Saturday, 20 July 2019 11:51

ያልተከፈለ ዕዳ ምንጊዜም ዕዳ ነው!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንዳንድ ተረቶች ከአንድ ዘመን ይልቅ ሌላ ዘመን ላይ ግጥም፣ ልክክ ይላሉ፡፡ ይሄኛው ተረትም ሌላ ዘመን ላይ ተርከነው ዛሬም አለሁ አለሁ ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ አዳኝ ወደ ጫካ ሄዶ ሲመለስ፣ አንድ ወዳጁ ያገኘዋል፡፡
ወዳጁ - “ወዳጄ ከየት ትመጣለህ?”
አዳኙ፡- “ከጫካ”
ወዳጁ፡- “ምን ልታደርግ ጫካ ገባህ?”
አዳኙ፡- “አደን አድናለሁ ብዬ”
ወዳጁ፡- “አይ ወዳጄ፤ ዛሬ አውሬው ሁሉ ሸሽቶ ምን የሚታደን አለ ብለህ ለፋህ?”
አዳኙ፡- ‹‹ከሰው የከፋ አውሬ አይጠፋም ብዬ ነው››
ወዳጁ፡- “ከሰው የከፋ?”
አዳኙ፡-  “እንዴታ!”
ወዳጁ፡- “እርግጠኛ፤ ነህ ከሰው የከፋ አውሬ አለ?”
አዳኙ፡- “በጭራሽ አላጣም”
ወዳጁ፡- “አይ ወዳጄ፣ ልፋ ቢልህ ነው!”
አዳኙ፡- “ለምን?”
ወዳጁ፡- “ታዳኝ አውሬ እኮ የለም፡፡ አውሬ ለመፍጠር ከፈለግህ፣ እንደፈረደብህ ራስህ ፍጠር እንጂ ያሉት ወይ ታድነዋል፣ ወይ አገር ለቀው ሄደዋል!”
አዳኙ፡- “የሄዱበት አገር ሄጄ አድናቸዋለሁ”
ወዳጁ፡- “እዚያማ አንተ ሳይሆን እነሱ ናቸው የሚያድኑህ!”
አዳኙ፡- “ሂሳቡ ስንት ነው?”
ወዳጁ፡- የምኑ?”
አዳኙ፡- “እነሱ የሚገሉኝ ከሆነ ሥራቸውን ለሠሩበት ሂሳባቸውን ልሰጣቸው ብዬ ነው!”
***
ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋችን ዕዳ አለበት፡፡ በቀላሉም ተከፍሎ አያልቅም፡፡ የመርገምት ሁሉ መርገምት ዕዳ ይዞ መጓዝ ነው፡፡ ዕዳ ደግሞ ዕዳ ከፋይ ትውልድ ይጠይቃል፡፡ እኛ ደግሞ እንደዚያ ያለ ትውልድ ገና አልፈጠርንም፡፡ ብዙ ትውልድ ቀያይረናል፡፡ ረብ ያለው፣ ፍሬ የሚያፈራ ትውልድ ግን በእጃችን የለም፡፡ ያ ደግሞ የሚነግረን ባዶ መሆናችነን ነው፡፡ ባዶነት ማንንም አኩርቶ አያውቅም፡፡
 All that has gone before
Was a preparation to this,
and this is only preparation
to what is to come!
“እስከዛሬ የሆነው ሁሉ ለአሁኑ መዘጋጀት ነበር፡፡ ይሄ የዛሬው ደግሞ ለመጪው ማዘጋጃ ነው፡፡ “ጉዳዩ የሚመጣው አይታወቅምም የሚል ስሜት አለው፡፡ ዛሬ የደረስንበትን ያየ፣ ነገ ይሄ ይሆናል ማለት አይቻለውም፡፡
ፀሐፍት የሚሉትን ማድመጥ በጣም ደግ ነገር ነው፡፡     “a change is as good as rest” የለውጥ የእረፍትን ያህል ፀጋ ነው፡፡ ሆኖም ለውጣችን ወደተሻለ አቅጣጫ ካልሆነ፤ መልካም መንገድ ላይ አይደለንም፡፡ እረፍትም አይሆንልንም፡፡
ዛሬም እንደ ትላንት ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› ማለት የለብንም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ገጣሚ እንዳለው፤
‹‹ነገ፤
እባክህ አትምጣ
እኔው እመጣለሁ
ደሞ ዛሬ ብዬ እሞኝብሃለሁ“
ማለት ተገቢ ነው፡፡ ነገን ማን ያምነዋል? በመንግስት አናምነውም፡፡ በተቃዋሚዎች አናምነው፡፡ በራሳችን በህዝቦችም እንኳን አናምነውም፡፡ ማረጋገጫው ዕውነተኛ ለውጥ ነው፡፡ የሚያሳምን ለውጥ፡፡ እስአሁን ካየነው የተለየ፡፡ ደመ ግቡ ለውጥ፡፡ የተማረ ለውጥ! ወግ ማረግ ያለው ለውጥ!
ይህን ሁሉ ለውጥ የምንመኘው እኛ ተለውጠን አገር መለወጥ ነው፡፡ ያ ደግሞ “የአዲስ ግልባጭ” ምኞት አይደለም፡፡ የጥንት የጧት ህልማችን አይደለም፡፡ የልብ ትግላችን ነው!! ዞሮ ዞሮ ያልተከፈለ ዕዳ ምንጊዜም ዕዳችን ነው፡፡ እንበርታና እንክፈለው!  

Read 10525 times