Saturday, 20 July 2019 11:49

የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ ላይ የደቡብ ክልል ም/ቤት አፋጣኝ ውሣኔ እንዲሰጥ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

የዎላይታ የ“ክልልነት” ጥያቄ በአስቸኳይ ለደቡብ ክልል ም/ቤት ቀርቦ ውሣኔ እንዲሰጥበት የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) የጠየቀ ሲሆን የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ በበኩላቸው፤ ህዝቡ የክልልነት ጥያቄውን በሠላማዊ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ፤ የዲኢህዴንን ውሣኔም እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡
የዎላይታ ህዝብ በ1983 የሽግግር ወቅት ራሱን ችሎ በክልል ዘጠኝ መደራጀቱን፤ ኋላም በድንገተኛ ውሣኔ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተጨፍልቆ፣ የደቡብ ክልል በሚል እንዲዋቀር መደረጉን ያስታወሰው የዎብን መግለጫ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ህዝቡ ክልል የመሆን ፍላጐቱን በተለያዩ አግባቦች ሲያንፀባርቅና ሲጠይቅ መቆየቱን አውስቷል፡፡
 በ1992 ዓ.ም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የብሔሩ ተወላጆችም በቋንቋ አጠቃቀምና በክልልነት ጉዳይ ላይ ሠላማዊ ሠልፍ አድርገው እንደነበርም ንቅናቄው አስታውሷል፡፡  የዎላይታ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ፤ ለአንድ መቶ ሃያ አምስት አመታት የዘለቀ መሆኑን የጠቆመው ዎብን፤  አሁን ያለው ህገመንግስት በፈቀደው በክልል የመደራጀት መብት መነሻነት ከህዝብ ቁጥር አንፃርና ዎላይታ የቀደመ የራሱ አስተዳደር የነበረው መሆኑን ታሣቢ በማድረግ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀበሌዎች እስከ ዎላይታ ዞን ም/ቤት ድረስ ጉዳዩን በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ህዝበ ውሣኔ እንዲመቻች፣ ለክልሉ ም/ቤት የውሣኔ ሃሳቡ እንዲቀርብ መጠየቁን ይገልጻል፡፡
ለ11 ቀናት፤ ስብሰባ አድርጐ ሐምሌ 8 ቀን 2011 የስብሰባውን ውጤት ያሳወቀው የክልሉ ገዥ ፓርቲ ደኢህዴን፤ የዎላይታን ጥያቄ አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሣኔ በአስቸኳይ በግልጽ እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡
የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በበኩላቸው፤ በሰሞኑ የደኢህዴን ስብሰባ ላይ የክልሉን ጥያቄዎች ለመፍታት በምሁራን በቀረበው ጥናትና ምክረ ሃሳብ መሠረት፣ የሲዳማ ህዝብ ክልል ሆኖ ከተደራጀ በኋላ ቀሪዎቹ የክልሉ ህዝቦች በአንድ ላይ ይቀጥሉ መባሉን ገልጸዋል፡፡
ይህ ውሣኔም የዎላይታን ህዝብ ጥያቄ ያላስተናገደና ወደ ጐን የገፋ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይ ጉዳዩን በድጋሚ መታየት እንዳለበት፤ ህዝቡ በሠላማዊ መንገድ ክልል የመሆን ጥያቄውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ዳጋቶ አሳስበዋል፡፡


Read 9718 times