Saturday, 20 July 2019 11:52

ሱዳን ልትድን ነው መሰል…

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

 • በዩኤንና በአፍሪካ ሕብረት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር እገዛ።
    • ችግርን ማውገዝና ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ በሚያዛልቅ መፍትሔ መገንባትንም ያጣመረ - የተደመረ መንገድ!
      
      ለበርካታ ወራት ስትታመስ የከረመችው ሱዳን፣ ‹‹አለፈላት፣ ከአምባገነንነት ተገላገለች›› ተብሎ፣ በእልልታና በጭብጨባ ከተበሰረ በኋላ፤ ሳምንት ሳይሞላት ወደ ባሰ ቀውስ ማምረቷ እንደማይገርም ይገልጻል - ከወር በፊት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የቀረበው ጽሑፍ።
እንዲያውም፣ ማምለጫ በሚያሳጣ የዘመናችን ቅጥ አልባ ፖለቲካ አማካኝነት፣ ወደ ከፋ አምባገነንነት፣ ወይም ወደለየለት ትርምስ እየገባች እንደሆነ፣ የአገሪቱ ተስፋም እንደጨለመ ጽሁፉ ይተነትናል። የመንና ሶማሊያን፣ በተለይ ደግሞ ሊቢያንና ሶሪያን በምሳሌነት በመጥቀስም፣ የሱዳንን መከራ ለማስረዳት ይሞክራል።
ከአውሮፓ ሕብረት የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን፣ የዩኤን የአቋም መግለጫዎችንና የአፍሪካ ሕብረት ውሳኔዎችን ለሚሰማ ሰው ግን፣ የሱዳን ጉዳይ፣ ያን ያህልም አሳሳቢ አልነበረም። የአገሪቱ ችግር በጣም ቀላል፣ መፍትሄውም ጊዜ የማይፈጅ ፈጣን እንደሆነ ነው የሚያስመስሉት።
በእርግጥም ፣ በእንዲህ አይነት የፖለቲካ ስሌት፣ ‹‹የሱዳን ችግር››፣ የጄኔራል ዑመር አልበሽር አስተዳደር ብቻ ነበር። ‹‹መፍትሄውም››፣ ጄነራሉን ከሥልጣን ማውረድ ብቻ ነው - በቃ ችግር ተወገደ ተብሎ የምስራች ይበሰራል። ምን ያደርጋል?
‹‹ችግር ተወገደ›› ማለት፣ ‹‹መፍትሄ ተገኘ›› ማለት አይደለም፡። ይሄ እንዴት ይጠፋቸዋል? በሶማሊያ አይተውታል። የዚያድ ባሬ ወታደራዊ መንግስት በተቃዋሚዎች ተሸንፎ ሲፈርስ፣ ‹‹ለውጥ መጣ››፣ ‹‹ከባድ ችግር ተወገደ›› ብሎ በደስታና በፌሽታ መጨፈር እንደማለት ነው።

