Print this page
Saturday, 20 July 2019 11:48

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ለ3ኛ ጊዜ በኤርትራ ጉብኝት አድርገዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ከትናንት በስቲያ ሃሙስና ትናንት በኤርትራ ያልተጠበቀ የስራ ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ጋር በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስሮች ላይ ትኩረት አድርገው መወያየታቸው ተገለጸ፡፡
ከዚህ ቀደም በወደብ አጠቃቀምና  በድንበር አካባቢ በሚዘረጋው የጋራ የንግድ ትስስሮሽ ጉዳይ ላይ በስፋት መወያየታቸውን ያስታወሰው ‹‹ኤርትራያን ፕሬስ››፤ ሁለቱ መሪዎች የደረሱባቸውን ስምምነት በተመለከተ ግን ያለው የለም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ወደ አስመራ ያቀኑት ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ጋር ሲሆን አየር መንገድ ባለፈው አንድ አመት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዘረጋው የትራንስፖርት ግንኙነት ከፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ምስጋና እንደተቸረው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረበትን 1ኛ አመትም ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 11 ያከበረ ሲሆን በዚህ አንድ አመት ውስጥ በየቀኑ ሁለት ጊዜ ከአዲስ አበባ አስመራ በረራ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
አየር መንገዱ ለአንድ ዓመት በሰጠው አገልግሎትም 130ሺህ ያህል ተጓዦችን በሁለቱ ሀገሮች መካከል ማጓጓዙ ታውቋል፡፡ በፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ባሻገር በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነትና ቀጠናሮ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም የኤርትራ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገፃቸው አመልክተዋል፡፡  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ጥረት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዳግም ወደ ሠላም ከተመለሠበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራን ሲጐበኙ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን በተመሳሳይ የሀገረ ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂም ለሶስት ጊዜያት ያህል ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከሁለት አስርት ዓመታት የፍጥጫ ጊዜያት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ማድረጋቸውን ተከትሎ ከሣውዲ አረቢያና ከተባበሩት አረብ ኤምሬት መሪዎች ከፍተኛ የክብር ኒሻን መሸለማቸውም አይዘነጋም፡፡

Read 7935 times