡ ሰዎች ያጎርሱኛል፤ እኔም አጎርሳቸዋለሁ፡፡ ከኢትዮጵያዊ ፍቅረኛዬ ጋርም እንጎራረሳለን ነው፡፡


__________________________________                           ‹‹ቤተሰቦቼ ሳይማሩ እኔን ስላስተማሩኝ አከብራቸዋለሁ››


            ምናልከው ፋንታሁን እባላለሁ፡፡ የ24 ዓመት ወጣትና የአስተዳደርና ልማት ጥናት (ገቨርናንስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ስታዲስ) ትምህርት ክፍል ተመራቂ ነኝ፡፡ ትውልዴ ምሥራቅ ጎጃም፣ ደብረ ማርቆስ አካባቢ ሉማሜ ወረዳ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ አይነ ስውርነት ያጋጠመኝ ከሦስት ዓመት ዕድሜዬ ወደ አራተኛ  ስሸጋገር ነው፡፡ ያኔ  ብዙ አላስታውስም፡፡ እስከ ሰባት ዓመቴ ሳልማር ነው ያደግኩት፡። እርግጥ ቤተሰቦቼ ቄስ ት/ቤት ሊያስገቡኝና ሊያስተምሩኝ ብዙ ሞክረዋል፡፡ እኔ ልጅነትም ስላለ ቁጭ ብዬ እምቢ ብዬ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ስምንተኛ አመቴ ስሸጋገር (ሃይስኩል) አንድ ጊዜ ከበበው የሚባል አጎቴ፣ በሸዋና ወለጋ መካከል  የምትገኝ ባኮ የምትባል ከተማ ወሰደኝና እዛ በሚገኘው የአይነ ሥውራን አዳሪ ት/ቤት አስገባኝ፡።
በአዳሪ ት/ቤት ውስጥ ሁላችንም ተመሳሳይ ስለሆንን የውጭው ተፅዕኖ ብዙም አይሰማንም ነበር፡፡ ውጪ ሲወጣ ግን ያለው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ ባኮ የተማርኩት እስከ ስምንተኛ ክፍል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን አዲስ አበባ ሽሮሜዳ አመሃ ደስታ (እንጦጦ አምባ) መሰናዶ ትምህርቴን መነን ነው የተማርኩት በነዚህ ቆይታዎች ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ተማሪዎች አይቀርቡንም፡፡ እኛም ባኮ፣ አንድ አይነቶች አንድ ላይ ስላሳለፍን ሌሎችን አልለመድንምና እንፈራ ነበር፡፡ ይሄ ነገር በተለይ ለእኔ ብዙ ነገር አጉድሎብኛል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ሰበታ ውስጥ ‹‹መርሃ እውራን›› ከሚባል ማዕከል ለቤት ኪራይ ድጋፍ ይደረግልን ነበር፡፡ ሌላውን ግን በቤተሰብ ድጋፍ ነው ስማር የነበረው፡፡ ቤተሰቦቼ ገጠር ነው ያሉት፡፡ አሁን አንድ አጎቴ እዚህ አዳራሽ ውስጥ ይገኛል፤ ሊያስመርቀኝ መጥቷል፡፡
ዛሬ በማዕረግ ለመመረቄ ጥንካሬ የሆነኝ፣ ራሱ ያለሁበት ሁኔታ ነው፡። እንኳን አካል ጉዳተኛ ማንኛውም ሰው ካልተማረ ዋጋ የለውም፡፡ መማር በተለይ ለኛ ነገሮችን ያቀልልናል፡፡ ከዚያ በተረፈ ከጀርባዬ ያሉት ቤተሰቦቼ ትጋት፤ ብርታትን ይሰጠኛል፡፡ እኔን ሰው ይሆናል ይለወጣል ብለው በማስተማራቸው፣ በጣም ነው የማከብራቸው፡፡ እነሱም ያከብሩኛል፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ጠንከር ብዬ እንድማርና ለዚህ ውጤት እንድበቃ አድርጎኛል፡፡
እንዳልሽው የተማርኩበት ዘርፍ ቶሎ ስራ ያስገኛል ብዬ አላምንም፤ ግን በተገኘ ጊዜ ጠብቄ ወይም ካጠናሁት ትምህርት ጋር ተጓዳኝ በሆነ ሥራ ተሰማርቼ ራሴንም አገሬንም ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ ውጤቴ 3.55 ነው፡፡ ጥሩ ውጤት ስላለኝ በስራ ፍለጋው እተጋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


Read 4779 times