በነባር ችግር ምትክ የባሰ ሲመጣስ?
‹‹የድሮው ፈረሰ፣ ነባሩ ተለወጠ›› ማለት፣… ‹‹ከቀድሞ የበለጠ አዲስ ነገር ታነፀ፣ በመጥፎው ፋንታ፣ መልካም ምትክ ተፈጠረ›› ማለት እንዳልሆነ፣ የሶማሊያ ታሪክ፣ ገና ተተርኮ ያላለቀ አሳዛኝ ምሳሌ ነው። ይሔውና 30 ዓመት ሙሉ፣ መከራዋን ትበላለች። የዚያድ ባሬ አምባገነንነት፣ በበርካታ የጦር አበጋዞች አምባገነንነት ነው የተተካው። በዘር በሉት በጎሳ፣ በየአቅጣጫው የተቧደኑ ከደርዘን በላይ ታጣቂ ነውጠኞች፣ አገሪቱን በጦርነት አተራምሰው፣ አውድመው፣ አንድደው፣ የእልቂትና የስደት አገር አድርገዋታል።
የጦር አበጋዞቹ ወይም በጎሳ የተቧደኑት ነውጠኞች ለበርካታ ዓመታት የፈፀሙት ጥፋትና ያስከተሉት ትርምስ ሳያንስ፣ ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር የሚያደባልቁ ክፉዎች፣ የጭፍንነትና የሽብር፣ የአምባገነንነትና የጭካኔ መዓት ጨመሩባት።
መጀመሪያ፣ ከዚያድ ባሬ ወታደራዊ አምባገነንነት ወደ ጦር አበጋዞች አምባገነንነትና ወደ ጎሳ ነውጠኞች ተለወጠ፡። ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ሆነ። በዚህም አላበቃም። የአልሸባብ ሽብርና ጭካኔ አገሪቱን አተራመሰ። ከማጡ ወደ ረመጡ እንዲሉ።
ነባሩን ችግር ማስወገድ ማለት፣ አዲስ መፍትሄ ማግኘት ማለት አይደለም። ለውጥ ማለትም፣ ያኛው በዚህኛው ተለወጠ ማለት እንጂ፣ መጥፎ በጥሩ ተተካ ማለት አይደለም።
ነገርየው ያን ያህል ውስብስብ አይደለም። ነባሩን ማፍረስና ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ የተሻለ ምትክ መገንባትም ያስፈልጋል። ያኛውን መጥፎ አምባገነን መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ ተተኪ መፍጠርም አብሮ መታሰብ አለበት። መፈንቀለ መንግሥትን የማውገዝና ወታደራዊ አምባገነንነትን የማስወገድ ያህል፣… አገርን የሚያፈርስ፣ ሚሊዮኖችን ለእልቂትና ለስደት የሚዳርግ የእልፍ አምባገነኖች ትርምስ እንዳይፈጠርም ጭምር አስቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡።
እንደ ሶሪያ፣ ከ500 ሺሕ በላይ ሰዎችን ለሞት፣ ግማሽ ያህሉን ሕዝብ ለተፈናቃይነትና ለስደት የሚዳርግ፣ ከዚያም ነባሩን አምባገነንነት የሚያባብስ ለውጥ፣ የትም መቼም ቢሆን ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም።
እንደ ሊቢያና እንደ የመን፣ ነባር አምባገነንንና ወታደራዊ አገዛዝን በማስወገድ፣ እጅጉን የከፋ ፋታ የለሽ ስርዓት አልበኝነትን፣ ጦርነትንና ትርምስን በቦታው መተካት… በጭራሽ መፍትሄ አይደለም። ለውጥ ስለሆነ ብቻ መልካም ለውጥ ሊባል አይችልም።
እንዲህም ሆኖ፣ የአፍሪካ ሕብረትና እነ ዩኤን፣ የሱዳን ጉዳይ ብዙም አላስጨነቃቸውም። ችግሩ ቀላል፣ መፍትሄው ፈጣን እንደሆነ ለማሳየት ይመስል፤ ወታደራዊው መንግስት በ15 ቀን ለሲቪል በማስረከብ ስልጣኑን መልቀቅ አለበት የሚል ውሳኔ ታወጀ። አዎ፣ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘ ወታደራዊ ሃይል፣ እንዳሻው በሥልጣን ላይ እንዳይቆይ መከላከል ተገቢ ነው። ነገር ግን አምባገነንን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ በቦታው ትርምስ እንዳይፈጠር ለማሰብ አለመፈለጋቸው ያስገርማል። በዚህም ምክንያት ነው፤ የሱዳን ተስፋ እየጨለመ መሆኑን የሚገልጽ ጽሑፍ በአዲስ አድማስ የታተመው - የዛሬ ወር።
በእርግጥም፣ በማግስቱ እሁድ፣ ውጥረቱ እየከረረ፣ አመፁ እየጦዘ ሊፈነዳ መቃረቡ ሲታይ፣… በሌላ በኩልም፣ በሣልስቱ ሰኞ እለት ወታደራዊው መንግሥት የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ዘመቻ ማካሄዱ ሲጨመርበት፣… ወደ ለየለት የጭካኔ አምባገነንንነት፣ ወይም ደግሞ በተቃራኒው ወደ ለየለት ትርምስ (ማለትም ደርዘን የየአካባቢው አምባገነኖች፣ ሺ የየመንደሩ የጎበዝ አለቆች ወደሚፈነጩባት ትርምስ) እየገባች ነው መባሉ አይገርምም።
አገሪቱ ከተተራመሰች በኋላ፣ እነዩኤንና የአፍሪካ ሕብረት፣ ‹‹ሁሉንም ፓርቲዎች ያሰባሰበ ድርድር››፣ ‹‹ሁሉንም የሲቪል ማህበራት ያሳተፈ ጉባኤ››፣ ‹‹ሰላም ወዳድ ሴቶችን ያንቀሳቀሰ እርቅ››፣ … ‹‹Dialogue, consultation, discource, conversation, compromise, negotiation…›› የሚሉ የ‹‹ሱታፌ›› ጥሪዎችን ማዝነባቸው አይቀርም።
ነገር ግን፣ የነ ዮኤን እልፍ የድርድርና የተሳትፎ አይነቶች፣ የሊቢያና የየመን የመከራ ዓመታትን ከማራዘም የተለየ ፋይዳ አላስገኙም። በእንግሊዝ ፓርላማ አማካኝነት የተካሄደ ዝርዝር ጥናትም ይህንን ይመሰከራል። አምባገነንን ማስወገድ፣ በቂ መፍትሄ አይደለም። ደርዘን አውራዎችና ሺ ጥቃቅን አምባገነኖች  በቦታው ከተተኩ፣… ከማጥ ወደ ረመጥ ሆኖ ያርፈዋል። የዩኤን፣ የአውሮፓ ሕብረት አገራትና የኤንጂኦ ልዑካን፣ በሊቢያ ያስገኙት ውጤትም፣ ትርምስ ብቻ እንደሆነ የእንግሊዝ ፓርላማ ጥናት አንድ በአንድ ይዘረዝራል። መነበብ ያለበት ሪፖርት ነው።
የተደመረ መንገድ።
በአዲስ አድማስ የወጣው ጽሑፍ፤ በነዩኤን እጅ፣ ሱዳን ተስፋ እንደማይኖራት መግለጹ፤ እውነት አለው። ግን አንድ ነገር ስቷል። የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ለሱዳን እንደሚደርሱላት ማን አወቀ?!
ወታደራዊ መንግስት ለረዥም ጊዜ ሥልጣን ላይ እንዳይቆይ የሚከላከል ብቻ ሳይሆን፣ በወታደራዊ መንግስት ምትክ አገሪቱንና ጎረቤቶችን ሁሉ የሚያናጋ ትርምስ እንዳይፈጠር የሚረዳ የመፍትሄ መንገድ የተከፈተው፣ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ፈጣንና ብልህ እገዛ ነው። ችግርን ከማስወገድ ጐን ለጐን፣ መፍትሄ መፍጠርንም ያሟላ፣ የመደመር መንገድ ጠቀመ!
ሱዳን፣ ከእነሶሪያ ዓይነቱና ከእነሊቢያ የጦርነት ቀውስና ምስቅልቅል ለጊዜው ተርፋለች። የመደመር መንገድን ካወቁበት፣ ሁልጊዜ ማስተዋልና መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገ ከተገነዘቡ፣ የማይፈልጉትን ነገር ለመቃወምና ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ የሚፈልጉትን ነገር በውል ለማወቅና ለመገንባት ማሰብ እንደሚኖርባቸው ካልዘነጉ፣ አመቱን መዝለቅ፣ የጨለመውን ተስፋ ማፍካት ይችሉ ይሆናል።

Read 909 times Last modified on Saturday, 20 July 2019 12:08